የተጣሩ መረጃዎች

በምስሉ ላይ የሚታዩት ወታደሮች በቅርቡ በአፋር እና በሶማሌ መካከል በተከሰተው ግጭት የተሳተፉ ናቸው?

በ19 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Afmeer tv. የተባለ 224,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ አንድ ባለ አንድ ጋቢና ወታደራዊ ተሽከርካሪ እና ወታደሮችን የሚያሳይ ምስል፤ የሶማሌ ልዩ ኃይል እና የአፋር ክልል ኃይሎች በሲቲ ዙሪያ (ቀድሞ ሺኒሌ ዞን በመባል የሚታወቀው) ድንበር ላይ ከፍተኛ ፍልሚያ እያካሄዱ እንደሆኑ እና በግጭቱም በአፋር ክልል ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰና ሶስት ንፁሀን ሶማሌዎች ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል ከሚል ፅሁፍ ጋር አጋርቷል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከዚህ በታች ያሉው የፀትታ ሀይሎችን የሚያሳየው ምስል ከግጭቱ ጋር እንደማይገናኝና በቅርቡ በሶማሌ እና በአፋር ክልል ኃይሎች መካከል የተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጧል። በመሆኑም መረጃውን ሃሰት ብሎታል። .

በኢትዮጵያ የሚገኙት የአፋር ብሄረሰብ አባላትና የኢሳ ሶማሌ ብሄረሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ግጭት ውስጥ ከገቡ ከ10 አመታት በላይ ተቆጥሯል። በድንበር አከባቢዎች በተለይም ከሶማሌ ክልል ዘጠኝ ዞኖች አንዱ በሆነው በሽንሌ ዞን እና በአፋር ክልል ገቢ ራሱ እና አውሲራሱ ዞኖች መካከል የእርስ በርስ ግጭቶች እንደነበረም የሚታወቅ ነው። አክራካሪዎቹ ግዛቶች ኡንዱፎ ፣ ገዳማይቱ እና አዳይቱ ከተሞች በሁለቱ የአፋር ዞኖች ውስጥ ይገኛሉ። በርካታ የኢሳ ሶማሌዎች በአፋር ክልል በገቢ ራሱ እና በአውሲረሱ ዞኖች በሚገኙ ከተሞች ውስጥ በመስፈራቸው ምክንያት የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች እና ግጭቶች በየጊዜው ይነሳሉ። በ2006 ዓ.ም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አነሳሽነት የሶማሌ እና የአፋር ክልላዊ መንግስታት በመካከላቸው ላለው የድንበር ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ይሆን ዘንድ የሰላም ስምምነት ተስማምተው የተፈራረሙ የነበረ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት ሶስቱ አወዛጋቢ ግዛቶች ወደ አፋር ክልል ማለትም ገዳማይቱ ወደ አሚባራ ወረዳ ፣ ኡንዱፎ ወደ ገዋኔ ወረዳ እና አዳይቱ ወደ ሚሌ ወረዳ እንዲዋሀዱ ተደርጎ ነበር። ሆኖም በ2011 ዓ.ም የሶማሌ ክልል ሶስት ቀበሌዎችን ለአፋር ክልል ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና  በአከባቢው ህዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ እና ህገ-መንግስታዊ ያልሆነ ውሳኔ ነው በማለት ከስምምነቱ ውጪ እንደሆነ ማስታወቁም የሚታወስ ሲሆን ከሁለት ወራት በፊት በሁለቱ የክልል ሃይሎች መካከል አዲስ የትጥቅ ግጭት ተከስቶ የ27 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ በፌስቡክ ጽሁፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረ ግጭት አይደለም፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው 26 ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ፌስቡክ ላይ ተለቆ ሲሆን ግጭቶች በክልሉ ኃይሎች መካከል ሲካሄዱ እንደነበር ይገልፃል።

Original Image:

በአፋር እና በሶማሌ ክልል ድንበር ዙሪያ ለአስርተ ዓመታት የዘለቁ ግጭቶች መኖሩ እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ምስሉ በሶማሌ እና በአፋር ክልል ኃይሎች መካከል ከተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ጋር የማይገናኝ እና በአሁን ሰአት በክልሎቹ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የማያሳይ ስለሆነ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

በምስሉ ላይ የሚታዩት መሳሪያዎች በድባቴ ወረዳ አስተዳደሪ ቤት የተገኙ ናቸው?

ታህሳስ 13 2013 ዓ.ም 🌡#𝐒𝐓𝐎𝐏_𝐀𝐌𝐇𝐀𝐑𝐀_𝐆𝐄𝐍𝐎𝐂𝐈𝐃𝐄 በተባለ ከ3500 በላይ ተከታዮች ባሉት የትዊተር ገፅ አንድ የሰው ምስል እና ሁለት የተለያዩ ባህላዊ መሳሪያዎችን የሚያሳይ ምስል ተለቆ ነበር። ከምስሉ ጋር ተያይዞም መሳሪያዎቹ የተገኙት በዲባቴ ወረዳ  (በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን)  አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ ሲሆን በአካባቢው ያሉ አማራዎችን ለማጥቃት በሚል በቤታቸው ውስጥ መከማቸቱን የሚገልፅ ሀሳብ ያለው ፅሁፍ አለ፡፡ ፅሁፉም “ደበሊ በልጋፎ ይባላል፤ የቤጉ ድባጤ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ ብዙዎችን በማስጨፍጨፉ ወደ መተከል ዞን ሹመት አግኝቶ የመጣ ባለስልጣን ነው፤ ቤቱ ሲፈተሽ ይህ ሁሉ አማራን ማስጨፍጨፊያ ተገኝቷል” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት በምስሉ ላይ የሚታዩት የስለት መሳሪያዎች በድባቴ ወረዳ አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ የተገኙ አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። ስለዚህም የሀሰት መረጃ በማለት ፈርጆታል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በመተከል ዞን ግጭቶች እና መፈናቀሎች ተከስተዋል ፡፡ በዞኑ እና በአከባቢው ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተባባሱ በመሆናቸው የቤኒሻንጉል እና የአማራ ክልል መንግስታት እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ ታህሳስ 13 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ፒኤችዲ) ፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ፣ የጦሩ ዋና አዛዥ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አሻድሊ ሀሰን አካባቢውን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከመተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል ፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው በታህሳስ 14 2013 ዓ.ም በቡለን ወረዳ በቢኩጂ ቀበሌ ላይ ከባድ ብሄርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ ተከስቷል እንዲሁም ቤቶች ተቃጥለዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት መተከል ዞን በተፈጠረው የጎሳ ግጭት እና የፀጥታ ችግር መካከል በምስሉ ላይ የሚታዩት መሳሪያዎች በአማራዎች ላይ ጭፍጨፋ ለማድረግ በዲባቴ ወረዳ አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ ተከማችተው ተገኝተዋል ብማለት በትዊተር ላይ ተሰራጭቷል። ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ በተባለ የምስል ማጣሪያ ለማጣራት እንደተቻለው የተለያዩ ስለታም መሳሪያዎችን የሚያሳየው አንደኛው ምስል ለመጀመሪያው ጊዜ የተለቀቀው መስከረም 10 2012 ዓ.ም  በኢትዮጰያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የፌስቡክ ገፅ ላይ ሲሆን በቁጥር 2,765 የሚሆኑት መሳሪያዎች ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በአይሱዙ ሲጓዙ በደብረ ብርሃን ከተማ መያዛቸውም ተያይዞ ተገልፁአል። ሁለተኛው ምስል ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር 17 2013 ዓ.ም  ደብረማርቆስ ዴንማርክ በተባለ የፌስቡክ ገፅ ላይ መሳሪያዎቹ በቻግኒ በጅምላ ግድያ ከተሳተፉ መካከል አንዱ በሆነ አንድ ሀብታም ሰው ቤት ውስጥ ተገኝቷል በማለት ነበር የተለቀቀው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን የፀጥታ ችግር እና የእርስ በእርስ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት በትዊተር ገፁ የተሰራጨውን መረጃ ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋሉት ምስሎች አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ ባለመሆናቸው ምክንያት ሀሰት በማለት ፈርጆታል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

በመጪው ምርጫ ኦፌኮ አይሳተፍምን?

አዲስ ስታንዳርድ በፌስቡክ ላይ ከ151,000 በላይ ተከታዮች ያሉት በትዊተር ላይ ደግሞ ከ180,000 በላይ ተከታዮች ያሉት በኢትዮጵያ የሚገኝ የዜና አውታር ነው። አዲስ ስታንዳርድ በድህረ-ገፁ ላይ በእንግሊዘኛ በተፃፈ ርዕስ “ዜና: የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቃዋሚ ፓርቲ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በመጪው ምርጫ ላይ እንደማይሳተፍ ገልጿል” የሚል ርእስ ያለው የትዊተር ፅሁፍ ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡ ይህንኑ ፅሁፍ በፌስቡክ እና በትዊተር ገፆቹም በማጋራት ላይ ይገኛል ፡፡ ድህረ-ገጹ ፓርቲው በኦሮምኛ እና በአማርኛ የላከውን መግለጫ እንደ ማስረጃነት በመጠቀም ከላይ የተጠቀሰውን መረጃ ከላይ በተቀመጠው ርዕስ ስር አቅርቧል፡፡ ሆኖም ሀቅቼክ በዜና አውታሩ የቀረበውን ፅሁፍ እና ማስረጃ በመመርመር አሳሳች ርዕስ እንዳለው አረጋግጧል፡፡

በኢትዮጵያ በመጪው ምርጫ ይሳተፋሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ጠንካራ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አንደኛው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል እንደፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና (PHD) ፣ እንደምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እና እንደጃዋር መሃመድ የመሳሰሉ ግለሰቦችን ያካተተ ፓርቲም ነው። በአሁኑ ጊዜ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት በሽብርተኝነት ፣ በዓመፅ ቅስቀሳ ፣ በቴሌኮም ማጭበርበር እና በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ክስ ተከሰው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸው ይታወቃል፡ ፡አቶ ጃዋር መሀመድ በአራቱም ወንጀሎች ተጠርጥረው የተከሰሱ ሲሆን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በአንፃሩ ከቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ውጪ በሁሉም ክሶች በጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደቀረበባቸው የሚታወቅ ነው። በቅርቡም አቶ በቀለ ገርባ እና ጃዋር መሀመድ የሀገሪቱን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን ምክንያት በማድረግ ያለፈውን የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ለመቅረብ ፈቃደኛ ያመሆናቸውን ገልፀው በጊዜያዊ ማቆያቸው አቅራቢያ በሚገኝ ጊዜያዊ ችሎት መቅረብ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ኦፌኮ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አብዛኛዎቹ አመራሮቻቸው እና አባላቶቻቸው የታሰሩ በመሆናቸውና ከዋና መስሪያ ቤቱ ውጭ ያሉ ቢሮዎቻቸው በመዘጋታቸው በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ “እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል” የሚል መግለጫ አውጥቷል ፡፡ .

ምስል 1-ከኦፌኮ የተሰጠ መግለጫ በአማርኛ

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ሶስት ነገሮችን እንዲሟሉለት መጠየቁ ሀቅ ነው። (እነዚህም በእስር ላይ ያሉ የኦፌኮ አመራሮች እና አባላት እንዲለቀቁ ፣ የተዘጉ የኦፌኮ ቢሮዎች ተመልሰው እንዲከፈቱ እና ለምርጫ ቅስቀሳ እና ሌሎች የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ አመቺ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋዋል)። አዲስ ስታንዳርድም ከላይ የተጠቀሰውን የኦፌኮ መግለጫ በጽሁፉ አካል ውስጥ በሚገባ ገልፆታል፡፡ አዲስ ስታንዳርድ ባወጣው ፅሁፍ መልእክቱን እንደ አርዕስተ ዜና የተጠቀመው ቢሆንም ከላይ በተጠቀሰው ደብዳቤም ሆነ የኦሮምኛ አቻው ፓርቲው አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታዎች ውስጥ በምርጫ ላይሳተፍ እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች ቢያቀርብም ፓርቲው በመጪው ምርጫ በእርግጠኛነት አንካፈልም የሚል መልእክት እንዳልያዘ መገንዘብ ይቻላል። ምንም እንኳን የፅሁፉ ዋና አካል አርዕስቱን በትክክል እንዳብራራ መከራከር ቢቻልም ፣በኮሎምብያ ዩንቨርስቲ በተደረገ ጥናት 60 ፐርሰንት የሚሆኑት የትዊተር ተጠቃሚዎች የትዊተር መልእክቶችን የሚያጋሩት አርዕስቱን  ሳያነቡ እንደሆነ ያሳያል። ይህም እንደነዚህ ያሉ ርዕሶች ህዝብን ለማሳሳት ያላቸውን አቅም የሚያሳይ ነው። 

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ የፅሁፉን አርዕስት በጥልቀት ከመረመረ በኋላ (ዋና የፅሁፉን አካል ሳያጠቃልል) አሳሳች ርዕስ በማለት መረጃውን ፈርጆታል። ለዚህ ውሳኔ ምክንያቱ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተጻፈው አርዕስት ላይ የተጠቀሰውን መልእክት  ፓርቲው በመግለጫው ላይ ባለማስተላለፉ ነው።

አጣሪ: አብዱላሂ አብዱልቃድር

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።

በምስሉ ላይ ያሉት ወታደሮች ኢትዮ- ሱዳን ድንበርን የተቆጣጠሩ የሱዳን ወታደሮች ናቸው?

ኩዒታ – Kuéta የተባለ ከ2100 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ ታህሳስ 10፣ 2013 ዓ.ም ወታደሮችን የሚያሳይ ምስል  2000 ኪ.ሜ የሚሆነው አከራካሪ ድንበር ሙሉ በሙሉ በሱዳን ቁጥጥር ስር መሆኑን እና ቅንጣት ያክል መሬቱን እንደማይስጡ የሚገልፅ ፅሑፍ አክሎ ለጥፏል። ከምስሉ ላይም የተፃፈው ፅሁፍ “… የሱዳን መንግስት ተጨማሪ ብዙ ሺ ማጠናከሪያ ሰራዊት ወደ ድንበር ማጓጓዙ ታውቁዋል፡፡ የግብጽ መንግስትም የሱዳን ሉአላዊነትን ከማስከበር አንጻር የትኛውንም አይነት ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባት ከሱዳን ጎን መሰለፉን አስታውቋል…” ሲል ይነበባል።   ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከስር በምስሉ ላይ የሚታዩት የሱዳን ወታደሮች በቅርቡ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ግጭት ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ አለመሆኑን አረጋግጧል፤ ስለዚህ ሀሰተኛ ምስል መሆኑን አረጋግጧል።  

 

ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር በአማራ ሚሊሻ እና በሱዳን ወታደሮች መካከል ግጭት መከሰቱ የሚታወቅ ነው ሲሆን በ8  ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን እና የሱዳንን አዋሳኝ ድንበር ግዛቶች መቆጣጠሩን  ገልጿል። ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያሉት ዓለም አቀፍ ድንበሮች ግልፅና የማያከራክሩ እንደሆኑና ሱዳን ከክልሏ ቅንጣት እንደማትሰጥ በወቅቱ መግለፁም ይታወቃል ፡፡ የሰራዊቱ መግለጫ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ዓለም አቀፍ ድንበር ግልፅ እና አጠራጣሪ አለመሆኑን የበለጠ ሲያብራራ ሱዳን ሉዓላዊ ግዛቷ በሌላ ሀገር እንዲተዳደር አትፈቅድም ብሏል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ፒ.ኤች.ዲ) በ8  ታህሳስ 2013 ዓ.ም በትዊተር ገፃቸው አስተዳደራቸው ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር የተፈጠረውን የድንበር ግጭት በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉት ግጭቶች የሁለቱን አገራት ትስስር አያፈርሱም በማለት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ፍጥጫ አቃለውታል። ታህሳስ 13፣ 2013 ዓ.ም ሀገሪቱን የሚያዋስኑ ድንበሮችን ለመለየት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን ባለሥልጣናት ጋር በካርቱም ተነጋግረዋል።

በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው መረጃ ቢሰራጭም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ ዘዴ እንደሚያመለክተው በመረጃው ላይ የተጠቀመጠው ምስል የተነሳው የቻይናው ዥንዋ ጋዜጣ ጋዜጠኛ በሆነው መሀመድ ባቢከር ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጋቢት 4 2009 ዓ.ም (በፌስቡክ ተጠቃሚው ከመለቀቁ 3 አመት ከ9 ወር እና 6 ቀን በፊት) አላሚ በተባለው የእንግሊዝ ፎቶግራፊ ኤጀንሲ ነበር። ምስሉ 11,450 የሚሆኑ የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰራዊት በካርቱም በተመረቁበት ወቅት በተካሄደ ሰልፍ የተነሳ መሆኑንም ሀቅቼክ አረጋግጧል። 

Original Image:

በመሆኑም ምንም እንኳን መረጃው በፌስቡክ በተጋራበት ወቅት የሱዳን ጦር የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አከባቢ ያለውን ቦታ መቆጣጠሩ እውነት ቢሆንም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መረጃውን ለመደገፍ ተያይዞ የተለቀቀው ምስል ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ይህ ምስል በምዕራብ ጎንደር የተከሰተ የተሽከርካሪዎች ግጭትን የሚያሳይ ነው? 

ታህሳስ 4 ቀን 2013 Mooyiiboon Dhuufeera የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ (432 ጓደኛዎች ያሉት አንድ የፌስቡክ  አካውንት)   ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ንምስረታ ሃገረ ትግራይ (31.2 ሺ አባላት ያሉት የፌስቡክ ቡድን) ተብሎ በሚጠራ የፌስቡክ ግሩፕ ላይ አራት የተለያዩ ምስልዎችን የያዘ የፌስቡክ ጽሁፍ ያጋራ ሲሆን የፌስቡክ ተጠቃሚው ግለሰብ በፌስቡክ  መልዕክቱ የቀረቡት ምስሎች ላይ የሚታዩት የተጋጩ ተሽከርካሪዎች በ4 ታህሳስ 2013 ቀን በምዕራብ ጎንደር በዳንሻ ወረዳ ዘመቲን ቀበሌ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ ወድመዋል ከሚል መረጃ ጋር አያይዞ አቅርቧል፡፡ 

የፌስቡክ ፅሁፉ አደጋው የ 38 ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ ጠቅሶ የፌስቡክ ግሩፑ አባላት ለጓደኞቻቸው እንዲያጋሩት ይማጸናል። በተጨማሪም የፌስቡክ ጓደኞቹን ከጽሁፉ ጋር ተያይዞ የቀረበውን መስፈንጠርያ በመጠቀም የሟቾችን ማንነት በቴሌግራም ቻናል እንዲመለከቱ ጥሪ  አቅርቧል፡፡ ሆኖም በቴሌግራም ቻናሉ ላይ የሟቾች አስከሬን ፎቶ እንደተጠቀሰው አይገኝም፡፡ ሀቅ ቼክ ከዚህ በታች ያሉት ምስሎች ሰሞኑን በምዕራብ ጎንደር የተከሰተ የትራፊክ አደጋን እንደማያሳዩ አረጋግጧል ፣ በመሆኑም መረጃውን ሀሰት በማለት ፈርጆታል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የመኪና አደጋዎች ከሚከሰቱባቸው አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ እርግጥ ነው። ባለፈው በጀት ዓመት በመላው አገሪቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት 4,133 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልልም ከፍተኛ መጠን ያለው የመኪና አደጋዎች እንደሚከሰቱ የሚታወቅ ነው፡፡ አዲስ ዘይቤ በቅርቡ እንዳስነበበው ከሆነ በታህሳስ ወር የመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በባህር ዳር ከተማ ብቻ  59 የትራፊክ አደጋዎች ተከስተዋል። የትራፊክ አደጋዎቹ  የ40 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን 25 ሰዎችን ለከባድ የአካል ጉዳት ዳርጓል። በተጨማሪም 19 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ዘይቤ በላከው መግለጫ መግለፁ የሚታወስ ነው። ስለዚህ መረጃው በአማራ ክልልና በአጠቃላይ በሀገሪቱ የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ችግር መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ምስል 1: 

 ምስል 1: ትክክለኛ ምስል


በፌስቡክ ገጹ ላይ የተለጠፈው ምስል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች በተሰኘ የምስል መፈተሻ መንገድ ሲፈተሽ የመኪናው አደጋ በምዕራብ ጎንደር እንዳልተከሰተ አመልክቷል። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌስቡክ ላይ የተለጠፈው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ነበረ። ምስሉ ነሐሴ 2012 በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም በደጀና ወረዳ ዘመቲን ቀበሌ ላይ የተከሰተ የትራፊክ አደጋ ምስል ነው።  በአደጋው የጭነት መኪና እና አውቶቡስ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው 39 ሰዎች ሲሞቱ 11 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም 26 ሰዎች ለቀላል ጉዳት ተዳርገዋል። በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚገኘውን ልጥፍ በሚከተለው መስፈንጠርያ በመጠቀም ማግኘት ይችላል። 

በዚህም መሰረት ሀቅቼክ መረጃውን በተመለከተ ባደረገው ማጣርያ በምስሉ ላይ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ በምዕራብ ጎንደር ታህሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም  የተከሰተ የትራፊክ አደጋ እንዳልሆነ በማረጋገጥ መረጃውን ሀሰት በማለት ፈርጆታል። 

አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ

 

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

 

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

 

ምስሉ በአዳማ ከተደረገ የኩላሊት ስርቆት ጋር የተገናኘ ነው?

ጋጋ ቆሌ ኢጋ በተባለ ከ2900 በላይ ጓደኞች ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ በአዳማ ከተማ ህፃናት እየጠፉ መሆኑን እና የኩላሊት ስርቆት አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አጋርቶ ነበር። መረጃው ከ25,000 ጊዜ በላይ ሼር ተደርጓል። ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት የተለቀቀው ምስል ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት ነው በማለት በይኗል።

 

የሰውነት ክፍል ንቅለ ተከላ (ኦርጋን ትራንስፕላንት) ከአንድ ለጋሽ አካል ላይ የተወሰደን የሰውነት ክፍል በበሽታ የደከመ ሌላ ሰው ላይ የመትክል ቀዶ ህክምና ሂደት ነው። ንቅለ ተከላው በአብዛኛው የሚካሄደው ለጋሹ ከሞተ በኋላ ቢሆንም የኩላሊት እና የጉበት ንቅለ ተከላ ግን ለጋሹ በህይወት እያለ ሊደረግ ይቻላል። ኩላሊት ከለጋሹ ሰውነት ላይ ከተለያየ በኋላ ከ36 – 48 ሰዐታት ድረስ መቆየት እንደሚችል የሚታወቅ ነው። የሰውነት ክፍል ልገሳ እጥረት መኖሩ፤ ህገወጥ የሰውነት ክፍል ሽያጭየሰውነት ክፍል ስርቆትየሰውነት ክፍልን በግዴታ የመውሰድ ወንጀሎች እንዲስፋፉ አድርጓል። የሰውነት ክፍል ሽያጭ ከኢራን በስተቀር በሁሉም ሀገራት የተከለከለ ሲሆን ቻይና ደግሞ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እስረኞችን የሰውነት ክፍል ያለ ፍቃዳቸው በመውሰድ  ትታወቃለች። በአለም ላይ ብዙ የሰውነት ክፍል ስርቆት እንዳለ ይነገራል።

 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተካሄደው መስከረም 11፣ 2008 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የጤና ኮሌጅ ከሚችገን ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባባር ነበር። እስከ ሚያዚያ 24፣ 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ለ102 ህሙማን ብቻ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ተችሏል። ይህም የሆነበት ምክንያት በአግባቡ የሰለጠኑ የቀዶ ህክምና ሃኪሞች እጥረት እንዲሁም ንቅለ ተከላውን ለማድረግ የሚያገለግል መሳሪያ እጥረት በመኖሩ ነው።

 

ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እነደሚያመለክተው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በ18 ነሐሴ 2009 ዓ.ም (ፌስቡክ ላይ ከመለቀቁ 17 ወራት በፊት) ነበር። ምስሉ የተነሳው በጣሊያን ሮም ውስጥ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች ከመኖሪያቸው ፒያሳ ኢንዲፔንዴዛ ከተባረሩ በኋላ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነበር።

የተለያዩ የሰውነት ክፍል ስርቆቶች መኖራቸው እውነት ቢሆነም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት ምስሉ በአዳማ ያልተነሳ መሆኑን እና ህፃናት ለሰውነት ክፍል ስርቆት እየታገቱ ነው ከሚለው መረጃ ጋር ምንም ግንኙነት እና ማስረጃ የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። በዚህ መሰረት ሀቅቼክ መረጃው ሀሰት ነው በማለት በይኗል።

 

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

 

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

 

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

 

በምስሉ ላይ የሚታየው ግለሰብ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ሞቶ ተገኝቷል?

ታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም አነ ንባእላ ትግራይ (15,849 ተከታዮች ያሉት አካውንት) በተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ አንድ የፌስቡክ መልእክት በተለቀቀ መልዕክት ከዚህ በታች በገለባ ላይ ተኝቶ የሚያታየውን ሰው ምስል (ፅሁፉ ግለሰቡ ሴት ናት ይላል) በትግራይ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በረሃብ ምክንያት ሞቶ የተገኘ ሰው ምስል ነው ሲል ገልጿል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “በትግራይ ከጥይት ያመለጡ ሰዎች  በረሃብ ምክንያት እየሞቱ እንደሆነና “በአለም ውስጥ ያሉ የትግራይ ተወላጆች እና የትግሬ-ወዳጆች እንዲያዩት እባክዎን ያጋሩ” የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እንዲሁም “ንብረት ተዘርፏል ፣ ኤሌክትሪክ ሀይልም የለም ፣ ባንኮች በመዘጋታቸው ምክንያት ገንዘብ የለም” በማለት የፌስቡክ ተጠቃሚው ምስሉን በዓለም ዙሪያ እንዲያካፍሉ ይለምናል። ሆኖም ሀቅቼክ ከዚህ በታች ያለው ምስል ትግራይ ውስጥ ያሉትን እውነታዎች እንደማያሳይ አረጋግጧል። ስለዚህ የፌስቡክ ተጠቃሚው ምስሉን በሐሰት ያቀረበውን መረጃ ለመደገፍ በመጠቀሙ ብይኑ ሐሰት ሆኗል ፡፡

 

ከ25 ጥቅምት 2013 ጀምሮ በፌዴራል መንግስት በሚመሩ ሃይሎች እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ አለመረጋጋት መከሰቱ እርግጥ ነው። በክልሉ የተከሰተው ግጭት እና ሌሎች (እንደ የበረሃ አንበጣ ወረራ እና COVID19 ያሉ) ችግሮች በትግራይ ክልል እየተባባሰ ለሚገኘው የሰብዓዊ መብት ቀውስ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ግጭቱ የህውሀት ሀይሎች በሰሜን እዝ ላይ ያደረሱትን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የትራንስፖርት፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎት በክልሉ ተዘግተው የቆዩ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ የትግራይን ዋና ዋና ከተማዎችን  ከተቆጣጠሩ በኋላ በክልሉ የግንኙነት መስመርና የሰብዓዊ እርዳታ መስመርን ለመመለስ እየሰራ ይገኛል። እንደ UNHCR UNOCHA እና ICRC  ያሉ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በክልሉ የምግብ ፣ የመድኃኒትና የሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት እንዳለ እንደገለፁ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡ የፌዴራል መንግሥት ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል በሺዎች የሚቆጠር ኩንታል የምግብ ምርቶችን  ወደ መቀሌ እና ሽሬ ከተማዎች ልኳል ፡፡ 

ምስል 1: የተቀየረ ምስል (“ኣህህህ እናት!” ከሀዘን ስሜት ገላጭ ምስል ጋር)

 

ምስል 2: ዋናው ምስል 

 

ሆኖም በፌስቡክ አካውንቱ የወጣው ምስል ሪቨርስ ኢሜጅ በተሰኘው የምስል ፍለጋ ዘዴ በሚመረመርበት ወቅት በጭድ ላይ ተኝቶ የሚታየው ግለሰብ ከትግራይ አለመሆኑን ያመላክታል። በአንፃሩ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካው የማህበራዊ ሚድያ ድህረገፅ ሬዲት (Reddit) ላይ በ16 ህዳር 2013 ዓ.ም በኔፓል ቋንቋ በተጻፈ ጽሑፍ ጋር የቀረበ ምስል እንደነበረ ማየት ይቻላል። የሬዲት ተጠቃሚው ምስሉን ከተተረጎመው ጽሑፍ “በኬፒ ኦሊ ( የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር) ቋንቋ በአገሪቱ ውስጥ ብልጽግናን ማየት የሚፈራ ብሄራዊ ያልሆነ አካል ነው” ከሚለው መልዕክት ጋር አጣምሮ  ያቀረበ ሲሆን ጽሁፉን የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማግኘት ይቻላል፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲኔካላ (cinekala.com) የተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ድህረገፁ ላይ ግለሰቡ የ77 ዓመት ዕድሜ ያለው የራይ (የኔፓል የብሔረሰብ ቋንቋ ቡድን) ብሄር አባል እንደሆነ እና ለ10 ዓመታት እንደታመመ በመግለጽ እራፊ የጨርቅም ሆነ አልጋ ስላልነበረው በገለባ ላይ ተኝቶ እንደተገኘ አስነብቧል። ታሪኩን የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡

ሀቅቼክ ጽሁፉን ከመረመረ በኋላ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ጊዜ የተነሳ ምስል አለመሆኑን አረጋግጧል። በምስሉ ላይ የሚታየው ሰውም በትግራይ ክልል ሞቶ አልተገኘም። በመሆኑም መረጃውን ያጋራው አካል ሀሳቡን ለመደገፍ የተሳሳተ ምስል በመጠቀሙ ምክንያት ሀቅቼክ ከላይ የተጠቀሰውን መረጃ ሐሰተኛ ነው ብሎ ደምድሟል፡፡

አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ

 

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

 

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።

በምስሉ ላይ የሚታየው ወታደር በትግራይ ክልል በሚደረገው የህግ ማስከበር ስራ ላይ የሚገኝ ነው? 

በ30 ህዳር 2013 ዳዊት እንጢቾ በተባለ 5000 ጓደኞች እና 541 ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ በመሸታ ቤት ውስጥ መጠጥ እየጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ክልል ባለው ተልዕኮ ወቅት በግዳጅ ላይ ያለ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት አባል ነው በማለት ከታች የተቀመጠውን መረጃ አጋርቷል። ፅሁፉም “የብልፅጋና ፓርቲ ህግን በማስከበር ላይ ነው” ሲል ይነበባል፡፡ ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መጠጥ እየጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ክልል መሆኑን የሚያሳይ ያለመሆኑን ተከትሎ መረጃው ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡ 

በፌደራል መንግስት እና በህውሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ መካከል ከ29 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግጭት መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ ከሶስት ሳምንታት ውግያ በኋላ የፌደራል መንግስት ሀይሎች መቀሌ፣ ሽሬ፣ አዲግራት፣ አክሱም እና የተለያዩ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠራቸው የሚታወቅ ሲሆን የህወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ፒ.ኤች.ዲ) እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም በተለያዩ ወቅቶች የህወሃት አመራሮችና እና የትግራይ ልዩ ሀይል አባላት በመቀሌ ከተማ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ውድመት ለመቀነስ ሲባል ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን እንደገለፁ የሚታወቅ ነው። እነዚህ መረጃዎች የሚያሳዩት የፌደራል የመከላከያ ሰራዊትና እና የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ የትግራይ ክፍል ውስጥ ተሰማርተው በህግ ማስከበር ስራ ላይ እንደሚገኙ ነው።

 

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች የተባለ የምስል ማጣሪያን በመጠቀም የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክተው ከሆነ በፌስቡክ ተጠቃሚው የተለቀቀው ምስል በትግራይ በነበረው ግጭት  ጊዜ የነበረ አይደለም፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በ11 ህዳር 2013 ዓ.ም ፍራንክ ጋሹምባ በተባለ የኡጋንዳ የማህበረሰብ አንቂ (አክቲቪስት) እና ብሎገር  ነበር፡፡ በጊዜው ፍራንክ ጋሹምባ ምስሉን የለቀቀው “የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን የሚያስከብረው ወታደር” በማለት ከፃፈው የእንግሊዘኛ መልዕክት ጋር ነበር። በመሆኑም ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ በምስሉ ላይ ሲጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ውስጥ አለመሆኑን እና ወታደሩ የትግራይ ህዝብን ንብረት ሲበዘብዝ የሚያሳይ እንዳልሆነ ማረጋገጡን ተከትሎ ምስሉን ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡ 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

 

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

 

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ 

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

ከስር የሚታየው ምስል በማይካድራው ጭፍጨፋ ጊዜ የተነሳው ነው?

በታህሳስ 2፣ 2013 ዓ.ም ሰላም ንኩሉ የተሰኘ 3418 ጓደኞች እና 1337 ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ከስር በሚታየው ምስል ላይ የስለት መሳርያ ይዘው የሚገኙት ግለሰቦች በማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ናቸው በማለት የተለቀቀ ሲሆን ግለሰቡ ምስሉ በሚገባ ተይዞ ግለሰቦቹ ለህግ እንዲቀርቡ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ሀቅ-ቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ በማይካድራው ጭፍጨፋ ወቅት የነበረውን እውነታ የማያሳይ ሆኖ  ስላገኘው ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡

ምስል 1

 

 

በትግራይ ክልል በፌደራል መግስትና በሕወሓት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በጥቅምት 30  በህዳር 1 2013 ዓ.ም ከ600 በሚበልጡ ንፁሀን ዜጎች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጭፍጨፋው የተፈፀመው በከተማዋ የመንግስት አካላት እና የፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ በተደረገለት ራሱን ሳምሪ በማለት በሚጠራ አክራሪ ቡድን እንደሆነ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች ሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች መግለፃቸው የሚታወስ ነው። በተጨማሪም እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና አመነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፃ ወንጀለኞቹ በከተማዋ በሚኖሩ የአማራ እና ወልቃይት ኢትጵያውያን ላይ አሰቃቂውን የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀሙት ቆንጨራ፣ መጥረቢያ፣ ገመዶችን እና ሌሎች ስለታም ነገሮችን በመጠቀም መሆኑ ታውቋል፡፡ የማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ በገለልተኛ አካላት ምንም አይነት ምርመራ ማካሄድ የማይፈቀድ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖሰት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርመራዎች እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡ 

ምስል 1፡ በተጠቀሰው የፌስቡክ ገፅ የተሰራጨው ፎቶ። 


 

ሪቨርስ ኢሜጅ በተባለ የምስል ማጣርያ መንገድን በመጠቀም ሀቅቼክ ለማወቅ እንደቻለችው ከሆነ በፌስቡክ ገፁ ላይ የተለቀቀው ምስል ከ600 በላይ ሰዎች በተገደሉበት የማይካድራው ጭፍጨፋ ወቅት የተወሰደ አለመሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው ሀምሌ 3 2013 ሲሆን ኢብሳ የሚል ስም ባለው የትዊተር ገፅ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ እንደተለቀቀ መረዳት ይቻላል። በወቅቱ ኢብሳ ከላይ ከሚታየውን ምስል ከሌሎች አራት ምስሎች ጋር ያጋራ የነበረ ሲሆን ምስሎቹን “#ፍትህ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኦሮሞ ህዝቦች #አብይ መሄድ አለበት” ከሚል ፅሁፍ ጋር እንዳጋራ ከላይ የተቀመጠውን መስፈንጠርያ በመንካት ማየት ይቻላል። በመሆኑም ምንም እንኳን በማይካድራ በአሰቃቂ መልኩ በ600 ሰዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ላይ ጥቃቱን የፈፀሙት አካላት ስለታማ መሳርያዎችን እንደተጠቀሙ የተለያዩ ተዓማኒነት ያላቸው የመንግስት አካላትና በሰብአዊ መብት ዙርያ የሚሰሩ ድርጅቶች ቢገልፁም ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ በምስሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች ከሁኔታው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውም ስለሆኑ በማረጋገጡ የተነሳ መረጃውን የሀሰት ነው ሲል ፈርጆታል፡፡

 

አጣሪ፡ ሀጎስ ገ/አምላክ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

 

 

 

 

Exit mobile version