የተጣሩ መረጃዎች

  ቪድዮው ከትግራይ ክልል የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶችን ያሳያል ?

 ከ13 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ አካውንት፣ “ከትግራይ የተዘረፉ ቅርሶች ለአለም ገበያ በዚህ አይነት ሁኔታ እየተቸበቸቡ ነው።” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ africanews.com ወደተባለ ድረ-ገጽ የሚመራ ሊንክ አጋርቷል

Africanews.com የተባለው ይህ ድረ-ገጽ በየካቲት 7 ፤ 2014 ዓ.ም “Tigray conflict surge in ancient ethiopian relics for sale.” የሚል ርዕስ ያለውን አንድ ቪድዮ አውጥቶ ነበር። 

ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ200 በላይ ግብረመልስ ያገኘ ሲሆን ከ90 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል።  ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት ቪድዮው ከትግራይ ክልል ተዘርፈው በኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ድረ-ገጽ ላይ ለሽያጭ የቀረቡ ቅርሶችን እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የፌስቡክ ፖስቱን ለመደገፍ የቀረበውን ቪድዮ ትክክለኛነት መርምሮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል። 

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።

በጦርነቱ ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ወቅቶች ትላልቅ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ለውድመት የተዳረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትም በጦርነቱ ምክንያት ለወደሙት እድሜ ጠገብ እና ጥንታዊ መስጊዶችን እንዲሁም ቤተክርስትያኖችን ለመጠገን እና ወደቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ቃል ገብቷል።  

የእንግሊዙ ጋዜጣ The independent እንደዘገበውነ e-bay የተባለው የመገበያያ ድረ-ገጽን ጨምሮ በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከቤተ-ክርስትያኖች የተዘረፉ እንደሆኑ የሚገመቱ ቅርሶች ለሽያጭ እየቀረቡ እንደሆነ ዘግቧል።

E-bay የተባለው የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ድረ-ገጽ ለሽያጭ ቀርበው የነበሩ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶችን ከገጹ ላይ ያወረደ ቢሆንም አሁንም ድረስ አንዳንድ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የሆኑ ቅርሶች በዚህ ድረ-ገጽ ላይ ለሽያጭ ቀርበው ይገኛሉ።

Africanews.com የተባለው ድረ-ገጽ ባያያዘው ቪድዮ ላይ “ከአንድ አመት በላይ በፈጀው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ቅርሶች መካከል ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠሩ የብራና ላይ ጽሁፎች በጥቂት ዶላሮች  ዋጋ በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ እየቀረቡ ነው” በማለት ይናገራል።

እነዚህ ለሽያጭ የቀረቡት ቅርሶች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ ቅርሶች ሊሆኑ እንደሚችሉም ይህ የዜና ድረ-ገጽ ይዘግባል።

ሀቅቼክ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት በፌስቡክ ፖስቱ ላይ የተያያዘው ቪድዮ ለመጀመርያ ጊዜ የታተመው በህዳር 14 ፤ 2014 ዓ.ም ከ4.5 ሚልዮን በላይ ተከታይ ባለው አንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ነበር።

ይህ የዩቲዩብ ቪድዮም “ተዘርፈው የነበሩ 13 ጥንታዊ ቅርሶች ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።” የሚል ርዕስ የቀረበ ነበር። 

ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ቪድዮ ከ5000 ጊዜ በላይ ታይቷል።

የተለያዩ ጥንታዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ክልል እንደተዘረፉ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም የፌስቡክ ፖስቱም ሆነ የድረ-ገጹ ቪድዮ መረጃውን አያረጋግጥም።

በዚህም መሰረት፣ መረጃውን ለመደገፍ ከፖስቱ ጋር የተያያዘውን ቪድዮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

ሀሰት፡ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከእስር አልተፈታም

አንድ የፌስቡክ አካውንት የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ እና መስራች የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከእስር ተፈቷል በማለት የካቲት 8 ፤ 2014 ዓ.ም አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ የሚያሳየው ይህ ከፖስቱ ጋር የሚዘዋወረው ምስል፣ “ወንድማችን ዮናስ ወልደየስ እንዳሳወቀን ታምራት ነገራ ከእስር ተፈቷል። ሰዎች ያለጥፋታቸው መታሰር መቆም አለበት” በሚል መግለጫ ተጋርቷል።

 

ታምራት ነገራ በታህሳስ 1 ፤ 2014 ዓ.ም ከቤቱ በድንገት ተወስዶ ከታሰረ በኋላ ለሳምንት ያክል ያለበት ቦታ አልታወቀም ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ታህሳስ 7 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረብ ችሏል።  

እስሩን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጋዜጠኛውን ኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘው የገላን ፖሊስ ጣቢያ አዘዋውሮታል።   

በመጨረሻም የጋዜጠኛው ጉዳይ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሸጋገር በፍርድ ቤቱ በመወሰኑ ሌላ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳያስፈልግ ሆኗል። 

በየካቲት 8 ፤ 2014 ዓ.ም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህዳር ወር ላይ ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል።  

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል

ይህ መረጃም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖስት የተደረገው በነሃሴ 1 ፤ 2013 ዓ.ም ታምራት ነገራ በሚል  አንድ የፌስቡክ አካውንት ላይ ነበር።

ከዚያም በኋላ ይህ ምስል በቅርቡ በየካቲት 7 ፤ 2014 ዓ.ም “ነገ በተጠራው ልዩ የፓርላማ ስብሰባ SOE የሚነሳ ከሆነ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ጨምሮ ሌሎች በአዋጁ ምክንያት የታሰሩ በሙሉ ከእስር ይለቀቃሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው።” በሚል ትዊት ላይ ተጋርቶ ነበር። 

በተጨማሪም ሀቅቼክ የታምራት ነገራን ቤተሰብ ደውሎ ያነጋገረ ሲሆን ጋዜጠኛው እስካሁን ከእስር እንዳልተፈታ ማረጋገጥ ችሏል። 

ይህም በመሆኑ፣ ታምራት ነገራ እንደተፈታ ተደርጎ የቀረበውን የፌስቡክ ፖስት ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።   

ሀሰት፡ ምስሉ በራያ ግንባር የተማረኩ መሳሪያዎችን አያሳይም

ከአንድ ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የቴሌግራም ቻናል “በዛሬው ዕለት በራያ ግንባር በጀግኖቻችን ከትግሬ ወራሪ ሃይል የተማረከ መሳርያ” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ ጥር 27 ቀን ፤ 2014 ዓ.ም ላይ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የቴሌግራም ፖስቱ ከ6700 በላይ ዕይታን አግኝቷል።   

ከ17ሺህ በላይ ተከታይ ያለው ሌላ የፌስቡክ ገጽ ተመሳሳይ ይዘት ካለው ፅሁፍ ጋር አንዱን ምስል አጋርቶት ነበር። ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ800 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ100 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ፅሁፉን ለመደገፍ የቀረቡትን ምስሎች ትክክለኛነት መርምሮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል። 

  

በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል በማስወጣት በአፋር እና አማራ ድንበር አካባቢዎች ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።

የፌዴራል እና የክልል ልዩ ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በኋላም የህወሓት ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል አፈግፍገዋል። ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ እንደሚቆዩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ህወሓት የአማራ እና አፋር ሚሊሽያዎች በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረጉብኝ ነው ሲል ወቀሳውን አቅርቦ ነበር።

ሀቅቼክ ምስሎቹን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሎቹን በአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን የዩቲዩብ ቻናል ላይ ጥር 25 ፤ 2014 ዓ.ም በቀረበ የዜና ቪድዮ ላይ አግኝቷቸዋል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የዩቲዩብ ቪድዮው ከ150ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል። 

የመጀመርያው ምስል በዜና ቪድዮው በ23ተኛ ደቂቃ ከ05 ሴኮንድ ላይ ይገኛል   

 

 

ሁለተኛው ምስል በዜና ቪድዮው በ22ተኛ ደቂቃ ከ57ተኛ ሴኮንድ ላይ ይገኛል 

 የዜና ቪድዮው፣ “በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ጥምር ሃይል አማካኝነት በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደው ርምጃ ከ100 በላይ የሚሆኑ አባላቱ ተደምስሰዋል” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በቪድዮው ተማረኩ ያላቸውን የሽብር ቡድኑን አባሎች ያሳያል። 

በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፖስቱ ጋር የተያያዙትን ምስሎች ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል። 

አታላይ፡ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሽልማት ዕድል አላቀረበም

Safaricom Ethiopia በተባለ እና ከ16,000 በላይ ተከታይ ባለው የቴሌግራም ቻናል አንድ መልዕክት በሰፊው ሲዘዋወር ሀቅቼክ የተመለከተ ሲሆን መልዕክቱ ሰዎች የቴሌግራም ቻናሉ አባል እንዲሆኑና ሌሎችንም የቻናሉ አባል እንዲሆኑ እንዲጋብዙ ይናገራል። በዚህም መሰረት፣ “አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ወደቻነሉ ጋብዞ ያመጣው ሰው 80,000 ብር የሚያወጣ አፕል ላፕቶፕ ተሸላሚ ሆነ” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

መልዕክቱ በተጨማሪም ሰዎች የቴሌግራም ቻናሉን እንዲቀላቀሉ በመጋበዝ ሌሎችም ተመሳሳይ ላፕቶፖችን እና iPhone 13 Pro Max የሞባይል ስልክ ቀፎዎችን መሸለም የሚችሉበት እድል እንዳለ ይናገራል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ መልዕክቱ ከ58,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደርሷል።

ሀቅቼክ መልዕክቱን በመመርመር የማጭበርበሪያ (የማታለያ) መንገድ (SCAM) እንደሆነ አጣርቷል።  

ተመሳሳይ ይዘት ያለውና ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ሌላ የፌስቡክ ገጽም ይህን መልዕክት አጋርቶት ነበር። ይሁን እንጂ ገጹ ቀደም ብሎ በጥር 2012 ዓ.ም በሌላ ስም ተከፍቶ የነበር ሲሆን በኋላ ላይ በጥር 5 ፤ 2014 ዓ.ም ስሙን ቀይሯል። ይህ የሚያሳየው የፌስቡክ ገጹ ለሌላ አላማ የተከፈተ እንደነበርና አሁን ስሙን ወደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በመለወጥ እያዘዋወረ ላለው መልዕክት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር አላማ እንዳለው ያስረዳል ነው። 

በግንቦት 13 ፤ 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የገንዘብ ሚኒስቴር የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት እንዲሳተፉ ጨረታ አውጥቷል

በተፈጠረው የቴሌኮም ፕራይቬታይዜሽን እድል አሸናፊ በመሆን ሳፋሪኮም ፣ የቮዳኮም ግሩፕ ፣ የቮዳፎን ግሩፕ እና የሱሚቶሞ ግሩፕ በጥምረት በመሆን በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት አንዲሰጡ ፍቃድ ማግኘት ችለዋል።

በዚህም መሰረት ግንቦት 14 ቀን ፤ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለኬንያው ሳፋሪኮም እና ለጃፓኑ ሱሚቶሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩበትን ፍቃድ ሰቷቸዋል። 

በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ብሩክ ታዬ እንደገለፁት፣ ቮዳኮም ፣ ቮዳፎን ፣ እና የእንግሊዝ ልማት እና ፋይናንስ ኤጀንሲ (CDC)ን የሚያጠቃልለው የጋራ ስምምነት ፍቃዱን ለማግኘት እስከ 850 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ከፍለዋል። 

የአገልግሎት ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎም ሳፋሪኮም ሰፊ የማስታወቂያ፣ የሰው ኃይል ቅጥርና የተለያዩ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል። የቴሌግራም መልዕክቱም ይህን የብዙዎች ትኩረት ያገኘውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰፊው በመዘዋወር ላይ ይገኛል። 

ሀቅቼክ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ስለጉዳዩ ያናገረ ሲሆን ድርጅቱ የቴሌግራም ቻናል ያለው ቢሆንም ምንም አይነት የሽልማት ፕሮግራም እንደሌለውና የሚዘዋወረው የቴሌግራም ቻናል የድርጅቱ እንዳልሆነ መረዳት ችሏል።     

የድርጅቱ ይፋዊ የማህበራዊ ሚድያ ገፆችም  ፌስቡክ ፣ ቴሌግራም ፣ ትዊተር ፣ ኢንስታግራም እና ሊንኪድን  እንደሆኑ ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጽሁፉን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የተቀነባበረ ሲሆን፣ ከጀርባ ያለው ምስል እና የሳፋሪኮም ምልክት ያለበት ሱቅ በኬንያ የሚገኘው የድርጅቱ መሸጫ እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሚል ስም በተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ ላይ እየተዘዋወረ ያለውን መልዕክት ሀቅቼክ የማጭበርበርያ (የማታለያ) መንገድ (SCAM) ብሎታል።                      

ሀሰት: ምስሉ በበራህሌ ግንባር በአፋር ህዝባዊ ሰራዊት የተያዘን የጦር መሳሪያ አያሳይም

ከአንድ ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የቴሌግራም ቻናል በጥር 23 ፤ 2014 ዓ.ም “የአፋር ህዝባዊ ሰራዊት በዛሬው ዕለት በበራህሌ ግንባር ገቢ ያደረገው የጦር መሳርያ” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የቴሌግራሙ ፖስት  ከ12000 ጊዜ በላይ መታየት የቻለ ሲሆን ሌሎች ከ46 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው የቴሌግራም ቻናሎችም አጋርተውታል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል በማስወጣት በአፋር እና አማራ ድንበር አካባቢዎች ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።    

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጦር ግንባር በመገኘት ጦሩን ለመምራት መወሰናቸውን እስካስታወቁበት ጊዜ ድረስ የህወሓት ሃይሎች ከአዲስ አበባ 183 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረሲና ከተማ ድረስ ገፍተው መጠጋት ችለው ነበር። 

የፌዴራል እና የክልል ልዩ ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በኋላም የህወሓት ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል አፈግፍገዋል። ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ እንደሚቆዩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ህወሓት የአማራ እና አፋር ሚሊሽያዎች በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረጉብኝ ነው ሲል ወቀሳውን አቅርቦ ነበር።

በጥር 16 2014 ዓ.ም የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው “የህወሓት ሃይል በአፋር ክልል የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል በሚያስብል ሁኔታ በኪልባቲ እና ራሱ ዞን ፤ በአብ አላ እና መጋሌ ወረዳዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል።

ይህ የቴሌግራም ፖስትም ይህን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ሀቅቼክ የፖስቱን ትክክለኛነት ለማጣራት የጉግል ግልባጭ ምስል ፍለጋን ተጠቅሞ ያደረገው የፍለጋ ውጤት እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሃሴ 30 ፤ 2013 ዓ.ም ጎልጉል (Goolgule) በተባለ ድረገጽ ላይ “ባጠናቀቅነው የሰኔ ወር በቁጥጥር ስር የዋሉ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች” በሚል ርዕስ ከቀረበ ፅሁፍ ጋር የተያያዘ ነበር።  

በአፋር ድንበር አካባቢ ግጭቶች እንዳሉ የሚሰማ ቢሆንም ምስሉ በአፋር ሚሊሻዎች አማካኝነት በበራህሌ ግንባር የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን አያሳይም። 

በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፓስቱ ጋር የተያያዘውን ምስል ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

ሀሰት፡ ምስሉ በአፋር ሀይሎች የተያዙ የጦር መሳርያ ጥይቶችን አያሳይም

 አንድ የፌስቡክ ፖስት ከ62,560 በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተለጠፈበት ከጥር 17 ፤ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ50 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። የፌስቡክ ገጹ አብዛኛውን ጊዜ የአፋር ጉዳዮች ላይ የሚተነትን ሲሆን የፌስቡክ ፖስቱም ከ 1200 በላይ ግብረ መልሶችን ማግኘት ችሏል።

ከፖስቱ ጋር የተያያዘው ምስል በቁጥር በዛ ያሉ ጥይቶችን የሚያሳይ ሲሆን በአማርኛ የተያያዘው ጽሁፍ፣ “ጁንታው ማስረከብ ጀምረዋል አፋርም መረከብ ጀምረዋል። በሰሜናዊ ግንባር ህወሓትን በራሱ መሳርያ እየማረከ ድል ማድረጉን እየቀጠለ ነው” የሚል ነው። 

የፌስቡክ ፖስቱ ጁንታው ብሎ የሚጠራው የትግራይ ተዋጊ ሀይሎችን ሲሆን አፋር ደግሞ የትግራይ አጎራባች ክልል ነው። እንደሚታወቀው የአፋር ልዩ ሀይሎች እና ሚሊሽያ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመጣመር ከህወሓት ጦር ጋር ውጊያ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የፌስቡክ ፖስቱ የጥይት ምስሎችን ያሳይ እንጂ ምስሉ የቆየ እና አሁን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ግጭት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ስለዚህ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል። 

ጦርነቱ የጀመረው በጥቅምት 2013 ዓ.ም የህወሓት ሀይሎች በትግራይ ሰሜን ዕዝ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ሲሆን ይህ ጦርነት ሶስት ሃገራቶችን ማለትም ኢትዮጵያ ኤርትራ እና ሱዳንን ሲጎዳ በሌላ በኩል ደግሞ በዋነኝነት ሶስት ክልሎችን ማለትም ትግራይ አማራን እና አፋርን ጎድቷል።

የፌደራሉ መንግስት በብሄራዊ መግባባት እና አንድነት ላይ የሚያተኩር አገር አቀፍ ውይይት ላይ ያለውን ፍላጎት ያስታወቀ ሲሆን በቅርቡም የፌደራሉ መንግስት የህወሓት አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ክስ አቋርጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፋር ክልላዊ መንግስት  የህወሓት ሃይሎች ተከታታይ ጥቃት እያደረሱበት እንደሆነ አስታውቋል።    

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት የጉግል ግልባጭ የምስል ፍለጋን ተጠቅሞ ያደረገው ፍለጋ ውጤት የሚያሳየው ምስሉ ከፈረንጆቹ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ጽሁፎች ላይ አብሮ ታትሟል። ከዚህም በተጨማሪ ምስሉ በነሃሴ 2006 ዓ.ም በAMISOM (African Union Mission in Somalia) አማካኝነት የተያዘ መሳሪያን እንደሚያሳይ ሀቅቼክ አረጋግጧል። በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፓስቱ ጋር የተለጠፈውን ምስል ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

አሳሳች፡ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስቷል?

ሬውይተርስ በጥር 18 ፤ 2014 ዓ.ም ባወጣው የዜና ሪፖርት፣ “የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ከውሳኔ ላይ ደርሷል” የሚል ርዕስ በድረ ገጹ ላይ አንድ ጽሁፍ አስነብቦ ነበር።” ይሁን እንጂ ሀቅቼክ መረጃውን ሚንስትሩ ከሰጠው መግለጫ ጋር በማመሳከር ዜናውን አሳሳች ብሎታል። 

በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በህወሓት እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን ድረስ ቀጥሏል። የፌደራሉ መንግስት በሰኔ 2013 ከመቀሌ እና ከክልሉ አካባቢዎች ለቆ ከወጣ በኋላ የህወሓት ሃይሎች እራሳቸውን በማጠናከር በአማራ ክልል በምትገኘው የደብረሲና ከተማ ድረስ በመምጣት መቆጣጠር ችለው ነበር። 

ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች መስፋፋቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በመላው ሃገሪቱ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ እና ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስራ ላይ አውሎ ነበር። 

ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በህወሓት ሃይሎች ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃን በመውሰድ ተቀጣጥረዋቸው ከነበሩት የአማራ እና አፋር ክልሎች አስወጥቷቸዋል። ከመጀመርያው ዘመቻ መጠናቀቅ በኋላ የፌደራል እና ሌሎች የክልል ልዩ ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡ እና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ በተጠንቀቅ እንዲቆዩ መንግስት ማዘዙን አስታውቋል።    

በቅርብ መንግስት ጃዋር መሀመድ፣ ስብሃት ነጋን እንዲሁም ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር ፈቷል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ጦርነቱን ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ለድርድር እየተዘጋጀ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። 

የኢፌዲሪ የሚንስትሮች ምክር ቤት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቋረጥ ጥር 18 ቀን  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አስተላልፏል። 

ይህ የሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ ሬውተርስ የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ አስተላልፏል የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ሁኔታውን አጣርቶ አሳሳች ብሎታል። 

የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የውሳኔ ኃሳብ ቢያቀርብም ኃሳቡ ላይ በመወያየት ውሳኔውን ሊያፀድቅ የሚችለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ምክር ቤቱ ሰነዱ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መርቶታል።  

ጥቅምት 23 ፤ 2014 ዓ.ም የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ከሆነ የአስቸኳይ አዋጁ ከመጠናቀቁ በፊት ማንሳት እንደሚችል አስቀምጧል። 

ይህም በመሆኑ ሀቅቼክ የዜና ሪፖርቱ ያቀረበውን መረጃ ሚንስትሩ ከሰጠው መግለጫ ጋር በማመሳከር ዜናውን አሳሳች ብሎታል። 

ሀሰት፡ ምስሉ በድሮን ጥቃት የደረሰበትን የጭነት መኪና አያሳይም

ከ45 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በታህሳስ 29 ፤ 2014 ዓ.ም “ዛሬም በሁመራ ግንባር አሸባሪው ሐይል በአሉን መሰረት አድርጎ ትንኮሳ ፈጽሞ ነበር። የማትታየው በላይነሽ ጠብሳው ወደከሰልነት ቀይራው ተመልሳለች።” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይህን ምስልም ሌሎች የፌስቡክ ገጾች ሲያዘዋውሩት ነበር።

ይሁን እንጂ ምስሉ በድሮን ጥቃት የደረሰበትን የጭነት መኪና ስለማያሳይ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል። 

በኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግስት እና በህወሓት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ ዓመት በላይ አሳልፏል። የፌደራሉ መንግስት ለ7 ወራት ያክል መቀሌን ተቆጣጥሮ ከቆየ በኋላ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ በሰኔ 2013 መጨረሻ አካባቢ ጦሩን ከአብዛኛው የክልሉ ቦታዎች አስወጥቷል። ነገር ግን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በህወሓት ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት አልቻለም ነበር። ከዚያም በኃላ የህወሓት ሃይሎች ወደ አፋር እና አማራ አጎራባች አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጥቃት ፈጽመዋል። 

በህዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦሩን በግምባር በመሆን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ አብዛኛው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ነጻ ወተዋል። ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች ተሸንፈው ሳይሆን ተቀጣጥረዋቸው ከነበሩ አካባቢዎች ለሰላም ድርድር እድልን ለመስጠት በሚል ማፈግፈጋቸውን አስታውቀዋል። በተቃራኒው የፌደራሉ መንግስት የህወሓት ሃይሎች ተሸንፈው እንጂ እነሱ እንደሚናገሩት አፈግፍገው እንዳልሆነ ተናግሯል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የመጀመሪያው ምዕራፍ ዘመቻ መጠናቀቁን ተከትሎ የፌደራሉ ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡ እና ይልቁንም ያስለቀቋቸውን ቦታዎች ይዘው እንደሚቆዩ አስታወቀዋል።  

ይሁን እንጂ የፌደራሉ መንግስት እና ጥምር ሃይሎች በተለያዩ ግንባሮች ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት ሙከራ እንዳደረጉ ክስ ሲቀርብባቸው የቆዩ ሲሆን የህወሓት ህይሎች ደግሞ በበኩላቸው ራሳቸውን በመከላከል የመልሶ ማጥቃት ዕርምጃ እንደወሰዱ ተናግረዋል። ይህ የፌስቡክ ፖስትም በዚህ ሃሳብ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

በመኪኖቹ መካከል በአይን በግልጽ ከሚታዩት ልዩነቶች በተጨማሪ ሀቅቼክ የወደመውን የጭነት መኪና ትክክለኛነት ለማጣራት የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ዘዴን ተጠቅሟል። 

ትክክለኛ ምስል 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ በታህሳስ 17 ፤ 2014 ዓ.ም ከ#nomore-Ethiopia የተባለ ድህረገጽ ላይ የተገኘ ሲሆን ህወሓት የኮምቦልቻ ከተማን ተቀጣጥሮ በነበረበት ወቅት ያወደመው መኪና እንደሆነ ድህረገፁ ይገልጻል። ስለዚህ የፌስቡክ ፖስቱን ለመደገፍ የቀረበው ምስል ትክክለኛ ስላልሆነ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።

ሀሰት፡ ምስሉ የህወሓት ሃይሎች ዘርፈው የሄዱትን እቃዎች አያሳይም

ከ41ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ በታህሳስ 1 ፤ 2014 ዓ.ም “የህውሃታውያንን ቁራሊዮ ናቸው ስንል አንድም ቀን አልተሳሳትንም። ይሄው የዘረፉትን ኮተት ይዘው ሲሄዱ ተይዘዋል…”። የሚል ገላጭ ጽሁፍ በመጠቀም አንድ ምስል አያይዞ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ከ50 ጊዜ በላይ ሲጋራ ከ240በላይ ግብረ መልስ አግኝቷል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም አንስቶ በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት ቀጥሏል። በግንቦት 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ ሁሉንም የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ ዋና ዋና ቦታዎች አስወጥቷል። 

ከዚያ በኋላ የህወሓት ሃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር ወደክልሉ ደቡባዊ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ አጎራባች በሆኑት የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በሕዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦርነቱን በግምባር ሆነው ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የተለያዩ የማጥቃት እና የመልሶ ማጥቃት የጦርነት ዜናዎች እየተሰሙ ይገኛልሉ። 

በህዳር 29 ፤ 2014 ዓ.ም የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኮምቦልቻ እና ደሴ አካባቢ ያሉ የእርዳታ ምግብ እና ቁሳቁስ መጋዘኖች በመዘረፋቸው የምግብ እርዳታ ስርጭት ማቆሙን ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፈን ዱያሪክ በህዳር 29 ረቡዕ ዕለት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ አካባቢ ብዛት ያለው ለዕርዳታ የሚውሉ የምግብ አቅርቦቶች እንዲሁም በምግብ ዕጥረት ለተጎዱ ህጻናት ሊሰራጭ የተዘጋጁ አልሚ ምግቦች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል። 

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።    

ሀቅቼክ ምስሉን ለማጣራት የጎግል ተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋን የተጠቀመ ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው በጥር 8 ፤ 2011 ዓ.ም sapeople.com በተባለ ድህረ-ገጽ ላይ “SA Mentality? Over 1,600 Lives Lost on South Africa’s Roads Over Christmas Period” በሚል ርዕስ ስር በቀረበ ጽሁፍ ላይ ነበር። 

ከዚህ በተጨማሪ በፎቶሾፕ የተቀነባበሩ ምስሎችን ከምንለይባቸው መንገዶች አንዱ ምስሉን በትኩረት በመመልከት የተጋነኑ የቀለም ልዩነቶችን ፣ የምስሎቹ ጠርዝ መፈዘዝ ከታየበት ፣ ጥላ እና በግልጽ የሚታይ የመጠን ልዩነቶች ምስሉ የተቀነባበረ ለመሆኑ ማሳያ ሲሆኑ ይህም ምስል በፎቶሾፕ ለመቀነባበሩ እንደማሳያ መሆን የሚችለው የመኪናው የታርጋ ቁጥር የቀለም ግነት ነው።

 

ምንም እንኳን የህውሓት ሀይሎች በተለያዩ ከተሞች ዘረፋ እንደፈጸሙ ቢዘገብም  “የህወሓት ሃይሎች ያገኙትን እቃ እየጫኑ እየዘረፉ ነው” በማለት የተጋራው ምስል ሀሰት ነው። 

አሳሳች ርዕስ ፡ ከአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራና ኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ አይደሉም

ከ4 ሚሊየን በላይ ተከታይ ያለው የፊስቡክ ገጽ በሕዳር 30 ፤ 2014 ዓ.ም “ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ ኤርትራና ኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆኑ” የሚል ርዕስን በመጠቀም በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ450 በላይ ግብረመልስን ሲያገኝ ከ21 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። ሀቅቼክ ገጹ የተጠቀመው ርዕስ ከጽሁፉ ይዘት ጋር ስለሚለያይ አሳሳች ርዕስ ብሎታል።    

 

በአለም ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን ከጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው አለም-አቀፍ ኮሚቴ Committee to protect journalist (CPJ)  በያዝነው አመት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በ2021 በመላው አለም የታሰሩ የጋዜጠኞች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደጨመረ በአንድ ሪፖርቱ ላይ አስነብቦ ነበር። 

በ2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ እንዲሁም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከሃገር የተሰደዱ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በተከፈተው አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

ይህንንም ተከትሎ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች ከእስር እንደተለቀቁ ይታወሳል። በፈረንጆቹ 2018 ኢትዮጵያ ከብዙ አመታት በኋላ ምንም አይነት ጋዜጠኛ ለእስር ያልተዳረገባት ሀገር ሆና መመዝገብ የቻለች ሲሆን ከዚያ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ ምንም አይነት በእስር ላይ ያለ ጋዜጠኛ ያልነበረው በፈረንጆቹ 2004 ነበር። 

reference: https://theatlas.com/charts/r1yRA3yxV  

Committee to protect journalist (CPJ) ባወጣው ሪፖርት መሰረት እስከ ሕዳር 22 ፤ 2014 ዓ.ም ድረስ በመላው ዓለም በአጠቃላይ 293 የሚሆኑ ጋዘጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። በወጣው ጥናት መሰረት ቻይና 50 ጋዜጠኞችን በማሰር የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ 25 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም 3ተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ከአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያው ሆናለች። ጎረቤታችን ኤርትራ 16 ጋዜጠኞችን በማሰር የ7ተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ 9 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም 11ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ነገር ግን የፌስቡክ ፖስቱ፣ “ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆኑ”የሚል ርዕስ ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ የተያያዘውን ማስፈንጠርያ በመከተል የሪፖርቱን ይዘት ስንመለከት፣  Committee to protect journalist (CPJ) ባወጣው ጥናት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ የቀዳሚነቱን ደረጃ እንደያዘች ያስነብባል። አያይዞም ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ የሚዲያ ነጻነት መፍትሄ የሚሻ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ገልጿል። በፈረንጆቹ 2018 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በሚዲያ ነጻነት ላይ ጉልህ ለውጦችን የታዩ ቢሆንም በ2021 ደግሞ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት መካከል ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ደረጃን የያዘ መሪ እንደሆነ ያስነብባል።    

በአፍሪካ ውስጥ ካሉት 54 ሃገራቶች መካከል ከሰሃራ በታች ያልሆኑ ሃገራት በሰሜኑ የአህጉሪቱ አካባቢ የሚገኙት እንደ አልጄሪያ ፣ ግብጽ ፣ ሊቢያ ፣ ሞሮኮ  እና ቱኒዚያ ሲሆኑ የቀሩት 49 የሚሆኑት የአፍሪካ ሃገራት ከሰሃራ በታች የሚገኙ ናቸው።

ስለዚህ በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተመለከተው ርዕስ በጽሁፉ ውስጥ ካለው ይዘት ጋር ሲለሚለያይ ሀቅቼክ አሳሳች ርዕስ ብሎታል።      

Exit mobile version