ሀሰት ፡ ምስሉ ትግራይ ድንበር አካባቢ የሰፈሩ የኤርትራ ወታደሮችን አያሳይም

ከ100 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ መጋቢት 17 ቀን፣ “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ውሳኔ [ለሰብዓዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ ማቆምን] ተከትሎ የኤርትራ ጦር ትግራይ ድንበር አካባቢ 13 ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቀ ክፍለ ጦር ወደ ድንበር አስጠጋች” የሚል የፅሁፍ መግለጫ ያለው አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ1400 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ 140 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ነገር ግን ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱ ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።    

ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም መንግስት ከህወሓት ጋር አየተደራደረ ነው ተብሎ የሚናፈሰውን መረጃ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ “ስለ ድርድር ጉዳይ ብዙ ሲወራ ሰምቻለው ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ድርድር የሚባል ነገር የለም” በማለት ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፣ “እስካሁን ድረስ ድርድር አላደረግንም ማለት እስከመጨረሻው ድረስ ንግግር(ድርድር) አናደርግም ማለት አይደለም ምክንያቱም ድርድር እና ንግግር ችግርን የመፍቻ አማራጮችን የምናይበት ነው” በማለት የመንግስትን አቋም አሳውቀዋል። 

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም የፌደራሉ መንግስት አስቸኳይ እና አላማውን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ ያደረገ ግጭት ማቆም አውጇል። መንግስት በመግለጫው አንዳሳወቀው፣ ውሳኔው ወደትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ችግር ማድረስንና ህይወት ማዳንን ታሳቢ ያደረገ ነው። በመግለጫው መንግስት ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አማፂያኑ “ከማንኛውም የጦርነት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ እንዲሁም ከተቆጣጠሯቸው አጎራባች አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ” አንዱ ነው።

ይህንን የፌደራሉን መንግስት ውሳኔ ተከትሎ ህወሓት በበኩሉ የትኛውንም አይነት ግጭት ለማቆም ተስማምቷል። 

ነገር ግን ይህ የዕርቅ ውሳኔ በሂደት ላይ ባለበት ሰዓት የመከላከያ ሰራዊት ትግራይ ድንበሮች አካባቢ እየተጠጋ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሀሳብ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።   

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት ጥረት ያደረገ ሲሆን ምስሉ ከዚህ ቀደም ሀምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም “ሳዋ-የብሄራዊ ቀን የብር እዮቤልዩ ክብረ በዓል” በሚል ርዕስ የታተመ ፅሁፍ አካል ሆኖ አግኝቶታል።  

ፅሁፉ ሳዋ ተብሎ የሚጠራው የኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የነበረውን የብር እዮቤልዩ ክብረ በዓልንና የ32ተኛ ዙር ምልምል ሰልጣኝ ወታደሮች የተመረቁበት ሁነትን በማስመልከት የቀረበ የዜና ሪፖርት ነበር። 

የኤርትራ ጦር በትግራይ ድንበር አካባቢ ሰፍሯል የሚሉ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ይህ የፌስቡክ ፖስት ፅሁፉን ለመደገፍ የተጠቀመው ምስል የቆየ እና ከመረጃው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው ነው።

ይህም በመሆኑ የፌስቡክ ፖስቱ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመውን ምስል አጣርቶ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።     

H.R. 6600 እና S.3199 የሚባሉት ረቂቅ ህጎች ፀድቀዋል? ሩሲያ እና ቻይናስ ህጎቹ እንዳይፀድቁ በድምፃቸው መሻር ይችላሉ?

ከሰሞኑ በተለያዩ የሶሻል ሚድያ አውታሮች ላይ H.R.6600 እና S.3199 በተባሉ ረቂቅ ህጎች የአሜሪካው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያለውን ግጭት እንዲያቆም ለማስገደድ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው አቅርቧል። እነዚህን ረቂቅ ህጎች በተመለከተ በማህበራዊ ሚድያው ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ የነበሩ ፖስቶች እና አሳሳች ሪፖርቶች ተስተውለዋል።

ሀቅቼክ ከነዚህ ህጎች ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ እንዲሁም አሳሳች የሆኑ መረጃዎች እና ሪፖርቶችን ተመልክቷል። አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶችም S.3199 የተባለው ረቂቅ ህግ እንደፀደቀ አድርገው መረጃ ሲያስተላልፉና ሲያዘዋውሩ ሰንብተዋል።

ሌሎች ደግሞ H.R.6600 የተባለው ህግ በሩሲያ እና በቻይና ተቃውሞ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውሳኔውን ሊያቋርጡት እንደቻሉ አስነብበዋል።  

እነዚህን ሀሰተኛ እና አወዛጋቢ መረጃዎችን በጥቂቱ ለማሳየት ያክል :- 

የረቂቅ ህጎቹ አላማ ምንድን ነው? 

የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች ላይ የተንፀባረቁት ኃሳቦች ይህን የሚመስሉ ሲሆን በህጎቹ ዙሪያ የሚቀርቡ መረጃዎችን ትክክለኝነት ለመረዳት በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረቡት እነዚህ ህጎች ምንድን ናቸው፣ ህግ ሆነው የሚፀድቁበት ሂደትስ ምን ይመስላል የሚለውን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

HR6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋትን ፣ ሰላምን እና ዴሞክራሲን ለማምጣት ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ተዋወቀ። የአሜሪካ ሴኔት አባል በሆነው ቶም ማልኖውስኪ አነሳሽነት እንዲሁም የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል በሆኑት ማይክል ማኮውል እና ግሪጎሪ ሚክስ ደጋፊነት የቀረበው ይህ ረቂቅ ህግ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማቆም በኢትዮጵያ መንግስትና በግጭቱ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ላይ ጫና ማሳደርን እሳቤ ያደረገ የህግ ማዕቀፍ ነው።    

ይህ ረቂቅ ህግ ከፀደቀ ንብረቶችን ማገድ፣ የቪዛ ክልከላ እንዲሁም ከአሜሪካ እና አለም አቀፍ ከሆኑ ተቋማት የእርዳታ ክልከላ እንዲደረግ ያስችላል።  

ሌላኛው ረቂቅ ህግ S.3199  ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ የሴኔት አባል በሆነው ሮበርት ሜንዴዝ አነሳሽነት የተዋወቀ ነው።  ይህ ረቂቅ ህግ እንደ ህግ ከፀደቀ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖችን በገንዘብ እንዲሁም በጦር መሳሪያ የሚደግፉ አካላት ላይ ማዕቀቦችን  ለመጣል የሚያስችል ህግ ነው። 

S.3199 ህግ በዋነኝነት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስት ከአለም አቀፍ ተቋማት የሚሰጡ ማንኛውም አይነት የብድር እንዲሁም የብድር ማራዘሚያዎችም ሆነ የትኛውንም አይነት የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፎች ላይ ክልከላ የሚያደርግ ህግ ነው። 

የመንግስት አቋም

የነዚህ ረቂቅ ህጎች ጉዳይ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚድያ አውታሮች ላይ በሰፊው አወዛጋቢ እና አወያይ ሀሳብ ሆኖ ቆይቷል። በአሜሪካና በተለያዩ የአለም ክፍሎችም ህጎቹን በመቃወም ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ የረቂቅ ህጎቹን መፅደቅ የሚያበረታቱ የተቃውሞ ሰልፎችም ተደርገዋል።

ረቂቅ ህጎቹን በማስመልከት መጋቢት 13 ቀን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ አቶ ደመቀ መኮንን ውጭ ሀገራት ላሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች H.R.6600 እና S.3199 ረቂቅ ህጎችን በመቃወም ሰልፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።  

በተጨማሪም መጋቢት 15 ቀን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሰነዶቹ እንዳይፀድቁ የሚያደርጉትን ተቃውሞ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።  

በቅርቡም በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የHR6600 እና S3199 ረቂቅ ህጎችን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎ ነበር።

ህጎቹ እውን ፀድቀዋል? አሜሪካና ቻይናስ ህጉን መሻር ይችላሉ?

ረቂቅ ህጎቹን በተመለከተ በማህበራዊ ሚድያ አውታሮች ሲዘዋወሩ ከነበሩት ኃሳቦች አንዱ ረቂቅ ህጎቹ እንዳይፀድቁ በሩሲያ እና ቻይና አማካኝነት ውድቅ መደረጉን የሚያሳዩ ነበሩ። 

ይሁን እንጂ እነዚህ ረቂቅ ህጎች በአሜሪካ መንግስት ምክር ቤቶች የቀረቡ በመሆናቸው በአሜሪካ በብሄራዊ ደረጃ ብቻ የሚፀድቁ ይሆናል። እነዚህ ረቂቅ ህጎች በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና በአለም አቀፍ ስምምነቶች ደረጃ የሚወሰኑ ማዕቀቦች አይደሉም። 

ይህም በመሆኑ ሩሲያም ሆነ ቻይና ያላቸውን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ሊጠቀሙ የሚችሉት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫና ስልጣን ብቻ ሲሆን፣ በአንፃሩ እነዚህ H.R.6600 እና S.3199 ረቂቅ ህጎች በአሜሪካ መንግስት ደረጃ የቀረቡ በመሆናቸው የህጎቹ መፅደቅ ላይ ምንም አይነት መብትና ስልጣን አይኖራቸውም። 

ሁለተኛው እና አወዛጋቢ ጉዳይ የነበረው የS3199 ረቂቅ ህግ በቅርቡ ህግ ሆኖ ፀድቋል የሚል ነበር።

እነዚህ ሁለቱ ረቂቅ ህጎች ህግ ሆ 5 የተለያዩ ደረጃዎችን ማለፍ ይኖርባቸዋል። እነዚህም ለውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ መተዋወቅ፣ በሴኔቱ መፅደቅ በመቀጠልም በምክር ቤቱ መፅደቅ ያለበት ሲሆን በመጨረሻም በፕሬዝዳንቱ ከፀደቀ በኋላ ህግ መሆን ይችላሉ። 

በሌላ መልኩ ረቂቁ በሴኔት አባል አማካኝነት የቀረበ ከሆነ በሴኔቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ድምፅ ተሰጥቶበት ወደ ሙሉ ሴኔት የሚተላለፍ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ረቂቅ በተወካዮች ምክር ቤት አባል የቀረበ ከሆነ በውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ድምፅ ተሰጥቶበት ወደ ሙሉ የተወካዮች ምክር ቤት ይተላለፋል።

ከነዚህ በአሜሪካ ረቂቅ ህጎችን የማፅደቅ ሂደት አንፃር ስንመለከተው፣ S3199 ረቂቅ ህግ የቀረበው በሴናተር አማካኝነት ነው። በሴኔቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ረቂቁ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሴኔቱ ድምፅ እንዲሰጥበት ተላልፏል። ይህ ረቂቅ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ በሴኔቱ፣ በተወካዮች ምከር ቤት እና በአሜሪካው ፕሬዝደንት መፅደቅ አለበት። ይህ ረቂቅ ህግም ወደ ፕሬዝደንቱ ከማለፉ በፊት በሴኔቱ እና በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት የሁለቱን ድምፅ ማግኘት አለበት።

በሌላ በኩል HR6600 የሚባለው ረቂቅ ህግ የተዘጋጀው በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ነው። ይህ ረቂቅም የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ድምፅ ተሰቶበት ወደ አሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ተላልፏል። በተመሳሳይ ሁኔታም ይህ ረቂቅ ህግ በተወካይ በሴናተሮች ፀድቆ በመጨረሻም በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት ወደ ህግ መቀየር ይኖርበታል። 

ከዚህ መመልከት እንደምንችለው እነዚህ ሁለት ረቂቅ ህጎች እስካሁን ህግ ሆነው አልፀደቁም። በመሆኑም እነዚህ ረቂቅ ህጎች በሂደት ላይ ያሉ ሲሆኑ ህግ ሆነው እንዲፀድቁ ሶስት ሂደቶችን፤ ማለትም በሴኔቱ፣ በተወካዮች ምክር ቤት፣ እና በመጨረሻም በፕሬዝደንቱ ሊፀድቅ ይገባዋል።

ሀሰት፡ ምስሉ በኤርትራ የአየር መቃወሚያዎች ተመቶ የወደቀን አውሮፕላን አያሳይም

ከ110ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት “ከሱዳን የጦር መሳሪያ ጭኖ በኤርትራ የአየር ክልል ወደትግራይ ክልል ሲበር የነበረ አንቶኖቭ አውሮፕላን በኤርትራ የአየር መቃወሚያዎች ዶግ አመድ ሆኖ ወደ መሬት ሲበተን” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ መጋቢት 7 ቀን ላይ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተከሰተው ግጭት ለብዙዎች መፈናቀል ፣ ሞት እና መሰደድ ምክንያት ሆኗል። 

ሕዳር 5 ቀን ፤ 2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሶስት ሮኬቶች እንደተተኮሱ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።

ህዳር 24 ቀን ፤ 2014 ዓ.ም የሱዳን ሉዓላዊ ም/ቤት መሪ የሆኑት አብድልፈታ አልቡርሃን ከሱዳኑ አልሃዳት ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የሱዳን መንግስት ህወሓትን እንደማይደግፍ የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ ወስዳብናለች ያሉትን መሬት በጦርነት ሳይሆን በውይይት እንደሚፈቱት ተናግረዋል።  

ይህ የትዊተር ፖስትም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበትን የእርስ በርስ ግጭት እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የውዝግብ መቼት መረጃውን ለመፍጠር ተጠቅሞበታል። 

ሀቅቼክ ምስሉን ለመመርመር ባደረገው ጥረት ፎቶውን በአንድ AEROPRESS BG በተባለ የዩቱብ ቻናል ላይ አግኝቶታል። ይህ የዩቱብ ቻናል ከ2ሺህ በላይ ሰብስክራይበሮች ያሉት ሲሆን፣ “የካርጎ ማመላለሻ የነበረው Boeing 747-400 በአፍጋኒስታን ውስጥ ተከስክሷል” የሚል ጽሁፍን አያይዞ በሚያዝያ 22 ፤ 2005 ዓ.ም ይህን ቪድዮ አጋርቶ ነበር።

እንደ Wikipedia መረጃ ከሆነ ይህ Boeing 747-400 የተባለው አውሮፕላን አሁንም ለጭነት ማመላለሻነት እያገለገለ ይገኛል። 

የዚህን ቪድዮ ዝርዝር መረጃን በሚያዝያ 24 ፤ 2005 ዓ.ም በ CNN  ቴሌቪሽን ላይ የሚገኝ ሲሆን እንደ CNN የዜና ሪፖርት መሰረት በአውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ ሰባት አሜሪካኖች ሲሞቱ ስድስቱ ከሚቺጋን አንዱ ከኬንታኪ የመጡ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ዜጎች መሆናቸው ተረጋግጧል። 

የመከስከሱ አደጋ የተፈጠረበት ቦታ በአፍጋኒስታን የሚገኝ እና ቤግራም የተባለ የአሜሪካ የአየር ሀይል ቤዝ ነበር። 

ይህ የትዊተር ፖስትም ምስሉን ከዚህ ቪድዮ ላይ ቆርጦ በመውሰድ ሊጠቀምበት ችሏል። ስለዚህ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።             

Exit mobile version