የተጣሩ መረጃዎች

ከበይነ መረብ ላይ ማጨበርበሮች እራስን መጠበቅ

ሀቅቼክ ግንቦት 2013 ዓ.ም ላይ በኢሜል፣ በማህበራዊ ድር ገፆች እና በመልዕክት መለዋወጫዎች ላይ ሲዘዋወሩ የነበሩ ሀሰተኛ አታላይ መልዕክቶችን አስመልክቶ ማሳሰቢያ ጽፎ ነበር። ከመልዕክቶቹ ጋር የተያያዙት ማስፈንጠሪያዎች (ሊንክ) የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት የግል መረጃዎን በቅጽ ላይ እንዲሞሉ የሚጋብዙ ናቸው።

ፊሺንግ (phishing) አንደኛው የሳይበር (የበይነ መረብ) ወንጀል አይነት ሲሆን ሰዎች የግል መረጃዎቻቸውን፣ የባንክ መረጃዎቻቸውን እንዲሁም የይለፍ ቃላቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ታልሞ ትክክለኛ እና ተዓማኒ የሆኑ አካላትን በማስመሰል በኢሜል፣ በስልክ፣ ወይም በአጭር መልዕክት መልክ የሚላኩ መልዕክቶች ናቸው።

ይህን መሰል ማጭበርበሮች እና ማታለያዎች እየተበራከቱ መምጣቱን ተከትሎ ሰወች ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ሀቅቼክ እንደሚከተለው ይዳስሳል።  

አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ አይነት አጭበርባሪዎች የሚፈልጉትን የግል መረጃ ለማግኘት የተለያዩ የበይነ መረብ ቅጾችን (online survey) ይጠቀማሉ። ይህ መረጃ የማንነት ስርቆት (identity theft) ለማድረግ ወይም መረጃውን ለሌላ ሶስተኛ አካል ለመሸጥ ሊውል ይችላል። ለማጨበርበር፣ ለመመዝበር እና ጥቃት ለመፈፀም አታላይ ማስፈንጠሪያዎችን (Malicious links) የሚጠቀሙት እነዚህ መልዕክቶች አንደኛው ግባቸው ገንዘብ ማግኘት ነው።

የተበከሉ ማስፈንጠሪያዎችን በመጫን (በመክፈት) ትሮጃን እና ቫይረሶችን የመሳሰሉ ግዑዛን ስልክዎትን ወይም ኮምፒውተርዎትን ይቆጣጠሩታል። በሀሰተኛ ድረ ገፅ ላይ መረጃዎን እንዲያስገቡም ሊገፋፉ ይችላሉ።

የሳይበር ደህንነት ባለሞያ እና በደቡብ ኮሪያ ዶንጉክ ዩኒቨርስቲ የፒኤችዲ እጩ የሆነው ህዝቂያስ ደንገቶ ፊሺንግን በአጭሩ ሲገልጸው “አንድን ተጠቃሚ ለማታለል ወይም የግል መረጃውን ለማግኘት የሚፈጠሩ የሀሰት ድረ ገፆች” ይላቸዋል።

እንደ ህዝቂያስ ማብራሪያ አጨበርባሪዎች የአንድን ትክክለኛ ወይም ተዓማኒ አካል ድረ ገፅ በማስመሰል በሌላ URL አዲስ የተሟላ የድር አድራሻ ይፈጥራሉ። “የግል መረጃዎን (ኢሜል፣ የይለፍ ቃል እና የመሳሰሉትን) ከሰጧቸው በኋላ ለራሳቸው ጥቅም ይጠቀሙበታል” አክሎም “ይህ ሰዎችን ለምጥቃት ቀላሉ መንገድ ነው” ይላል።  

እንደዚህ አይነት ማጨበርበሮችን እንዴት መለየት ይቻላል?

  • የፊሺንግ ወይም የማታለያ መልዕክቶች፤ የሚያውቁትን ወይም የሚያምኑትን ድርጅት ሊመስሉ ወይም ሊያስመስሉ ይችላሉ
  • እውነት መሆናቸውን ለማመን በሚያዳግት መልኩ የተጋነኑ ናቸው፤ ለአይን የሚማርኩ እና ቀልብን የሚገዙ ሆነው ይቀርባሉ
  • ማስፈንጠሪያውን እንዲጫኑ ለማድረግ ሽልማት አለው በማለት ይገፋፋሉ
  • በአብዛኛው አስቸኳይ ናቸው፣ በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃሉ፣ አንዳንዴም የማብቂያ ሰአት ወይም ገደብ ያስቀምጣሉ
  • የባንክ እና የመሳሰሉትን አካላት ነን በማለት የአገልግሎት ተጠቃሚዎቻቸው መሆንዎትን ይገልፃሉ (ነገር ግን ተጠቃሚ አይደሉም)

እራስን ከእንደዚህ አይነት ማጨበርበሮች እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

  • የማስፈንጠሪያውን ወይም የድር አድራሻውን በደንብ መመልከት፤ ከትክክለኛው ድረ ገፅ ጋር ማስተያየት
  • መልዕክቶቹን በጥርጣሬ መመርመር
  • የግል መረጃዎን ከመስጠት መቆጠብ
  • ከመቸኮል እና አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰድዎ በፊት ተረጋግቶ ለማጣራት መሞከር
  • ከማያውቁት ምንጭ የሚላኩ ማስፈንጠሪያዎችን በችኮላ አለመጫን
  • አብዛኞቹ አጭበርባሪዎች መረጃዎን ለምን ጥቅም እንደሚያውሉት በግልጽ ሰለማይገልጹ፤ የገፁን የግላዊነት ፖሊሲ መመልከት
  • ስሙ የተጠቀሰውን ድርጅት መጠየቅ እና ከሚመለከተው አካል ማረጋገጥ

ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪም ድረገጹ ከHTTP እና HTTPS የፍለጋ ጣቢያ የትኛውን እንደሚጠቀም ማስተያየት እንደሚያስፈልግ ህዝቂያስ ይመክራል። 

HTTPS ከHTTP የሚለየው HTTPS ደህንነቱ የተጠበቀ እና በአሁን ጊዜ ተዓማኒ የሆኑ ትቋማት የሚጠቀሙበት በመሆኑ ነው።

በመጨረሻም  “በአሳሽዎ (browser) ፍለጋ ሲያደርጉ የአድራሻ ማስገቢያው ላይ የተቆለ ቁልፍ ምልክት መኖሩን ያጢኑ። ምልክቱም ድረ ገፁ የሚጠቀመው HTTPS መሆኑን እና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያሳያል።”  በማለት ባለሞያው ያስረግጣል።

እውን ባንኮች በቴሌግራም ላይ የበዓል ሽልማት አዘጋጅተዋል?

የተለያዩ የቴሌግራም ገፆች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ አባይ ባንክን እና የአማራ ባንክን ስምና ሎጎ በመጠቀም የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያጋሩ ተስተውለዋል። በገፆቹ ውስጥ ያሉት መልዕክቶችም ባንኮቹ ለመጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የቴሌግራም ገፆች እንዲነቃቁ ለባለ ዕድሎች ሽልማት ማዘጋጀታቸውን ይገልፃሉ፡፡

የቴሌግራም ገፆቹም ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ እንደየቅደም ተከተላቸው 52,350 ፣ 7,733 እና 67,480 ተከታዮች አሏቸው፡፡

ሃቅቼክ ልጥፎቹን በመመርመር አታላይ መልዕክቶች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

         

    

 

 

የመጀመሪያው የቴሌግራም ገፅ “እንኳን ደስ አላቸችሁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀብት 1.1 ትሪሊየን ትርፍ ምክንያት በማድረግ  የባንካችን ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ እስከ መስከረም 5 ብቻ የሚቆይ የቴሌግራም ገፅ ማነቃቂያ የሚሆን ሽልማቶች ተዘጋጅቷል።” ካለ በኃላ ለዕድለኞች የሚሸልመውን ዝርዝር ያስቀምጣል፡፡

ሽልማቶቹም “1ኛ” ብሎ ካስቀመጠው  ለ200 እድለኞች ከ300,000 ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችና እያንዳንዳቸው ከ50,000 ብር በላይ ግምት ያላቸው ሙሉ የቤት እቃዎች እስከ 5ኛው ለ 100 ዕድለኞች 5ሺ ብር እና የሞባይል ቀፎች ድረስ ይዘረዝራል፡፡

በመጨረሻም ዕድለኞቹ የሚሸለሙበትን መስፈርት “መጀመርያ የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። በመቀጠል ይህንን መልዕክት ከ50 በላይ ለሆኑ ሰዎች በፍጥነት ሼር ያድርጉ፡፡” የሚል ማሳሰቢያ አያይዟል፡፡ 

ሁለተኛው ገፅም “ዕድልዎን ይሞክሩ። በአዲስ አመት ልዩ የ500,000 ብር ስጦታ ከአባይ ባንክ” በሚል አጓጊ ርዕስ ከጀመረ በኃላ ባንኩ ለሽልማት አዘጋጅቷል ያላቸውን ሽልማቶች እስከ ስድስተኛ ደረጃ ድረስ ይገልፃል፡፡ ሽልማቶች የተባሉትም 1ኛ ላይ ካስቀመጠው “ለ50 እድለኞች 500,000 ብርና እያንዳንዳቸው ከ40,000 ብር በላይ ግምት ያላቸው ማቀዝቀዣ ፊሪጆች” አንስቶ ስድስተኛ ላይ እስካስቀመጠው ለ50 እድለኞች 5,000 ብር ድረስ ሰዎችን ሊያጓጉ የሚችሉ የተለያዩ ደረጃዎችን በረድፍ ሰድሯቸዋል፡፡

ለመሸለምም የቴሌግራም ቻናሉን መቀላቀል ፣ መልዕክቱን ለ50 ሰው ማጋራትና በባንኩ ስም ወደተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ መቀላቀልን እንደመስፈርት አያይዟል፡፡

ሶስተኛው ገፅም የቴሌግራም ቻናሉን በመቀላቀልና ለ50 ሰው በማጋራት ለ200 ዕድለኞች ከሚሰጠው ከ300,000 ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች እስከ ለ 100 እድለኞች 5ሺ ብር እና የሞባይል ቀፎ ድረስ መሸለም እንደሚችሉ ልጥፍ አጋርቷል፡፡ ገፁ የሽልማቱን ምክንያትም “አማራ ባንክ በ2014 መባቻ ሥራ ለመጀመር ሙሉ ዘግጅቱን አጠናቋል! … ሥራ ሲጀምር በመላ ሐገሪቱ ለሚከፈቱ ከ200 በላይ ቅርንጫፎች ደንበኞችን በቀላሉ ለማሰባሠብ የቴሌግራም ቻናል ከፍቶ እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡” በማለት ገልፆአል፡፡

ሃቅቼክ የመረጃውን ሃቀኝነት ለማጣራት የአማራ ባንክ የቦርድ አባል የሆኑትን ዶ/ር ለጤናህ እጅጉን አነጋግሯል፡፡ የቦርድ አባሉም “በአማራ ባንክ ስም የሚወጡት የቴሌግራም መልዕክቶች የፈጠራ ወሬዎች  ናቸው” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ባንካችን እስካሁን ምንም አይነት የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ስለሌለው ደንበኞቻችን ራሳቸውን ከተመሳሳይ የሃሰተኛ መረጃዎች ይጠብቁ፡፡” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ከስድስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በይፋዊው የፌስቡክ ገጹ ላይ ደንበኞቹ ራሳቸውን በተቋሙ ስም ከተከፈቱ ሃሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እንዲጠብቁ ያሳሰበ ሲሆን ድርጅቱ የሚጠቀምባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ 

በተያያዘም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና የአባይ ባንክን ይፋዊ ድረ ገፆች ላይ የተቀመጡት የቴሌግራም አድራሻዎች ለቴሌግራም ተጠቃሚዎች ለበዓል ስለሚሰጡ ስጦታዎችም ሆነ ሽልማቶች የሚዘግቡ መረጃዎች እንደሌሉ ተመልክተናል፡፡

በመሆኑም ሃቅቼክ በቴሌግራም ላይ የተዘዋወሩት መልዕክቶች በባንኮቹ ዕውቅና የሌላቸው አታላይ መልዕክቶች እንደሆኑ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ተጠቃሚዎች እንዲህ አይነት መረጃዎችን በሚመለከቱበት ጊዜ፡

  • የድረ ገፁን ስም እና አድራሻ በሚገባ ማጤን
  • መረጃዎችን እንደመጡ ከማመን ይልቅ በጥንቃቄ መመልከት፣ የላኪውን ትክክለኛ አድራሻ ማረጋገጥ
  • በፍጥነት እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ፣ ጊዜ ወስዶ መመርመር
  • የተጠቀሰውን አካል (ድርጅት) በቀጥታ መጠየቅ ይመከራል።

ምስሎቹ በህውሃት ሃይሎች ተመተው የወደቁ ድሮኖችን ያሳያሉ?

አንድ የትዊተር ገጽ በሰኔ 20 ፣ 2013 ዓ.ም ባጋራው ትዊት (የትዊተር ልጥፍ) በአማራ ክልል አከባቢ ተመተው የወደቁ ወታደራዊ ድሮኖች ስለመኖራቸው ሁለት ምስሎችን አያይዞ ልጥፏል። ከምስሎቹ ጋር ተያይዞ የተጻፈው ጽሁፉ “ከትግራይ ሀይሎች ባገኘውት መረጃ መሰረት የፌደራሉ መንግስት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ድሮኖች በአማራ ክልል የግጭት ቀጠና ውስጥ በህውሀት ሃይሎች ተሞቶ ወድቋል” ሲል ይነበባል።

የትዊተር መረጃውም ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ከ 375 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

ከህዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል መንግስቱ እና በሕውሃት ሀይሎች መካከል ወራት ያስቆጠረ ግጭት እየተካሄደ ነው። ጦርነቱ የጀመረው ትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ህወሀት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ እንደሆነ የፌደራል መንግስቱ ተናግሯል። በግጨቱም ሂደት፤ የአየር ሀይሉ በዘመናዊ ድሮኖች (ሰው አልባ አውሮፕላኖች) ብቃት ያለው መሆኑን፤ እነዚህ ድሮኖችም በጦርነቱ ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆኑ ከፍተኛ የመከላከያ ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት አሳውቀዋል። 

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለው የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሎቹ አሁን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።

የመጀመሪያው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው ጥቅምት 10 ፣ 2013 ዓ.ም ሲሆን ምስሉ የሚያሳየው በአርሳክ ጦር አማካኝነት ጥቃት የደረሰበትን የቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላን ነው። ምስሉ የተወሰደው በ2012 ዓ.ም በነበረው በናጎርኖ-ካራባክ ጦርነት ወቅት እንደሆነ ተገልፁአል።

 ትክክለኛ ምስል 1

ሁለተኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው ሃምሌ ፣ 9 2012 ዓ.ም ሲሆን ምስሉ የሚያሳየው በአዘርባጃን እና በአርሜንያ መካከል በነበረው ጦርነት በሃገራቱ ሰሜናዊ ድንበር አካባቢ በአዘርባጃን ጦር ተመቶ የወደቀ የአርሜንያ ድሮን ነው።

ትክክለኛ ምስል 2

ስለሆነም የትዊተር ልጥፉ በሕውሃት ሃይሎች ተሞቶ የወደቀን የኢትዮጵያ ድሮን የማያሳይ በመሆኑ ሀቅቼክ መረጃውን ሀሰት ብሎታል።    

               

ምስሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሰሜን ኮሪያ ያደረጉትን ጉብኝት ያሳያል?

ከ106,708 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ነሃሴ ፣ 19 2013 ዓ.ም ባጋራው የፌስቡክ ልጥፍ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ ሰሜን ኮሪያ አቅንተዋል” ከሚል ጽሁፍ ጋር ሁለት ምስሎችን አያይዞ አጋርቷል።

ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ730 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

ከሳምንት በፊት ነሃሴ ፣ 12 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከአማካሪዎቹ ጋር በመሆን ለአንድ ቀን የስራ ጉብኝት ወደ ቱርክ አቅንቶ የቱርኩን ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን አግኝተው ነበር። በውይይታቸውም በሁለትዮሽ እና በቀጠናው ጉዳይ ላይ ተወያይተው በመጨረሻም  የወታደራዊ ስምምነት ማድረጋቸው ተነግሯል።  

ይህንን ተከትሎም ሀቅቼክ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የያያዙትን ምስሎች በሪቨርስ ኢሜጅ በተባለው የምስል መፈለጊያ ተመልክቷል። ምስሎችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፉት በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከሁለት አመት በፊት በተመሳሳይ ቀን (ነሃሴ 20 ፣ 2011 ዓ.ም) ነበር። ምስሎቹም የተወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንተው ከደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት፤ ሙን ጄ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነበር። 

ትክክለኛ ምስል

ምስል፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ 2011 ዓ.ም ወደ ደቡብ ኮሪያ ባቀኑበት ጊዜ የተወሰደ።

ከዚህ በተጨማሪም ነሃሴ ፣ 20 2013 ዓ.ም የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ወደ እኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ይህም ጠቅላይ ሚንስተሩ ለስራ ጉብኝት ከሀገር እንዳልወጡ ያሳያል። ይህ ጽሁፍ እስከ ተጻፈበት ጊዜ ድረስ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሜን ኮሪያ ጉዞ ከሚመለከታቸው አካላት የወጣ ምንም መረጃ የለም። 

ስለሆነም ሀቅቼክ መረጃውን አጣርቶ ምስሎቹ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ማድራጋቸውን የማያሳይ በመሆኑ መረጃውን ሀሰት ብሎታል። 

የቱርኩ ፕሬዝዳንት የትግራዩን ግጭት ለማስቆም የማደራደር ጥያቄ አቅርበዋል?

አልጀዚራ ነሃሴ 13 2013 ዓ.ም በፌስቡክ ገፁ ባጋራው ፅሁፍ “ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ትግራይ ያለውን ግጭት ለማደራደር ጥያቄ አቅርበዋል” ብሏል።

ልጥፉ በ አርእስት ፅሁፉ “የቱርኩ ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተዋል ነገር ግን ምንም አይነት ስምምነት ይፋ አልተደረገም” ይህ የፌስቡክ ልጥፍ ከ 437 በላይ በሆኑ ተጠቃሚዎች ተጋርቷል።

ሀቅቼክ በድረ-ገፁ ውስጥ ያለው ፅሁፉ መርምሯል። በፅሁፉ ውስጥም የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያና ትግራይ ያለውን ግጭት ለማደራደር ጥያቄ ስለማቅረባቸው የሚገልጽ መረጃ ሰላለመኖሩ አረጋግጧል። ሰለሆነም ሀቅቼክ በፌስቡክ ልጥፉ እና በድህረ ገፁ ባለው ፅሁፍ መካከል ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለ በማረጋገጥ ይህን የፌስቡክ ልጥፍ  አሳሳች አርእስት ብሎታል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነሃሴ 13 2013 ዓ.ም በቱርክ አንካራ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝታቸውም ከቱርክ አቻቸው  ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጠናው ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ትግራይ ላለው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄን እንደሚደግፉ  መናገራቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያና ሱዳን ድምበር መካከል ባለው የአልፋሻቅ መሬት ላይ ያለውን የድምበር ግጭት ለማደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር በአንካራ የነበራቸውን ጉብኝት አያይዞ አል-አረቢያ እንግሊዝኛ ባሳተመው ጽሁፍ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያና ትግራይ ታጣቂዎች መካከል ያለውን ግጭት ለማደራደር ጥያቄ አቅርበዋል ሲል አስነብቧል።  

ቀጥሎም አልጀዚራ በፌስቡክ ገጹ ላይ “ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ትግራይ ያለውን ግጭት ለማደራደር ጥያቄ አቅርበዋል” የሚል አርዕስት ያለው ጽሁፍ ለጥፏል።   

            ምስል፡ ከድህረ ገፁ ከተገኘ ፅሁፍ

ይሁን እንጂ በድህረ ገፁ ውስጥ ያለው ፅሁፍ ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ትግራይ ያለውን ግጭት ለማደራደር ጥያቄ ስለማቅረባቸው ምንም አይናገርም። ፅሁፉ በፌስቡክ ላይ ካለው ልጥፍ ጋር በ ርዕስም ሆነ በይዘት ይለያያል።

በድህረ ገፁ ላይ ያለው ፅሁፍ አርዕስት ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ትግራይ ላለው ግጭት ሠላማዊ መፍትሄ እንደሚፈልጉ የሚናገር ሲሆን በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል እንዲሁም በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መራብ ምክንያት የሆነው ይህ ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያላቸውን ፍላጎት መናገራቸውን ይነበባል። 

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያና ሱዳን ድምበር መካከል ያለውን የድምበር ግጭት ለማደራደር ቱርክ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን ይገልጻል።

 ምስል፡ አሶሽየትድ ፕሬስ

ሰለሆነም በፌስቡክ ልጥፉ ላይ ያለው አርዕስት በድህረ ገፁ ካለው ፅሁፍ ጋር ሀሰተኛ ግንኙነት እንዳለው ሀቅቼክ ስላረጋገጠ የፌስቡክ ልጥፉ ላይ ያለውን መረጃ አሳሳች አርእስት ብሎታል።

ምስሉ በኢትዮጵያ አየር ሃይል የህወሃት ሃይል ላይ አርምጃ መወሰዱን ያሳያል?

ከ215,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ነሃሴ 5 2013 ዓ.ም ባጋራው  ልጥፍ ላይ መረጃውን “ሰበር ዜና” በማለት ያጋራ ሲሆን ሙሉ ትስሁፉም “በአማራ ክልል ልዩ ስሙ ገረገራ ትምሕርት ቤት ውስጥ በድብቅ ካንፕ ሰርቶ የመሽገው “የጁንታ ሐይል” ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት በአየር ሐይላችን በተወስደ ኦፕሬሽን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ተችሏል።’’ ሲል ይነበባል። በልጥፉ የተጠቀሰችው ገርገራ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከላሊበላ 73.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማ ናት።

በመሆኑ ምስሎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰለሆኑ ሀቅቼክ መረጃውን ሀሰት ብሎታል።

ይህ ልጥፍ ከህዳር 2013 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሓት) ጦር መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ከነበሩት መካከል አንዱ ነው። ጦርነቱ ከተጀመረ ከሶስት ሳምንት በኋላ የፌደራል መንግስት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን እና አብዛኛዎቹን የክልሉን ክፍሎች ተቆጣጥሯል።

ይሁን አንጂ ጦርነቱ ከተጀመረ ከስምንት ወራት በኋላ የፌዴራሉ መንግሥት ወታደሮቹን ከክልሉ ለማውጣት ወስኛለው በማለት የአንድ ወገን ሰብዓዊ የተኩስ አቁም አዋጅ ማወጁ ተሰምቷል። ይህን ተከትሎ የቀድሞው የክልሉ እና የህወሓት አመራሮች የኢትዮጵያ ሰራዊት ከክልሉ መውጣቱ ተከትሎ  ሰኔ 21 ቀን 2013 የክልሉን ዋና ከተማ እና አብዛኞቹን የክልል ግዛቶች መልሰው ተቆጣጠሩ።

የህወሓት-ሀይሎች ከ መካከለኛው የትግራይ ክፍል እየወጡ ወደ ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ መገስገስ በመጀመራቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትግራይን ፣ አማራ እና አፋር ክልልን በሚዋሰኑ የድንበር አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው ተዘግቧል። ሀምሌ 29 በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ ከተማን የህወሓት ሀይሎች  መቆጣጠራቸው ተዘግቧል። ያንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ነሐሴ 4 ኢትዮጵያውያን በህወሓት ኃይሎች ላይ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል። በአማራ ክልል የአየር ኃይሉ በህወሓት ጦር ላይ ጥቃት ፈፀመ የሚለው የፌስቡክ ጽሑፍ በእነዚህ ሁኔታዎች ወቅት ተጋርቷል።

ሃቅቼክ ሪቨርስ ኢሜጅ በተባለ የምስል ማጣሪያ ገፅ ምስሉን ፈልጎ፤  ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው ጥር 5 2012 መሆኑን አረጋግጧል። ምስሉ የተወሰደው በወቅቱ በባርሴሎና አቅራቢያ በሰሜን ምስራቅ ስፔን በሚገኝ የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ከተከሰተ ፍንዳታ ላይ ነው።

የመጀመሪያው ምስል

መንግስት በህወሓት ሀይሎች ላይ ጥቃት መጀመሩን የሚገልጹ ዘገባዎች ቢኖሩም ፣ ሃቅቼክ ምስሉ በገረገራ በህወሓት ሀይሎች  ላይ የተፈጸመ ጥቃት አለመሆኑን አረጋግጧል። ስለሆነም ምስሉ ከጉዳዩ ጋር  ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀቅቼክ የፌስቡክ ልጥፉን ሀሰት ብሎታል።  

ምስሉ የሱዳን ወታደሮች ምዕራብ ጎንደርን እየተቆጣጠሩ መሆኑን ያሳያል?

በለሳ TV የተባለ ከ 47,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ሚያዚያ 29፣ 2013 ዓ.ም በለቀቀው የፌስቡክ ልጥፍ ወታደሮችን እና ፍንዳታን የሚያሳዩ ምስሎችን አጋርቷል። በትግርኛ የተጻፈው ጽሁፍ ሲተረጎም “የሱዳን ጦር ወደ ምዕራብ ጎንደር በመግባት አዳዲስ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ መሆኑን የሱዳን የዜና አውታሮች ዘግበዋል …” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ ከልጥፉ ጋር የተያያዙት ምስሎች የሱዳን ጦረ ምዕራብ ጎንደር መግባቱን እና ግዛቶችን መቆጣጠሩን የማያሳዩ መሆኑን አረጋግጧል። ሰለሆነም ምስሎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ ሀቅቼክ መረጃውን ሀሰተኛ ብሎታል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አከባቢ ከህዳር 2013 ጀምሮ ግጭት ነበር። የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በኤል ገዳርፍ በሰላም በር እና ማሃጅ አከባቢ ያሉ ግዛቶችን ከኢትዮጵያ ጦር እና ከታጠቁ ሚሊሻዎች ማስመለስ መቻሉን ገልፁአል። ታህሳስ 22 2012 የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በተረከበው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ግዛቶች መልሶ ማቋቋም እና ሙሉ ቁጥጥር ማድረጉን አስታውቀዋል። ሀገራቱ ጉዳዩን ለመፍታት እና ድንበሩን ለማካለል ውይይት እና ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። በቅርቡም ሱዳን በሚያከራክሩ ግዛቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትደራደር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቀረበውን ጥያቄ ተቀብላለች

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከልጥፉ ጋረ የተያያዘው የመጀመሪያው ምስል የተወሰደው በፈረንሳይኛ ተፅፎ ከታተመ ፅሁፍ ላይ ሲሆን ግንቦት 2006 ዓ.ም ነበር የተነሳው። ሁለተኛው ምስል የተወሰደው በአረብኛ ተጽፎ ከተለቀቀ የፌስቡክ ልጥፍ ጋር ሲሆን መጋቢት 2009 ዓ.ም ላይ መለቀቁን ያሳያል።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የድንበር ግጭት መኖሩ እውነት ነው። ሆኖም በፊስቡክ ላይ የተሰራጨውን ልጥፍ ሀቅቼክ መርምሮ ምስሎቹ የሱዳን ጦረ ምዕራብ ጎንደር መግባቱን እና ግዛቶችን መቆጣጠሩን የማያሳዩ መሆኑን አረጋግጧል። ሰለሆነም ምስሎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ኝኙነት የሌላቸው በመሆናቸው የፌስቡክ ልጥፉን ሀሰት ብሎታል።  

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች)  እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲን አስጠንቀዋል?

በ5 የካቲት 2013 ዓ.ም Gonder tube/ጎንደር የተባለ (ከ 141,693 በላይ ተከታዮች ያሉት) የፌስቡክ ገፅ የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ምስል በመለጠፍ  ከ CJTN ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ወቅት ለኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል በማለት አጋርቷል። ጓደኞቹም መረጃውን እንዲያካፍሉ ጥያቄ አቅርቧል። በአማርኛ የተፃፈው ፅሁፍ “… የኦሮሞ ብልፅግና ያልተረዳው ሀቅ ቢኖር ጀዋርም ሆነ ቄሮ የሚባለው ቡድን ለእኔ ስልጣን መልቀቅ ቅንጣት ሚና አልነበራቸውም እኔ ስልጣኔን ያስረከብሁት ህወሃትን የአማራ ህዝብ መፈናፈኛ ስላሳጣ ነበር የኦሮሞ ብልፅግና ከህወሓት መማር ይኖርበታል ሲሉ ለሲጅቲኤን ተናግረዋል…” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን በመመርመር የቀድሞው ጠ / ሚ ኃይለማሪያም የኦሮሚያን ብልጽግና ፓርቲን እንዳላስጠነቀቁ እንዲሁም በቅርቡ ከ ሲጂቲኤን (CJTN) ጋር ቃለ ምልልስ እንዳላደረጉ አረጋግጧል። ሰለዚህ መረጃውን ሀሰት በማለት በይኖታል።

 

የደርግ ስርዓት ካለቀበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዲግ ጥምረት / ፓርቲ ለሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን ገዝቷል። ህወሃት በጥምረቱ ውስጥ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የበላይነት የነበረው ሲሆን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እና ሕዝባዊ አመጾች በመላ አገሪቱ ተከስቶ ነበር። ከመንግስት ተቃዋሚዎች መካከል የብዙሃን የተቃውሞ ሰልፎች መሐንዲስ  የነበረው አንዱ መሪ ጃዋር መሃመድ በኦሮሚያ ቄሮ የሚባለውን የኦሮሞ ወጣቶች አደረጃጀት በመመስረት መንግስት በብዙ ዘርፎች ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ተጽዕኖ አርጓል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚያዚያ 2010 ዓ.ም ስልጣናቸውን እንዲለቁና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሊ (ፒኤችዲ) እንዲተኩ አስተዋትጾ አርጓል። 

በ 2012 ዓ.ም ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ በመሆን ስሙን ወደ ብልጽግና ፓርቲ ቀይሯል። ህወሃትም ፓርቲውን ለመቀላቀል የቀረበትንን ጥሪ ውድቅ በማድረግ ወደ ትግራይ ክልል ተመልሷል። ከዛም በኋላ 25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ በተደረገው ጥቃት በሕወሃት በሚመራው የትግራይ ክልል ኃይል እና በፌዴራል መንግሥት በሚመራው ኃይል መካከል የትጥቅ ትግል ተካሂዷል። በፌዴራሉ መንግስት የሚመራው ኃይል የህወሃት ኃይል እና ዋና አመራሩን አፍርሷል ቢባልም በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ቀጥሏል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አስጠነቀቀ በማለት በፌስቡክ ላይ የተለቀቀው ልጥፍ በሰፊው እየተሰራጨ ሲሆን በሌሎች ተጠቃሚዎች ከ147 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ሆኖም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ ከሲጄቲኤን ጋር ቃለ ምልልስ አለማረጋቸውን እና ለኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ በቪዲዮም ሆነ የጽሑፍ ቃለ ምልልስ እንዳልሰጡ የመገናኛ ብዙሃኑ ሁሉም ገፆች ላይ በተደረገ ምርመራ ለማወቅ ተችሏል። በእርግጥ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለውን የትጥቅ ግጭት አስመልክቶ በውጭ ፖሊሲ ላይ የአስተያየት መጣጥፍ ፅፈዋል ፡፡

ስለሆነም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኦሮሚያን ብልጽግና ፓርቲን እንዳላስጠነቀቁ እና ልጥፉን ለመደገፍ የተጠቀሙት ማጣቀሻ ትክክለኛ አለመሆኑን ሰላገኘ መረጃው ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል ፡፡

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳ ሞተው መገኘታቸውን ያሳያል?

በ 5 የካቲት 2013 ዓ.ም ወንድዬ ያለው የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሰበር- ዜና በተባለ ከ 157,000 በላይ አባላት ባለው የፌስቡክ ግሩፕ ላይ “ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳ ሞተው ተገኝተዋል” በማለት አጋርቷል። ከልጥፉ ጋር ተያይዞም ቃሬዛ የያዙ ወታደሮች ምስል እና ሙሉ ቪዲዮ ለመመልከት ያስችላል የተባለ የተሌግራም ማስፈንጠሪያ ይገኛል። ሆኖም ሀቀቼክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና የጌታቸው ረዳን አስከሬን እንደማያሳየው እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

 

 

ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሕወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል መንግሥት በሚመራው ኃይል መካከል የትጥቅ ትግል ተካሂዷል። 19 ህዳር 2013 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት የክልሉን ዋና ከተማ መቐለ ከተማ መቆጣጠሩ ተዘግቧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲም የህወሓት ከፍተኛ ሃላፊዎች እና ወታደራዊ መኮንኖች በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆኑንም ተስተውሏል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የህወሃት የጀርባ አጥንት የሚባሉት ስብሃት ነጋ ፣ የቀድሞው የትግራይ ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱ ፣ የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ተከስተ (ፒ.ኤች.ዲ) እና ሌሎችም ይገኙበታል። 6 ጥር 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰጠው መግለጫ ሶስት የህወሃት ባለስልጣናት፤ የህወሃት የፖለቲካ መሪ የነበሩት አባይ ፀሃዬ  ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን እና የህወሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ እና ሌሎች የቀድሞ ወታደራዊ አባላት መገደላቸው ተነግሯል።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ24 የካቲት 2012 ዓ.ም አርሚ ታይምስ (Army times) በተባለ የወታደራዊው ማህበረሰብ ዜና እና መረጃ ምንጭ በሆነ ድረ ገፅ። ምስሉ ጥቅም ላይ የዋለው በስልጠና ወቅት ሰለሚደርስ አደጋ በተፃፈ ጽሑፍ ላይ ሲሆን “18 ጥር 2012 ዓ.ም ወታደራዊ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት የበረራ ፓራሜዲክሶች አስቸኳይ የቀዶ ህክምና ጥሪ ደረሳቸው” ሲል ይነበባል። ምስሉ የተነሳው የአሜሪካ ጦር ፎቶግራፍ አንሺ በሆነው የመጀመሪያ ክፍል ሳጅን ጋሪክ ሞርገንዌክ (Sgt. 1st Class Garrick W. Morgenweck) ነበር።

ዋናው ምስል

 

በተጨማሪም በልጥፉ ላይ “ሙሉ ቪዲዮ በቴሌግራም ተለቋል፤ ሊንኩን ተጭነው ይግቡ” የሚል ፅሁፍ ከቴሌግራም ማስፈንጠሪያ ጋር የሚገኝ ሲሆን በቴለግራም ቻናሉ ውስጥ አለ የተባለው ቪዲዮም ይሁን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለው ምንም አይነት መረጃ አይገኝም። 

ምንም እንኳን በቁጥጥር ስር የዋሉ እና የተገደሉ የህወሃት ባለስልጣናት ቢኖሩም ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳ ስላሉበት ሁኔታ የሚታወቅ መረጃ የለም። ስለሆነም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ የደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳን አስክሬን የማያሳይ በመሆኑ እና ከመረጃው ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

ምስሉ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ ታመው በሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ያሳያል?

በ16 ጥር 2013 ዓ.ም ታጅዲን አህማዲ(Taajudin Ahamadi) የተባለ (ከ 3,900 በላይ ጓደኞቹ ያሉት) የፌስቡክ ተጠቃሚ ከዚህ በታች ያለውን ምስል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በጠና ታመው በሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ነው በማለት አጋርቶ ነበር። ልጥፉ የወጣው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሚዲያ መጥፋት ተከትሎ ስለደህንነቱ ጥርጣሬዎች እና የተለያዩ ግምታዊ አስተያየቶች እየተሰራጩ ባለበት ወቅት ነበር። ልጥፉ በተለያዩ ተጠቃሚዎች ሲሰራጭ ተስተውሏል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ምስሉ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ መታመማቸውን እና በሆስፒታል ውስጥ እየታከሙ መሆኑን የማያሳይ እና ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጠ/ሚ ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሚዲያ መጥፋት ተከትሎ ስለደህንነቱ ጥርጣሬዎች እና የተለያዩ ግምታዊ አስተያየቶች እየተሰራጩ ይገኛል። አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠና መታመማቸውን ሌሎች ደግሞ ሞተዋል በማለት ገምተዋል። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት ዙሪያ የሚነሱ ግምቶች ሐሰት መሆናቸውን አስታውቋል።  እነዚህ ያልተረጋገጡ ግምቶች እየተሰራጩ ባሉበት መካከል በ20 ጥር 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተጎዱ ወታደሮች እና ሲቪሎች የሰው ሰራሽ አካላት ማምረቻን ሲጎበኙ ታይተዋል

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ጎፈንድሚ በተባለ የበይነ መረብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሲሆን ቢድሃን ታፓ የተባለ ሰው በደረሰበት የልብ ምት ማቋረጥ (cardiac arrest) ምክንያት ሲረዳበት በነበረው ጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል መሞቱን ተከትሎ የቢድሃን ታፓ ሚስት ፕሪስኪላ ራይን ለመርዳት ምስሉን በመጠቀም ገንዘብ ለመሰብሰብ በድረ ገፁ ላይ ተለጥፏል። 

የተቀናበረው ምስል

የመጀመሪያው ምስል

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ደህናነት እና የጤና ሁኔታ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች እና መላምቶች ሲነሱ ይስተዋላል። ሆኖም ሀቅቼክ ልጥፉን ከመረመረ በኋላ ምስሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመማቸውን እንዲሁም በሆስፒታል ውስጥ በመታከም ላይ መሆናቸውን የማያሳይ እና ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

 

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Exit mobile version