የተጣሩ መረጃዎች

አምስቱ የአፍሪካ ሀገሮች ግማሽ ያህል የሚሆነውን የአፍሪካ የሀገር ውስጥ ምርት ይሸፍናሉ?

ከሰሞኑ በአንድ የx ወይም በቀድሞ ስሙ ትዊተር ላይ የተጋራ ፖስት በያዝነው ዓመት በፈረንጆቹ 2024 ግማሽ የሚሆነውን የአፍሪካ የሀገር ውስጥ ምርትን (GDP) የሚመጣው ከአምስት ሀገሮች እንደሆነ በመግለፅ እነሱም አልጄርያ ፤ ግብፅ ፤ ኢትዮጵያ ፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ እንደሆኑ ይናገራል።ሀቅቼክ መረጃ እና ምንጮችን አመሳክሮ ይህ መረጃ እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል።    ሊንክዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ (IMF) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ከአፍሪካ የሀገር ውስጥ ምርት ትልቁን ኢኮኖሚ የሚይዘው ከአልጄርያ ፤ ግብፅ ፤ ኢትዮጵያ ፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ምርት (GDP) እንደሆነ ገልጿል። 

ሊንክ

ሀገራትየአሜሪካ ዶላር (በቢልዮን) 
ደቡብ አፍሪካ373.233
ግብፅ347.594
አልጄርያ266.780
ናይጄርያ 252.738
ኢትዮጵያ 205.130

የ2024 የሀገራት GDP ሰንጠረዥ

በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2024 እንደተለቀቀው የአለም ኢኮኖሚ ሪፖርት ከሆነ ከእነዚህ አምስት ሀገሮች የሚመረተው ምርት የአህጉሪቱን ግማሽ የሚሆነውን ምርት (GDP) እንደሚይዝ ያስቀምጣል። በፈረንጆቹ 2024 ከኤርትራ እና ከምዕራብ ሰሀራ ውጭ የአህጉሪቱ አጠቃላይ GDP 2,819.317 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን እነዚህ አምስት ሀገራቶች ከዚህ ውስጥ 1,445.475 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን ይሸፍናሉ።


ሊንክ

አለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ (IMF) ባስቀመጠው ትንተናም የአፍሪካን ኢኮኖሚ በመምራት ዘንድ እነዚህ የአፍሪካ ሀገራቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ አጽኖት ስጥቶ ገልፆታል። አልጄርያ ፤ ግብፅ ፤ ኢትዮጵያ ፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍርካን በተለያዩ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው በአህጉሪቱ በሚታዩ የኢኮኖሚ ምህዳር ውስጥ ትልቅ እና ቁልፍ ተዋናዮች በመሆን ጠንካራ እድገትን አሳይተዋል።    

እነዚህን መረጃዎች ስናጠናክር ይህ በX ወይም በቀድሞ መጠሪያው ትዊተር ላይ ምንጭ በመጥቀስ የተጋራው መረጃ ትክክል መሆኑን ሀቅቼክ ማረጋገጥ ችሏል።

         

ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን በሀገር ውስጥ ማተም ልትጀምር ነው?

እንደ ዩቲዩብ ባሉ የኦንላይን መድረኮች ላይ ከዘጠኝ ሺህ በላይ እይታዎች እንዲሁም በቲክቶክ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ እይታዎችን በማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለው ይህ ቪዲዮ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቅ መሠረተ ልማት ለመገንባት ከጃፓን ኩባንያ TOPPAN GRAVITY ጋር ስምምነት መፈራረሟን ይገልፃል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ቪዲዮ በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን ሀገር ውስጥ ማትም እንደሚያስችላት ይናገራል።

ሊንክ

ቪዲዮው መግለጫውን ለመደገፍ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትን እና የTOPPAN GRAVITY አስተዳዳሪዎችን ምስል ከቪዲዮው ጋር በማያያዝ ተጠቅሟል።

ሊንክ

ነገር ግን ሀቅቼክ መረጃውን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ስምምነቱ ለገንዘብ ህትመት ሳይሆን እንደ ፓስፖርት ፤ ብሄራዊ መታወቂያ ፤ ኤቲኤም ካርዶች ፤ የማስተርካርድ ምርቶች እና ሌሎች የመንግስት ሰነዶችን የመሳሰሉ ከፍተኛ የደህንነት ሰነዶችን ለማምረት እንደሆነ አረጋግጧል። 

በሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው በኢትዮጵያ እና በTOPPAN GRAVITY መካከል የተደረገው ስምምነት ደህንነታቸው የተጠበቀ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፓስፖርት፡  ለዜጐች ደህንነቱ የተጠበቀ የጉዞ አገልግሎት መስጠት ለማስቻል ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ካርዶች፡ የማንነት ማረጋገጫ እና የደህንነት እርምጃዎችን ለማሳደግ ፤ ኤቲኤም ካርዶች፡ ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ፤ ማስተር ካርድ ምርቶች፡ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የክፍያ ግብይቶችን ለማስቻል ሲሆን እነዚህ ሰነዶች በውስጣቸው ማይክሮ ቺፖችን በማካተት ደህንነታቸውን እና ትክክለኛነትን የበለጠ እንዲያሳድጉ ተደርገው የሚመረቱ ይሆናል።

ከፋና ዘገባ በተጨማሪ TOPPAN GRAVITY በድህረ-ገጹ ስለ ስምምነቱ እንደገለፀው “በኢትዮጵያ የሚገነባው የህትመት ፋብሪካ እንደ መጀመሪያ እርምጃ የቶፓን ግሩፕ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኢትዮጵያ የተሟላ አቅርቦት አቅም ለመፍጠር አቅዷል። ለወደፊቱ ለኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች መታወቂያ እና ፓስፖርት በማምረት በአፍሪካ ገበያ መፍትሄዎችን ይዞ የመምጣት ትልቅ ሃሳብ እንዳለውም ጠቁሟል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የፓስፖርት እና የመታወቂያ ደንቦችን በማውጣት ከአካባቢው ፍላጎቶች ጋር የተጣጣመ የአሰራር ዲዛይን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል።”

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ገንዘብ ማተምን እንደማይጨምር ለሀቅቼክ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ለውጥ ስታደርግ ከተለያዩ የገንዘብ ማተሚያ ድርጅቶች ጋር ስምምነቶችን ተፈራርማለች። ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት የገንዘብ ኖት ላይ  የተለያዩ ለውጦችን ብታደርግም፣ ስለ ገንዘብ ህትመት ይህን ያህል ሰፊ መረጃ ማግኘት ቀላል አይደለም።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ካደረገችው የገንዘብ ኖት ቅያሪ ባለፈ በታሪክ ባለፉት ዓመታት በርካታ ግዜ የገንዘብ ኖት ለውጦችን አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ጉዞ በ1895 ዓ.ም ሲጀምር ፣ 200,000 ዶላር ዋጋ ያለው አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ሥርዓት በ1886 ዓ.ም  በፓሪስ ሚንት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደተመረተ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የባንክ ኖቶች ወይም የወረቀት ገንዘቦች በ1907 ዓ.ም በአቢሲኒያ ባንክ ነበር የተዋወቁት ፣ ይህም ሳንቲሞችን እንደ መገበያያ ከመጠቀም ባሻገር የተደረገ ለውጥ ነው ። የአቢሲኒያ ባንክ በ5፣ 10 ፣ 100 እና 500 ዋጋ የመጀመሪያዎቹን የባንክ ኖቶችን አስተዋቆ ነበር።

በህዳር ወር 1990 ዓ.ም በሃገሪቱ ስልጣን ላይ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በደርግ ዘመን የነበረው ገንዘብ ላይ ጥቃቅን ለውጦችን እና የቀለም ማሻሻያዎችን አድርጎ ነበር። ከዚህ በተጨረማሪ የከፍተኛ ደረጃ ኖቶች በተለይም የ50 እና 100 ብር ሂሳቦች ላይ የተሻሻሉ የደህንነት ማረጋገጫዎች እና የተለየ ዲዛይንን አካቷዋል።

በመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተሻሻሉ የደህንነት ባህሪያትን እና ሌሎች ልዩ ክፍሎችን የያዘ አዳዲስ የገንዘብ ኖቶች አስተዋውቋል። አዲስ የተዋወቁት የገንዘብ ኖቶች ላይ ከ10 ፣ 50 እና 100 ቢል ኖቶች በተጨማሪ የ200 ብር ኖቶች እንዲቀርቡ ተደርገዋል። 

ምስል

ብሔራዊ ባንክ በግንቦት ወር 2000 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማተሚያ ድርጅቶችን በመጋበዝ ከ1.1 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ለማምረት ጨረታ አቅርቧል።

በ2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁለት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማተሚያ ኩባንያዎች – ጂሴኬ እና ዴቭሪየንት ጂም ኤች (ጀርመን) እና ደላሩ (ዩኬ) – የተለያዩ የኢትዮጵያ ብር ኅትመቶችን ለማተም የብዙ ሚሊዮን ዶላር ውል ሰጥቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። 

ሐምሌ 24, 2005 ዓ.ም በሚዲያዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሱዳን የብር ኖቶችን ለማሳተም እያሰበ እንደሆነ ዘገባዎች ወጥተው የነበረ ሲሆን የባለሙያዎች ቡድንም ወደ ሱዳን በመጓዝ በ1986 የተቋቋመውን የሱዳን ገንዘብ ማተሚያ (ኤስ.ፒ.ፒ.) የተባለውን የግል ድርጅት ጎበኝተዋል። በሪፖርቱ መሠረት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ባለሙያዎች ወደ ሱዳን ሄደው ኤስ.ፒ.ፒ. ማሽኖች እና የኩባንያውን አቅም እንደገመገሙ መረጃዎች ያሳያሉ።

ታህሳስ ወር, 2007ዓ.ም አዲስ ፎርቹን የተባለው ጋዜጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገር ውስጥ ጥሬ ገንዘብ እና በተጨማሪም የተለያዩ የደኅንነት ሰነዶችን ለማተም የሚያስችለውን ማተሚያ ፋብሪካ የማቋቋም ሂደት ላይ እንደሆነ አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን ዶቼ ቬለ መጋቢት 5 ቀን, 2014 ዓ.ም ባወጣው ፅሁፍ መሰረት ኢትዮጵያ ገንዘቧን እንድትታትም ከብሪታኒያ ግዙፉ የብር ኖት ማተሚያ ዴላሩ ጋር ስምምነት እንዳደረግች ገልፆ ነበር።

ምስል

ግንቦት 21 ቀን ,2016 ዓ.ም በወጣው ሌላ ዘገባ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ገንዘባቸውን በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ እንደሚያሳትሙ ተገልጿል። ከዚህ ዘገባ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን ዴላሩ በተባለ የእንግሊዝ አታሚ እንደምታሳትም የሚገልፁ መረጃዎች ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ምንዛሪ ህትመት ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ቢነሱም እስካሁን ከመንግስትም ሆነ ከብሄራዊ ባንክ የተገኘ ይፋዊ መረጃ የለም። ነገር ግን አሁን ላይ ኢትዮጵያ ‘ገንዘብ ማተሚያ ማዕከል’ ልትገነባ ነው እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ሃሰተኛ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በ TOPPAN GRAVITY መካከል የተደረገው ስምምነት የገንዘብ ህትመትን አይጨምርም።

የቪዲዮው አሳሳች መልዕክት የስምምነቱን ወሰን ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ቢችልም መረጃዎችን ከማሰራጨት በፊት ታማኝ ከሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።  ከፍተኛ የደህንነት ሰነዶች ላይ የተደረገውን ስምምነት ብር ለማተም በማለት በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል።

ኢትዮጵያ ከTOPPAN ግራቪቲ ጋር ገንዘብ ለማተም ስምምነት ተፈራረመች የሚለው ቪዲዮ ሀሰት ነው። 

ሀሰት፡ ይህ ቪድዮ በጎፋ ዞን የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ አያሳይም

በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም በጎፋ ዞን, ኢትዮጵያ የደረሰውን ከባድ የመሬት መንሸራተት ያሳያል በሚል የመግለጫ ፅሁፍ የተጋራ አንድ የቲክቶክ ቪዲዮ ከመቶ ሺህ ጊዜ በላይ ሲጋራ ከሶስት ሚሊዮን በላይ እይታዎችን ማግኘት ችሏል።

በሐምሌ ወር ቲክቶክ ላይ የተጋራው ቪዲዮው የሚያሳየው የመሬት መንሸራተት ሲሆን ፍርስራሾች ፣ ዛፎች እና አቧራ እንደጎርፍ ሲወርድ የሚያሳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ቪድዮ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ውስጥ የተከሰተ እንደሆነ እና በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 300 እንደደረሰ ይገልፃል።

እንደ ቢቢሲ እና ሌሎች የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ፤ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም አመሻሽ እና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ማለዳ ላይ የመሬት መንሸራተት ተከስቷል።

ቪዲዮ

አልጄዚራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቦታው ተሰብስበው እና ሌሎች ከሥሩ በአደጋው ወቅት ፍራሹ የተጫነባቸውን ሰዎች ፍለጋ አፈር ውስጥ ሲቆፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮም አጋርቷል።

እሁድ እለት የጣለው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተትን ሲያስከትል በአቅራቢያው ካሉ መንደሮች የመጡ የፖሊስ መኮንኖች፣ መምህራን እና ነዋሪዎች በሰኞ ዕለት ነፍስ የማዳን እና የሞቱ ሰዎችን አስከሬኖች የማውጣት ስራዎችን እያከናወኑ በነበሩበት ወቅት ሁለተኛ የመሬት መንሸራተት ተከስቷል።

እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) መረጃ ከሆነ በመሬት መንሸራተት አደጋው የሟቾች ቁጥር ወደ 257 ከፍ እንዳለ እና ቁፋሮው ሲጠናቀቅ ቁጥሩ እስከ 500 ሊደርስ ይችላል የሚል ግምትን አስቀምጧል። ከሟቾች በተጨማሪም በአደጋው ከ15,500 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ቢያንስ 1,320 ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት እና 5,293 ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ይገኙበታል።

ሀቅቼክ በቲክቶክ ላይ የተሰራጨውን ይህን ቪድዮ በቅርበት ሲመረመር መግለጫው እንደሚያትተው በኢትዮጵያ ፣ ጎፋ ዞን የተከሰተውን ሳይሆን በፈረንጆቹ 2022 በህንድ, ሜጋላያ ግዛት የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ የሚያሳይ ነው።

ቪዲዮ

CNN-News18 የተሰኘው የህንድ ሚድያ እንደዘገበው ከሆነ በሰሜን ምስራቅ ህንድ ሜግሃልያ ግዛት የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ተከስቶ ነበር። ይህ የዜና ተቋምም ይህን ክስተት የሚያሳይ ቪድዮ ብማህበራዊ ገፁ ላይ አጋርቶ ነበር።

ምንም እንኳን ቪዲዮው በተፈጠረው መሬት መንሽራተት አደጋ ክስተት ላይ መሰረት አድርጎ ቢሰራጭም ሀቅቼክ ይህ ቪድዮ በሀገራችን የተከሰተውን ሁኔታ ስለማያሳይ ሀሰት ብሎታል።

ይህ ቪዲዮ በትግራይ የተከሰተ ረሃብ ያሳያል?

ህዳር 18 2016 አንድ የፌስቡክ ገጽ በትግራይ የተራበ ጨቅላ ህጻን ነው በማለት ይህንን ቪድዮ አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ ቪዲዮው ወደ 8,000 የሚጠጋ እይታን ያገኘ ሲሆን ከ121 ጊዜ በላይም ተጋርቷል።

ከዚሁ ቪዲዮ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ልጥፍች በሌሎች የፌስቡክ ገጾች ላይም ተጋርተዋል። ተመሳሳይ ቪዲዮ በሌላ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወደ 5,000 የሚጠጋ እይታን ያገኘ ሲሆን ከ80 ጊዜ በላይም ተጋርቷል።

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከፍተኛ ድርቅ እና የረሃብ ቀውስ መከሰቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአበርገለ ወረዳ ብቻ ከ19,000 ሄክታር ሰብል 17,000 ሄክታር ሰብል ለድርቅ መጋለጡን የትግራይ ክልል ግዝያዊ መንግስት አስታውቋል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤድ) እና የተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ፕሮግራም (ዳብልዩ ኤፍ ፒ) በመንግስት ባለስልጣናት የእርዳታ ስርቆትን ክስ በመጥቀስ ዕርዳታውን አቁሟል።

በህዳር 3፣ 2016 ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ከስድስት ወራት እገዳ በኋላ በኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ ስርጭትን በታህሳስ ወር እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በ2016 ጥቅምት 20 የወጣው የኦቻ ዘገባ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአማራ እና በትግራይ ክልል በድርቅ መሰል ሁኔታዎች ተጎጂ ሆነዋል ብሏል።

በተጨማሪም የትግራይ ክልል አስተዳደር በወጀራትና አጽቢ ወረዳ ድርቅና ረሃብ መከሰቱን ገልጿል

ከሰሞኑ በትግራይ ክልላዊ መንግስት አበርገሌ ወረዳ ከፍተኛ ረሃብ እንዳለ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ አየተጋራ ቆይቷል።

በተጨማሪ እነዚህ ልጥፎች በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ሰዎች የገንዘብ ማሰባሰብያ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን ጀምረዋል።

በረሃብ የገንዘብ ማሰባሰብያ ዘመቻ መካከል አንድ የተራበ ጨቅላ ሕፃንን የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው ሲጋራ ነበር።

ነገር ግን ትክክለኛው ቪዲዮ ከሶስት ሳምንት በፊት ማለትም ህዳር 2፣ 2016 በቲክቶክ ላይ ተጋርቶ ተገኝቷል። 

የተጋራው ቪዲዮ በመጀመሪያ ካቶ ኒኮደም በተባለ የቲክ ቶክ አካውንት ላይ ተጋርቶ ተገኝቷል። ይህ የቲክ ቶክ አክውንት 1.8 ሚሊዮን ተከታዮች ሲኖሩት 34.5 ሚሊዮን የሚሆን ግብረመልስን አጊንቷል።

ይህ ኒኮደም የተባለ ግለሰብ በዩጋንዳ ወላጅ አልባ ህጻናትን የሚረዳ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሪ እንደሆነ ይገልጻል። ለዚህ ሃሰተኛ መረጃ ጥቅም ላይ የዋለውን ቪዲዮ ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ግለሰብ የቲክቶክ አካውንት ላይ እንክብካቤ እያገኙ ያሉ ሕፃናትን የሚያሳዩ ተመሳሳይ ቪዲዮዎችን በተደጋጋሚ ይጋራሉ።

ይህንኑ ህጻን ልጅ የሚያሳዩ ሌሎች ቪዲዮዎች እንዲሁ በዚሁ የቲክቶክ አካውንት ላይ ተጋርተዋል

ኒኮደም በ ጎፈንድሚ ላይ ባወጣው የገቢ ማሰባሰቢያ ልጥፍ ላይ “ሴቭ አፍሪካን ቻይልድ 254 ሚኒስትሪ (Save African Child 254 Ministry)” የተባለ በኡጋንዳ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚረዳ ድርጅት እና “ኪንደር ሂልፈዘንትረም (Kinderhilfezentrum)” የተባለ ሌላ ግበረ-ሰናይ ድርጅት መስራች እንደሆነ ገልጿል።

በተጨማሪም “ኒኮላስ ሰቡፉ” ትክክለኛ ስሙ እንደሆነ እና “ካቶ ኒቆዲም” ቅፅል ስሙ መሆኑን ገልጿል

በትግራይ ክልል ድርቅና የረሃብ ችግር መከሰቱን ዘገባዎች ቢያመለክቱም ይህ ቪዲዮ ግን በትግራይ የተራበ ሕፃንን የሚያሳይ አይደለም። 

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የፌስቡክ ፖስት ትክክል ያልሆነ ቪዲዮ በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ድምር ይበልጣል?

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአምስት አመት በፊት ከምስራቅ አፍሪካ በምጣኔ ሀብት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ  አሁን ከጎረቤቶቿ ሀገራት ኢኮኖሚ ድምር የላቀ ኢኮኖሚ አላት በማለት ተናግረዋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እአአ በመጋቢት 2018 ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ብልጽግናን እና ዲሞክራሲን ለማጎልበት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ቃል ገብተዋል። በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስትም ማሻሻያው ሀገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል ሲል ይገልጻል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በትክክለኛው የኢኮኖሚ አቅጣጫ ላይ እንደምትገኝ እና ኢኮኖሚዋም እያደገ መምጣቱን በተደጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን  በቅርቡ፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ባለፉት አምስት ዓመታት በእጥፍ ጨምሯል ያሉትም ከነዚህ መካከል የሚጠቀስ ነው።

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በቅርቡ ለክረምት ተማሪዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እያደገች መሆኗን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ጋር በማነፃፀር ለተማሪዎቹ አብራርተዋል፡፡

ጠ/ሚንስትሩ  እንደተናገሩት፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ልኬት ከአምስት ዓመታት በፊት ከኬንያ ቀጥሎ በምስራቅ አፍሪካ ሁለተኛው  ነበር። እ.ኤ.አ. በ2018 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 84.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር፤ እንዲሁም የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ እንደገለጸው፣ የሀገሪቷ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን  91.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ከአምስት ዓመታት በኋላ እአአ በ2022 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 126.8 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ፤ የኬንያ ደግሞ 119.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በዚህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከአምስት አመት በኋላ የኬንያን በልጦ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሆኗል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ድምር እንኳን ይበልጣል ወይም የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ኢኮኖሚ ተደምሮ ከኢትዮጵያ አንሷል በማለት ያስተላለፉት መረጃ ሀሰት ነው።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ስድስት ሀገራት ማለትም፡ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ እና እውቅና ባላገኘችው ሃገር ሶማሊላንድ ትዋሰናለች።

እንደ አለም ባንክ ዘገባ የሱዳን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እ.ኤ.አ. በ2022 51.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በዚህም መሰረት የኬንያ እና የሱዳንን የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ተደምረው ከኢትዮጵያ (171.2 ቢሊዮን እና 126.8 ቢሊየን ሲነጻጸር) ይበልጣሉ።

የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሌላንድ እና የሶማሊያ የቅርብ ጊዜ ኢኮኖሚ መረጃ በየራሳቸው ማዕከላዊ ባንኮች ወይም የስታስቲክስ ኤጀንሲዎች መረጃ ቋት ላይ አይገኝም። ስለዚህ እንደ አይኤምኤፍ ካሉ ሌሎች አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያወጡትን መረጃ አስደግፈን አቅርበናል።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እ.ኤ.አ. በ2022 የበርካታ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ)  አሃዞችን የዘገበ ሲሆን እነዚህም  አሃዞች እንደሚከተለው ናቸው፡- የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 120.37 ቢሊዮን ዶላር፣ የኬንያ 113.7 ቢሊዮን ዶላር፣ የሱዳን 33.75 ቢሊዮን ዶላር፣ የሶማሊያ 10.42 ቢሊዮን ዶላር፣ የደቡብ ሱዳን 8.54 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም የጅቡቲ 3.66 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።  ይህ የአይኤምኤፍ መረጃ ግን ስለ ኤርትራ እና ሶማሌላንድ ለተጠቀሰው አመት መረጃን እንደማያጠቃልል ልብ ሊባል ይገባል።

ስለዚህ በ2022 የአምስቱ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት (ኤርትራ እና ሶማሌላንድን ሳይጨምር) አጠቃላይ  ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 170 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን  120.37 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው።

ይህም ሲጠቃለል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያላት ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ድምር የበለጠ ነው ማለታቸው እ.ኤ.አ. በ2022 የኢኮኖሚ መረጃን መሰረት በማድረግ ሀሰት ሆኖ ተገኝቷል።

ሀሰት፡ ይህ ምስል በደመራ ዕለት ከወላጆቿ ተነጥቃ የታገተች ልጅን አያሳይም

ከደመራ በዓል ጋር ተያይዞ ይህች ህጻን አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ለብሳለች በሚል ከወላጆቿ ተነጥቃ በፌደራል ፖሊሶች ለ 10 ሰአታት ታግታለች በሚል የፅሁፍ መግለጫ አንድ የፌስቡክ አካውንት ይህንን ምስል አጋርቶት ነበር። ምስሉም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው መሰራጨት ችሎ ነበር። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ የቆየና እና ከዚህ በፊት የተጋራ መሆኑን አረጋግጧል። ምስሉም  በደመራ በዓል ላይ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ለብሳ በመገኘቷ ከወላጆቿ የተነጠቀች ልጅን አያሳይም፡፡ 

እንደ ጎርጎሮስያውያኑ አቆጣጠር በ1995 የወጣው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሶስት አግድም ሰንሰለቶች አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ ሲሆኑ በሰማያዊ መደብ ላይ ኮከብ ያረፈበት ነው።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተለይ በኮከብ አርማ አጠቃቀም  የግጭት፣ የአለመግባባትና የክርክር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ ሰዎች የቀይ፣ ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለም ባንዲራ ያለ የኮከብ አርማ ሲፈልጉ ሌሎች ደግሞ ይፋዊውን የኮከብ አርማ ይፈልጋሉ። የኮከብ አርማውን የማይፈልጉት ደግሞ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የተለያዩ ቡድኖች እና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይጻረራሉ ተብለው ይተቻሉ።

በደመራ በዓል አከባበር ላይ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ የኢፌድሪ  መንግስት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የቤተክርስትያኗን ምልክት ካላቸው ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሰንደቅ አላማ ውጪ ምንም አይነት እውቅና የሌለውን ባንዲራ እና ምልክት ለብሰው በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ እንዳይመጡ አስጠንቅቀዋል። .

በበዓሉ ላይ ሰዎች ከደመራ በዓል ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማይወክሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ወይም ምልክቶች ይዘው እንዳይመጡና መንግሥት ያወጣውን መመሪያ ማክበር እንዳለባቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።

ይህን ተከትሎ በደመራ በዓል ላይ አንድ ልጅ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ጥለት ያለው ቀሚስ ስለበሰች ከወላጆቿ ተነጥቃ በፌደራል ፖሊሶች ተወስዳለች በማለት በማህበራዊ ሚድያ ላይ ይህ ምስል ተጋርቷል።

ሀቅቼክ ይህን ፖስት መርምሮ ምስሉ የቅርብ ጊዜ እንዳልሆነ እና ተያይዞ የቀረበውን ሃሳብ የማይደግፍ መሆኑን አረጋግጧል።

በፖስቱ ላይ የሚታየው ምስል ከዚህ በፊት እ.አ.አ በጥር 2022 ትዊተር ላይ የተለጠፈ ሲሆን ምስሉ በመንግስት እና በህወሓት መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በኢትዮጵያ በነበሩ ሰላማዊ ሰልፎች ጊዜ ተጋርቶ የነበረ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ሀቅቼክ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ትክክለኛ ስላልሆነ ልጥፉ ሐሰት ብሎታል።

ሀቅቼክ ለተጨማሪ መረጃ ምስሉን ያጋራውን ግለሰብ ለማግኘት የሞከረ ሲሆን ነገር ግን ግለሰቡ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያዎችን ማረኩ ብለዋል?

ከ5ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ ኢታማጆር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋኖ ታጣቂዎች ታንኮችን ጨምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያዎች ማርከዋል ብለዋል  በሚል አንድን ቪድዮ አጋርቷል

ይህ ጽሁፍ እስከታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ​​​​ 1300 ግብረመልስን ስያገኝ  ከ90 ሺ በላይ ተጠቃሚዎች አይተውታል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪደዮው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያዎችን ማረኩ ማለታቸውን እንደማያሳይ አረጋግጧል። በዚህም የፌስቡክ ፖስቱ ሀሰት ተብሏል።

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚታወቁት ታጣቂዎች ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል።

የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሀላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት በ”አክራሪ” ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ባዘዘበት ወቅት የጸጥታው ቀውስ ተባብሷል።

በነሀሴ 2023 እ.አ.አ በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ የክልሉን ትላልቅ ከተሞች ለመቆጣጠር ችለው ነበር። ለዚህ ምላሽ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት ሁኔታውን መቀልበስ ችሏል። መንግስት ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ ብዙ ቦታዎችን መልሶ ቢቆጣጠርም፣ በክልሉ የነበሩት ግጭቶች ግን ተባብሰው ቀጥለዋል።

ሀቅቼክ የፋኖ ታጣቂዎች መሳሪያ እየማረኩ ነው የሚሉ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ዜናዎችንም ተመልክቷል። ሆኖም ከእነዚህ ልጥፎች መካከል አንዳንዶቹ በውሸት እና በአሮጌ ምስሎች የታጀቡ ነበሩ።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ አንድ  የፌስቡክ ገፅ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ታንክን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የጦር መሳሪያዎቻችንን ወስደውብናል” ሲሉ የሚሰሙበት አጭር ቪዲዮ በማጋራት፤ እነዚ በኢታማጆር ሹሙ የተጠቀሱ መሳሪያዎች በፋኖ የተፋረኩ እንደሆኑ አመላክቷል።ነገር ግን ሀቅቼክ የቪዲዮ ክሊፑ ይህንን እንደማያሳይ አረጋግጧል። ቪድዮው የተወሰደው እ.አ.አ በጥቅምት 2021 በዩቲዩብ ላይ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከታተመው ቪዲዮ ሲሆን፤ ይህም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ስለነበረው  ግጭት ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ተቆርጦ የተወሰደ ነው። በቪዲዮው ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የህወሓት ሃይሎች ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ታንኮችና ሌሎች መሳሪያዎችን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

ስለዚህ ሀቅቼክ  ይህ የፌስቡክ ፖስት የቆየና ትክክለኛ ያልሆነ ቪዲዮን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።

ቪዲዮው ክርስቲያን ታደለ ከእስር መፈታታቸውን ያረጋግጣል?

በነሃሴ 9 2023 እአአ ከ12 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የቲክቶክ ገፅ በእስር ላይ የነበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር መፈታታቸውን ያረጋግጣል በማለት  ይህንን  ቪድዮ አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ ቪድዮው 3439 ጊዜ ያህል ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪድዮው አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር መፈታታቸውን  እንደማያሳይ አረጋግጧል። በዚህም የቲክቶክ ፖስቱ ሀሰት ብሎታል።

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል

የፌደራል መንግስት የክልሉ ልዩ ሀይል አባላትን ለመበተን በወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል ሰፊ ተቃውሞ አጋጥሞታል።

ይህ ውሳኔ  ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀሰቅስና ክልሉ ውስጥ ትጥቅ ግጭት እንዲስፋፋ አድርጓል። በዚህም የፋኖ ታጣቂዎች ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ብዙ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችለው ነበር። ይህንን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት  በጠየቀው እርዳታ መሰረት በሀገሪቱ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት መንግስት ፖለቲከኞችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን አስሯል። የቀድሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት አቶ ክርስቲያን ታደለ በአዋሽ አርባ እስረኛ ማቆያ ካምፕ እንደሚገኙ አረግጧል

በዚህ መነሻነት አቶ ክርስቲያን ታደለ በቅርቡ ከእስር እንደተለቀቁ የሚገልጽ የቲክቶክ ቪዲዮ ተሰራጭቷል።

ይሁን እንጂ ቪድዮው ከዚህ በፊት በመጋቢት 9 ቀን 2020 እአአ በአስራት ሚዲያ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ታትሞ ከነበረው ቪድዮ ላይ ተቆርጦ የተወሰደ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። ቪዲዮው አቶ ክርስቲያን ታደለ በግዜው አዲስ አበባ በተዘጋጀ የሕዝብ ውይይት ላይ ንግግር ሲያደርጉ የሚያሳይ ነው።

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የቲክቶክ ልጥፍ ትክክል ያልሆነና የቆየ ቪድዮ በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

ምስሉ የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያን ሄሊኮፕተር መትተው እንደጣሉ ያሳያል?

አንድ የፌስቡክ ገፅ  ይህንን (ከታች ያለው) ምስል  የመከላከያ ጦር ሄሊኮፕተር በፋኖ ታጣቂዎች ተመቶ መውደቁን  ያሳያል በማለት አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ከ21 ጊዜ በላይ በመጋራት የብዙዎችን እይታ አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ምስሉ ፋኖ  የመከላከያን ሄሊኮፕተር መቶ እንደጣለ እንደማያሳይ በማረጋገጥ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።  

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት  የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚጠራውን የታጠቀ ቡድን  ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው ። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና  በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል።

እ.ኤ.አ. ነሀሴ 11 ቀን 2023 የወጡ ዘገባዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎች እንዳመላከቱት በዚህ ግጭት ሳቢያ በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል።

ምንም እንኳን መንግስት የአማራ ክልል ትላልቅ ከተሞችን መልሶ ቢቆጣጠርም አሁንም በኢትዮጵያ ሰራዊት እና በፋኖ ሚሊሻ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት ቀጥሏል።

ይህ በፌስቡክ የተጋራው ምስል በአማራ ክልል  የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያን ሄሊኮፕተር መትተው እንደጣሉ ለማሳየት የቀረበ ነው። ይህ መረጃ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሀቅቼክ የጉግል ተገላቢጦሽ ምስል መፈለጊያን በመጠቀም ምስሉን መርምሯል። በዚህም ምስሉ ከዚህ በፊት በአንድ ድህረገጽ ላይ እ.አ.አ በመጋቢት 3 ቀን 2023 የታተመ መሆኑን አረጋግጧል።

በምስሉ ላይ የሚታየው አንድ የሮማንያ የጦር ሄሊኮፕተር ሲሆን በጥቁር ባህር ላይ የጠፋው የሮማንያ ተዋጊ ጄትን ለመፈልግ እየበረረ ባጋጠመው ችግር የተከሰከሰ ነው።

ስለዚህ ሀቅቼክ  ይህ የፌስቡክ ፖስት የቆየና ትክክለኛ ያልሆነ ምስልን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።

ቪድዮው የፋኖ ታጣቂዎች በደብረማርቆስ መትተው የጣሉት የመከላከያን ሄሊኮፕተር አያሳይም

በነሀሴ  2023  ከ40 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ  አንድን ምስል የመከላከያ ጦር ሄሊኮፕተር በደብረ ማርቆስ  በፋኖ ታጣቂዎች  ተመቶ መውደቁን  ያሳያል በማለት  አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከሚታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ​​​​ 7000 እይታ በማግኘት ከ300 በላይ ግብረመልሶችን አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ቪድዮው ፋኖ በደብረ ማርቆስ የመከላከያን ሄሊኮፕተር መትቶ እንደጣለ እንደማያሳይ በማረጋገጥ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት  የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚጠራውን የታጠቀ ቡድን  ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው ። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና  በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል። ግጭቱ የተባባሰው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ ከተገደሉ በኋላ መንግስት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ‘ጽንፈኛ’ ያላቸው ታጣቂዎች እንዲዋጋ ባዘዘ ጊዜ ነው። አሁንም በአንዳንድ አከባቢዎች ግጭቱ እንደቀጠለ ነው።

እ.አ.አ. በነሀሴ 2023  የፋኖ ታጣቂዎች  አንዳንድ  ከተሞችን ተቆጣጥረው ነበር። መንግስትም ከተሞቹን መልሶ ለመቆጣጠር  መከላከያ ሰራዊት አሰማርቷል። በዚህም እነዚህ ትላልቅ ከተሞች መመለስ ችለዋል፣ ነገር ግን ግጭቱ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች እየተካሄደ ነው።

ይህ በፌስቡክ የተጋራው ምስል በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በደብረ ማርቆስ የመከላከያን ሄሊኮፕተር  መትተው እንደጣሉ ያሳያል ከሚል መረጃ ጋር ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ምስሉ ከዚህ በፊት ፌስቡክ ላይ በሚያዝያ 21 ቀን 2023 ታትሞ ከነበረው ቪድዮ የተወሰደ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። ቪድዮው እና ምስሉ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ሲበር በሞተር ብልሽት ምክንያት የተከሰከሰ የሚድሮክ ኢትዮጵያ (ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ) የሆነውን ሄሊኮፕተር ያሳያል።

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የፌስቡክ ፖስት ትክክል ያልሆነና የቆየ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

Exit mobile version