የተጣሩ መረጃዎች

ሀሰት፡ ምስሉ የደሴ ከተማን ወቅታዊ ሁኔታ አያሳይም

ከ 194,424 በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ አካውንት በ ጥቅምት 12 ፣ 2014 ዓ.ም “ደሴ አሁን” በማለት አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። የፌስቡክ አካውንቱ ባለቤት እና የተሰጡት አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ምስሉ ከቀረበው ጽሁፍ ጋር ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ሕውሃት ከተማዋን እንደተቆጣጠራት ሲሆን ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ 700 ሰው በላይ ምላሽ ሲሰጥበት ከ 55 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ ምስሉ በጽሁፉ እንደተነበበው በጊዜው የነበረውን የደሴ ከተማ እንቅስቃሴን ስለማያሳይ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል። 

ካለፈው ዓመት  2012 ዓ.ም ጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕውሃት) ሃይሎች እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል እስካሁን የቀጠለን ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊው አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ በመስማማት የመከላከያ  እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ አስወጥቷል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ዜናዎች እና መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ። ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የፌደራሉ መንግስት ተደጋጋሚ የሆኑ የአየር ላይ ጥቃቶችን ማድረግ ጀምሯል። 

የሕውሃት ቃል አቀባይ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ እንደተናገረው ከሆነ የአየር ጥቃቱ የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ ያነጣጠጠረ እንደነበረ ሲናገር መንግስት በበኩሉ የአየር ጥቃቱ በሕውሃት ሃይሎች ተይዞ በነበረ የወታደራዊ ካምፕ ላይ ኢላማ ያደረገ እንደነበር እና የሕውሃትን ክስ እንደማይቀበል ይናገራል። ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሕውሃት ሃይሎች አሁንም ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች በተለይም ወደ ወሎ አካባቢ ሃይሎቻቸውን እያስጠጉ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ደሴ በደቡብ ወሎ ዞን ከ አዲስ አበባ 400 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በውስጧ ከ 200,000 በላይ ህዝብን ይዛለች። ከከተማዋ ፖለቲካዊ እና ስታራቴጂካዊ ጥቅም አንጻር ለሕውሃት ወደ ወሎ ለሚያደርገው ጉዞ ደሴ እንደ ቁልፍ ቦታ ሆና ትታያለች።

ትክክለኛው ምስል 

ይህ የፌስቡክ ልጥፍ በእነዚህ ሁኔታዎች መካከል የተነበበ ጽሁፍ ይሁን እንጂ በተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ መሰረት ምስሉ ጦርነቱ ከ ሶስት አመት በፊት በ ጥር 3 ፣ 2011 ዓ.ም የተለጠፈ እና ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞም የነበረ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።      

ወደ ኖርዌይ ሃገር ለመሄድ የሚሞላ የቪዛ ሎተሪ ፕሮግራም አለ?

ቴሌግራም መልዕክት “የኖርዌይ ቪዛ ሎተሪ መሙያ ቅጽ” የሚል አንድ ማስፈንጠሪያ ሲዘዋወር አስተውለናል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ 300 ጊዜ በላይ የታየው  ይህ መልዕክት የቪዛ እድሉ በአለም ዙሪያ ላሉ 45,000 ሰዎች የተሰጠ እድል እንደሆነ ይናገራል።። 

 

በልጥፉ የተያያዘው ማስፈንጠሪያ “የኖርዌይ ኢሚግሬሽን ዳይርክቶሬት” ወደሚል ገጽ ይወስደናል። ይህ ድህረ-ገጽ በውስጡ የሚሞላ ቅጽ ያለው ሲሆን ቅጹ የግል መረጃዎችን ከነዚህም ውስጥ አድራሻ ፣ ኢ-ሜይል ፣ የይለፍ ቃል እና ሌሎችንም እንድንሞላ ይጠይቃል።

 

የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ ፕሮግራም በ1948 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በየአመቱ ለ55,000 ሰዎች የቪዛ እድል ይሰጣል። የ2014ቱ የዲቪ ቪዛ ፕሮግራም(DV-2023) በመስከረም 26 ፣ 2014 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን የሎተሪ ቅጹ በኦንላይን ብቻ የሚሞላ እና የዚህ አመት የሎተሪ መሙያ ጊዜ ደግሞ እስከ ጥቅምት 30 ፣ 2014 ዓ.ም ድረስ ብቻ የሚቆይ ይሆናል።

በጥቅምት 4 ፣ 2014 ዓ.ም በጋና አክራ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ “ወደ አንድ ድህረ ገጽ የሚመራ ማስፈንጠሪያ በመልዕክት መልክ እየተዘዋወረ ስላለ ከዚህ የማጭበርበሪያ መንገድ ተጠንቀቁ። ይህ የጽሁፍ መልዕክት የኖርዌይ ቪዛ ሎተሪ ወደሚል ኦንላይን የሚሞላው የቅጽ ገጽ ይወስደናል። ይህ የሚሞላ ቅጽ፣ የጽሁፍ መልዕክት እና ድህረገጽ ከቪዛ መሙያ ሲስተም ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ማጭበርበሪያ ስለሆነ ከእንደዚህ አይነት የማጭበርበሪያ መንገዶች ተጠንቀቁ።” በተጨማሪም “እንደዚህ አይነት የሎተሪ ፕሮግራም የለንም” በማለት አሳውቆ ነበር።   

ሀቅቼክም በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኖርዌይ ኤምባሲ በኢሜል ያነጋገረ ሲሆን የኤምባሲው ቆንፅላ ጽህፈት ቤት “ኖርዌይ ምንም አይነት የቪዛ ሎተሪ ፕሮግራም የላትም” በማለት አረጋግጠውልናል። አዲስ አበባ በሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ  ለመኖሪያ እና ለስራ ሲሞላ የነበረው የቪዛ ፕሮግራም ከሃምሌ 25 ፣ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች የሚስተናገዱት በኬኒያ ናይሮቢ በሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ ነው።  

እንደ አሜሪካ ያሉ በህጋዊ መንገድ ወደሃገራቸው የመሄድን እድል የሚያመቻቹ ሃገራቶች እንዳሉ ሁሉ ኖርዌይ ግን እንደዚህ አይነቱን ዕድል መስጠት አልጀመረችም። 

ስለሆነም ይህ የቴሌግራም መልዕክት የግል መረጃዎችን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ስለሚጠይቅ እና አሳሳች የሆነ መልዕክት በመሆኑ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።      

ሀሰት፡ ምስሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ግጭት ምክንያት የተቃጠለ መኪናን አያሳይም

ከ140,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድሮኖችን በመጠቀም የአየር ላይ ጥቃቶችን አካሄደ” በማለት አንድ ልጥፍ አጋርቷል።  ይህን ጽሁፉ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ያለውን ግጭት የሚያሳይ በማለት የሚቃጠል መኪናን አያይዞ ለጥፏል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ልጥፍ ከ 55 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ነገር ግን ይህ ምስል በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል በመከላከያ ሰራዊት የተወሰደን የአየር ላይ የድሮን ጥቃት ስለማያሳይ ሀሰት ነው።

የሕውሃት ሃይሎች በሰሜን ዕዝ የሚገኘውን ሰራዊት ካጠቁ በኋላ በፌደራሉ መንግስት እና በሕውሃት ሀይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ጥቅምት 24 ፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን እንደቀጠለ ነው።

በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ የፌደራሉ መንግስት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ ሙሉ በሙሉ አስወጣ። የፌደራሉ መንግስት ከክልሉ ለቆ ከወጣ በኋላ የሕውሃት ሃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር እና ወደ አማራ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ እየተስፋፋ ሄዷል። ይህን ተከትሎም በፌደራል መንግስቱ የሚካሄዱ አዳዲስ የወታደራዊ እርምጃዎች እና የመልሶ ማጥቃት ሪፖርቶች በብዛት እየወጡ ይገኛሉ። የሕውሃት ቃል አቀባይ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአማራ እና አፋር ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር በመሆን የአየር እና የምድር ጥቃቶች እያደረጉባቸው እንደሆነ አረጋግጧል

ሆኖም በጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ከላይ የተያያዘው ምስል በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል የደረሰውን የመኪና ቃጠሎ እንደማያሳይ ለማረጋገጥ ተችሏል። ምስሉ ከዚህ ቀደም africanews.com በሚባል አንድ አፍሪካዊ እና አለማአቀፋዊ የሆኑ ዜናዎችን በሚያቀርብ የሚዲያ ተቋም “ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች የዳንጎቴ ፋብሪካ ጥቃት ደረሰበት” በማለት ከአንድ ዜና ጋር ተያይዞ ተለቆ ነበር። መስከረም 24 ፣ 2009 ዓ.ም በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በደረሰው ግጭት ላይ ባለቤትነታቸው የዳንጎቴ ሲሚንቶ የሆኑ የተለያዩ መኪኖች እና ማሽነሪዎች አዳ በርጋ የሚባል አከባቢ ሲቃጠሉ ውድ የሆነው የሰው ህይወት እና ብዙ የህዝብ መገልገያ የሆኑ ተቋማት ወድመዋል። 

ናይጀሪያዊው የቢዝነስ ሰው አሊኮ ዳንጎቴ በስፋት በሲሚንቶ ኢንደስትሪው ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በአፍሪካ ከሚገኙ ትልልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ ነው። ፋብሪካዎቹም ኢትዮጵያን ጨምሮ በናይጄሪያ ፣ ሴኔጋል ፣ ጋና ፣ ካሜሮን ፣ ዛምቢያ ፣ ታንዛኒያ እና ሳውዝ አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ። 

በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በትግራይ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ብዙ ምስሎች እየወጡ ቢሆንም በልጥፉ ላይ ለማሳየት የተሞከረው ምስል ግን አሁን በሰሜኑ ካለው ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስለሌለው ምስሉ ሀሰት ነው።   

ሀሰት:ተንቀሳቃሽ ምስሉ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በጦላይ ማሰልጠኛ ተገኝቶ ወታደሮችን ሲያዝናና አያሳይም

በዩቱዩብ ፣ በድህረ ገጽ እንዲሁም ከ484,227 በላይ ተከታይ ባለው በፌስቡክ ገጽ ላይ  “ቴዲ አፍሮ ሰራዊቱን ስርፕራይዝ አደረገ” በማለት አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን አጋርቷል። 

ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በድህረ ገጹ ላይ ከ20,900 ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን፣ የፌስቡክ ልጥፉ ደግሞ 1,700 ያህል ሪአክሽን አግኝቶ ከ60 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ከድህረ ገጹ እና ከፌስቡክ ልጥፉ አስቀድሞ ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተለቀቀው በመስከረም 6 ፣ 2014 ዓ.ም በዩቱዩብ ቻናሉ ላይ ሲሆን ከ1,120 በላይ ዕይታም አግኝቷል። 

ይሁን እንጂ ፣ የፌስቡክ ልጥፉ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል ተገኝቶ ወታድሮችን ሲያዝናና ስለማያሳይ ልጥፉ ሀሰት ነው።

 

ከህዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር(ትህነግ) ሃይሎች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግስት ጋር ጦርነት ላይ ናቸው። የተለያዩ የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የስልጠና ካምፖች ውስጥ በጣም ብዙ አዳዲስ ምልምል ሰልጣኝ ወጣቶች እየተቀላቀሉ እንደሆነ ዘግበዋል። ይህንንም በማስመልከት አርቲስቶች እንዲሁም ትላልቅ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ለአዳዲስ ምልምል እና ተመራቂ ወታደሮች ካምፖቻቸው ድረስ እንዲሁም የጦር ግምባሮች ድረስ በመሄድ ጎብኝተው አነቃቅተው እና አበረታተው ተመልሰዋል ተብሎ ሲዘገብ ሰንብቷል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም በቅጽል ስሙ ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ብዙ አድናቂዎች ያሉት ሙዚቀኛ ሲሆን “ኢትዮጵያ” የሚለው 5ተኛው አልበሙ በግንቦት 12 ፣ 2009 ዓ.ም በአለም የቢልቦርድ ሰንጠረዥን ተቆጣጥሮ ነበር። 

ይህን ተከትሎ የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል የፊትለፊት ምስል  የተቀነባባረ እንደሆነ ለማውቅ ተችሏል። ምስሉ የድምጻዊውን ፊት በተሰበሰቡ የሰራዊት አባላቶች መካከል በማቀናበር የተሰራ ሲሆን ከዚያም ባላፈ ግን የተንቀሳቃሽ ምስሉ ይዘት በውስጡ የቴዎድሮስ ካሳሁን እና የሰራዊቱ የተለያዩ ምስሎች ለየብቻ የሚያሳይ ነው።  

ከዚህም በተጨማሪ የድምጻዊው ማናጀር ከሆኑትን አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ በስልክ ባደረግነው ቆይታ መረጃው ፍጹም ሀሰት እንደሆነ እና አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንም በጦላይ ማሰልጠኛ እንዳልተገኘ አስረድተውናል።    

ስለዚህ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በጦላይ ማሰልጠኛ ተገኝቶ ሰራዊቱን አዝናና የሚለው መረጃ ሀሰት መሆኑ ትርጋግጧል  

              

 

ሀሰት: ምስሎቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አዳዲስ ወታደራዊ ድሮኖችን መታጠቁን አያሳዩም

 “ደስ የሚል ዜና፤ መከላከያ VTOL ድሮን ታጠቀ” የሚል  የፌስቡክ ልጥፍ መስከረም 27፣ 2014 ዓ.ም ትጋርቷል። መረጃውን ያሰራጨው ገፅ ከ69,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን በልጥፉ ላይ አያይዞም “እነዚህ ድሮኖች ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታር ማስወንጨፍ የሚችሉ እና የጠላትን አቅጣጫ በማነፍነፍ ጥቃት ማድረስ የሚችሉ ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ናቸው” ሲል ይነበባል።

ይሁን እንጂ ልጥፉ ላይ ያለው መረጃ የተዛባ በመሆኑ እና ከልጥፉ ጋር የተያያዘው ምስል የተሳሳተ በመሆኑ ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

በትግራይ ክልል ያለው ግጭት መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አየር ሀየሉ ዘመናዊ ድሮኖችን መታጠቁን እና በጦርነቱ ላይ መጠቀሙን አስታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢራን ድሮኖችን ታጥቋል የሚሉ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።

በልጥፉ የተጠቀሱት VTOL ድሮኖች ምንድን ናቸው?

VTOL የሚለው ቃል ሲተነተን (Vertical take-off and landing) ወይም ወደ ከፍታ በቀጥታ ተነስተው ማረፍ የሚችሉ ማለት ነው።

እነዚህ ድሮኖች ሰው አልባ ሲሆኑ እንደ ሄሊኮፕተር አቀባዊ በሆነ አቅጣጫ ተነስተው አኮብኩበው መልሰው ወደምድር መመለስ የሚችሉ ናቸው። ከVTOL ሰው አልባ ድሮኖች መካከል መልቲኮፕተር (Multicopter) የሚባሉት አንዱ ናቸው።

መልቲኮፕተር (Multicopter) የሚባሉት እነዚህ የድሮን አይነቶች ቀለል ያሉ የድሮን አይነቶች ሲሆኑ የግፊት ሞተራቸውን በመጠቀም ፍጥነታቸውን በመጨመር እና በመቀነስ መቆጣጠር ይቻላል።

VTOL የሚባሉት የድሮን አይነቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት በማዕድን ቁፋሮ፤ በኮንስትራክሽን ስራ፣ በነዳጅ ማምረቻ ድርጅቶች፤ ለአከባቢ ጥናት እና ካርታ ስራ እንዲሁም ለደህንነት እና መከላከያ ስራዎች ነው። በዚህም የሰፋፊ ቦታዎችን ምስል ለመውሰድ፤ መልክዓ ምድራዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንዲሁም የአየር ላይ ክትትል ወይም ስለላ ለማድረግ ይጠቅማሉ። በአጠቃላይ እነዚህ ሰው አልባ ድሮኖች በአይነቶቻቸው መሰረት ለተለያየ አላማ ይውላሉ።

ከላይ በቀረበው ጥቂት ገለፃ መሰረት እነዚህ VTOL ድሮኖች በፌስቡክ ልጥፉ እንደተገለፀው ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታሮችን ማስወንጨፍ የሚችሉ እንዳልሆኑ ተረድተናል። ይህም የፌስቡክ ልጥፉን ሀሰት ያደርገዋል።

በተጨማሪም በፌስቡክ ልጥፉ ላይ በተያያዙት ምስሎች ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ መሰረት ምስሎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቁት በሕዳር 15፣ 2011 ዓ.ም ዢኑዋ (Xinhua) በተባለ የዜና አውታር ላይ ነበር። የዜና ዘገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በቻይና ቤጂንግ በተዘጋጀው የድሮን ማብረር ስልጠና ላይ እንደተሳተፉ ዘግቧል።

ከዚህም ባሻገር የልጥፉን ሀሰተኛነት ከሚያሳዩት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላቱ የለበሱት ልብስ አሁን የተቀየረው እና ከ2012 ዓ.ም በፊት ሰራዊቱ ሲጠቀምበት የነበረው የደንብ ልብስ መሆኑ ነው።

ስለሆነም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት VTOL የተባሉ ከራዳር ውጪ በመሆን ሞርታሮችን መተኮስ የሚችሉ ድሮኖችን ታጥቋል የሚለው መረጃ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

ሀሰት፡ምስሉ አሜሪካ በቅርቡ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን የወታደራዊ እርዳታን አያሳይም

የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 2.9 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ ቁሳቁሶች በእርዳታ መልክ ድጋፍ አደረገች በማለት አንድ የፌስቡክ ልጥፍ መስከረም 26፣ 2014 ዓ.ም አጋርቶ ነበር። ልጥፉ የተሽከርካሪ መኪኖችን የሚያሳይ ሁለት ምስሎችን አያይዟል። ድጋፉ የተደረገው ኢትዮጵያ በሶማሊያ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የአልሸባብን እና ሌሎች የአሸባሪ ቡድኖችን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት መሆኑን አያይዞ ጽፏል።   

ይሁን እንጂ ምስሎቹ አሜሪካ በቅርቡ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያደረገችውን ድጋፍ እንደማያሳዩ ተረጋግጧል። በመሆኑም ልጥፉ ሀሰት ነው።  

የአሜሪካ መንግሰት ለኢትዮጵያ እርዳታ ከሚያደርጉ አካላት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በንጉሳዊ አገዛዝ ጊዜ ፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ እንዲሁም ከመስከረም 11 ጥቃት በኃላ ዋና ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ቆይታለች። ኢትዮጵያም አሜሪካ በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብን እና አሸባሪ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በምታደርገው እርምጃ ዋነኛ አጋር ነች።

ይሁን እንጂ የተለጠፉት ምስሎች አሜሪካ በቅርቡ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን የወታደራዊ ቁሳቁሶች አያሳይም። ምስሉ የሚያሳየው ከአመት በፊት አሜሪካ ለኢትዮጵያ ያደረገችውን የወታደራዊ መገልገያ መሳሪያዎች ድጋፍ ነው። 

በምስሉ ላይ የሚታዩት መኪኖች እና አምቡላንሶች በመስከረም 19፣ 2013 ዓ.ም በአሜሪካ የመከላከያ ዲፓርትመንት በኩል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተበረከተ ነበር። 2.9 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣው ይህ ወታደራዊ ድጋፍ በቀጠናው አካባቢ በአልሸባብ አና በሌሎች አሸባሪ ድርጅቶች አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ታስቦ ነው። እርዳታውም አምቡላንሶችን ፣ ላንድ ክሩዘር መኪኖችን ፣ ከባድ ጭነት መኪኖችን የተለያዩ መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ስልጠናዎችን ያካተተ ነበር። 

እነዚህ ምስሎች መስከረም 19 ፣ 2013 ዓ.ም መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ባደረገ አል-አይን በተባለ የሚዲያ ተቋም ታትመው ነበር። ምስሉን አና ጽሁፉን ለመመልከት እዚህ ጋር ይጫኑ ። 

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግስት የተለያዩ ወታደራዊ ድጋፎችን አግኝታ የነበር ቢሆንም እነዚህ ምስሎች ግን ኢትዮጵያ በቅርቡ ከአሜሪካ ያገኘችውን ወታደራዊ ድጋፎችን አያሳይም።ስለዚህ ሀቅ-ቼክ ልጥፉን መርምሮ እና አገናዝቦ ሀሰት ብሎታል።

ሀሰት፡ ምስሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በግዳጅ ላይ መሆኑን አያሳይም

ከ100 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ አየር ሃይል በግዳጅ ላይ!!” በማለት ሁለት ተመሳሳይ ምስሎችን በመስከረም 2 ፣ 2014 ዓ.ም አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖችን ጨምሮ ልጥፉ ከ160 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ሃቅቼክ ምስሎቹን አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

ከህዳር 2012 ዓ.ም አንስቶ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ልጥፎች መካከል ይህ አንዱ ነው። ጦርነቱ የተጀመረው የሕውሃት ሃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ራሱን የመከላከል እርምጃ በማለት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመወሰዱ ነው። ግጭቱ መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድሮኖችን መጠቀም መጀመሩን እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቱ አየር ሃይል ዘመናዊ የጦር ድሮኖችን እየተጠቀመ መሆኑን አስታውቋል። ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎችም የወታደራዊ እርምጃዎች እንደቀጠሉ ይገኛሉ።

ሆኖም የጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ምስሉ ሰኔ 8 ፣ 2009 ዓ.ም በተለቀቀ የዩቲዩብ ቪዲዮ ላይ ይገኛል። ቪዲዮው “የኔቶ ሃይሎች በምን ያህል ፍጥነት ግዳጃቸውን ይፈጽማሉ? የኔቶ ሃይሎች በሮማኒያ  ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ” የሚል አርዕስት ያለው ሲሆን ከ15 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተቀረጸው በሮማኒያ ውስጥ “Exercise noble jump 17” በተባለ የወታደራዊ ልምምድ ወቅት ነው።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አየር ሃይል በሕውሃት ሃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ቢያሳዩም ይህ ምስል የኢትዮጵያ አየር ሃይል እርምጃ ሲወስድ አያሳይም። ስለሆነም በፌስቡክ ገጹ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ሀሰት ነው።  

ሀሰት፡ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በአፋር ግምባር የተደረገን ወታደራዊ እርምጃ አያሳይም

መስከረም 7 ፣ 2014 ዓ.ም ከ 35ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገጽ ላይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል  ተሰራጭቷል። ከተንቀሳቃሽ ምስሉም ጋር  “የአፋር ጀግኖች እና የመከላከያ ሰራዊት የሕውሃት ሃይሎችን ሲያባርሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ደርሶናል…” የሚል ጽሁፍ ተያይዟል። ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ 3800 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ በፌስቡክ ገጹ ላይ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል በአፋር ግምባር የተደረገን ወታደራዊ እርምጃ እንደማያሳይ እና ልጥፉ ሀሰት እንደሆነ ተረጋግጧል።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም ሕውሃት በሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ሕውሃት ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል። ጦርነቱ ከተጀመረ ከሶስት ሳምንታት በኋላ የፌደራሉ መንግስት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን ከተሞች ተቆጣጥሯል። ነገር ግን ስምንት ወራትን ከፈጀው ጦርነት በኋላ የፌደራሉ መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማወጅ በክልሉ የነበሩትን የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ እና ከአካባቢው አስውጥቷል

በ ሰኔ 21 2013 ዓ.ም የፌደራል መንግስቱ የተናጥል የተኩስ አቁሙን ስምምነት  ይፋ አድርጎ ከክልሉ ለቆ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሕውሃት ሃይሎች የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌን መቆጣጠር ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች ተስፋፍቷል። 

ይህ የፌስቡክ ልጥፍም ይህን በክልሉ እና አካባቢው ባለው ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ሲዘዋወር የነበረ ነው።  

ይሁን እንጂ ፣ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በተወሰደ ምስል የጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም አሁን በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል ካለው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተወሰደው ግንቦት 21 2013 በሳውዲ አረብያ ድንበር ላይ ጂዛን አክሲስ ተብላ በምትጠራው አካባቢ በሳውዲ እና በየመን ጦር መካከል የተደረገን ጦርነት የሚያሳይ ነው።  

ተንቀሳቃሽ ምስሉ 

ስለዚህ መረጃውን ስናጣራ ባገኘነው መረጃ መሰረት በአፋር አካባቢ ከሕውሃት ሃይሎች ጋር የተደረገ ጦርነት ያሳያል ተብሎ የተስራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ሀሰት ነው።

ትክክል፡ ደቡብ ግሎባል ባንክ ለቴሌግራም ተጠቃሚዎች ሽልማቶችን አቅርቧል

ከዚህ በፊት ሃቅ ቼክ ባስነበበው ጽሁፍ ፣ በአንዳንድ የቴሌግራም ቻናሎችና ግሩፖች ላይ ባንኮች አጓጊ ሽልማቶችን አዘጋጅተዋል በማለት ቻናሎቹን እንዲቀላቀሉ እና ማስፈንጠሪያዎቹን ለብዙ ሰዎች እንዲያጋሩ በማድረግ እንደሚያታልሉ አጋርቷል ።

የገጻችን ተከታታዮች ባቀረቡልን ጥያቄ መሰረት በቴሌግራም ላይ ሽልማቶችን ያቀረበ እና ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ቻናል አጣርተናል። ይህ በደቡብ ግሎባል ባንክ ስም የተከፈተው ቻናል ባስተላለፈው መልዕክት “ደቡብ ግሎባል ባንክ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ እስከ መስከረም 30/2014 ዓ.ም የሚቆይ የቴሌግራም ገፅ ማነቃቂያ የሚሆን ሽልማቶች አዘጋጅቷል” ሲል ይነበባል።

ከዚህ በፊት ከነበሩት የቴሌግራም ማላለሎች በተለየ ሃቅቼክ መልዕክቶቹ በትክክልም የተላኩት ከባንኩ መሆኑን አረጋግጧል።   

        

ልጥፉ አራት የተለያዩ የሽልማት አይነቶችን አስቀምጧል። የመጀመሪያው ሽልማት ለ ሶስት እድለኛ አሸናፊዎች ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችን ሲያስቀምጥ ካሉት ሌሎች የሽልማት አይነቶች መካካል ለአንድ ወር የሚቆይ የ ዲኤስቲቪ ዲኮደር ፓኬጅ ፣ የባንኩ የጎልደን ሜምበርሺፕ አካውንት እንዲሁም የ100 ብር የሞባይል ካርዶች ይገኙበታል።

ታድያ ይህን እድል መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች በመጀምሪያ ቻናሉን መቀላቀል ሲኖርባቸው በመቀጠልም ማስፈንጠሪያውን ለ50 ሰዎች በማጋራት ቻናሉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ምልክቱ ያስነብባል።

ይህን ነገር ለማጣራት ባደረግነው ጥረት መሰረት የደቡብ ግሎባል ባንክ ማርኬቲንግ እና ብራንድ ሲንየር ኦፊሰር የሆኑትን አቶ ተመስገን ፍቃዱን አነጋግርን “ የቴሌግራም ቻናሉ ትክክለኛ መሆኑን እና ለቴሌግራም ተጠቃሚዎችም የ100 ብር የሞባይል ካርድ ፣ የሞባይል ቀፎዎችን እና የዲኤስቲቪ ዲኮደሮችን እየሸለምን ነው” በማለት ገልጸውልናል።

በተጨማሪም የባንኩን የማርኬቲንግ እና የብራንድ ኦፊሰር የሆኑትን አቶ አስናቀ ወርቁ ሽልማቱ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠውልናል። ወደተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች በመደወል የመረጃውን ትክክለኛነት አረጋግጠናል።

ስለዚህ በደቡብ ግሎባል ባንክ ስም የቀረበው የአዲስ አመት የቴሌግራም መልዕክት ትክክል መሆኑን እንግልጻለን።           

ሀሰት፡ ምስሉ በቅርቡ በመቀሌ ከተማ የተደረገን የከባድ መሳሪያ ጥቃት አያሳይም

ጳጉሜ 3 2013 ዓ.ም ከ11 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ  በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ድምጽ በመቀሌ ከተማ ተሰምቷል በማለት አንድ ምስል አጋርቷል።

በተጨማሪም ልጥፉ “ከመቀሌ 49 ኪ.ሜ  ርቃ በአፋር ክልል በምትገኘው እና  አብላ ተብላ የምትጠራው ከተማ ድረስ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ ጽፏል”።

ይሁን እንጂ ምስሉ በቅርቡ በከተማዋ የተከሰተ ሁኔታን የሚያሳይ ባለመሆኑ ሀሰት ነው።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም ሕውሃት በሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ሕውሃት ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል። ጦርነቱ ከተጀመረ ከሶስት ሳምንታት በኋላ የፌደራሉ መንግስት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን ከተሞች ተቆጣጥሯል። ነገር ግን ስምንት ወራትን ከፈጀው ጦርነት በኋላ የፌደራሉ መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማወጅ በክልሉ የነበሩትን የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ እና ከአካባቢው አስውጥቷል

በ ሰኔ 21 2013 ዓ.ም የፌደራል መንግስቱ የተናጥል የተኩስ አቁሙን ስምምነት  ይፋ አድርጎ ከክልሉ ለቆ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሕውሃት ሃይሎች የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌን መቆጣጠር ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች ተስፋፍቷል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌስቡክ ልጥፉ ከባድ መሳሪያ ጥቃት የሚመስል ፍንዳታን የሚያሳይ ምስልን አጋርቷል።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለው የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው ሕዳር 7 2013 ዓ.ም በቪኦኤ አማርኛ ድህረ-ገጽ ላይ ነው። ምስሉም የተለቀቀው ድህረ-ገጹ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው ዘገባ ላይ ነበር። ዘገባውም ባሰፈረው ጽሁፍ በመቀሌ ከተማ በደረሰ የአየር ጥቃት አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱንና የመኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸውን አመላክቷል።

ስለዚህ በፌስቡክ ልጥፉ የተመለከተው ምስል በቅርቡ በከተማዋ መቀሌ ደረሰ የተባለውን የተኩስ ድምጽ እና በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃትን የሚያሳይ ስላልሆነ ምስሉ ሃሰት ነው።   

Exit mobile version