ይህ ቪዲዮ በቅርቡ የተመረጡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ዲቪ ያደረጉትን ንግግር ያሳያል?

በቅርቡ በDiversity Visa (ዲቪ) ላይ የሚጣሉ ገደቦችን በተመለከተ የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን የሚያሳይ ቪዲዮ በቲክቶክ ላይ በመሰራጨት ላይ ይገኛል። ይህ ቪድዮ በቅርብ ከተካሄደው የ(ዲቪ) 2026 ፕሮግራም ጋር በማያያዝ የቀረበ ነው።


ከቲክቶክ ቪድዮው ላይ የተወሰደ ምስል

ነገር ግን ሀቅቼክ ይህን ቪዲዮ በፈረንጆቹ 2017 ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዲቪ ፕሮግራምን ለማቋረጥ ያላቸውን ፍላጎት የገለፁበት ንግግር ሆኖ አግኝተነዋል።

ከNBC News (ኤንቢሲ ኒውስ) ዩቲዩብ ገጽ ቪድዮ ላይ የተወሰደ ምስል

NBC News ፖለቲካን ፣ ንግድን ፣ ጤናን ፣ ሳይንስን እና ባህልን ጨምሮ አጠቃላይ ሀገራዊ እና አለም አቀፍ ዜናዎችን የሚያቀርብ በአሜሪካ የሚገኝ ታዋቂ የዜና ድርጅት ነው። ይህ የዜና ተቋም በድህረ ገጽ ፣ በቲቪ ስርጭቶች እና በዲጂታል መድረኮች የተለያዩ ይዘቶችን ያቀርባል ፣ ይህም ተመልካቾች በቅርብ ወቅታዊ ትኩስ ዜናዎች ፣ ጥልቅ ትንታኔ እና ልዩ ዘገባዎች እንዲያገኙ ያደርጋል።

ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በስደተኞች ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም ይታወቃሉ። ብዙውን ጊዜ ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር እርምጃዎችን እና የኢሚግሬሽን ፕሮግራሞች ላይ ገደቦችን ይጥላሉ። የዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ ጉዳይን በተመለከተ ትራምፕ ፕሮግራሙን በመቃወም ለሃገሪቷ ደህንነት ስጋት ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ እና የአሜሪካን ጥቅም ማስከበር አልቻለም ብለው ተችተዋል።

በዳይቨርሲቲ ቪዛ ፕሮግራም ላይ የሰነዘሩት ትችት የአመልካቾችን የማጣራት ሂደት እና ተጠቃሚዎችን በመምረጥ ረገድ ብቃትን መሰረት ያደረገ መስፈርት አለመኖሩን ያነሳል።

ከTime (ታይም) ድህረ ገጽ ቪድዮ ላይ የተወሰደ ምስል

ትራምፕ በዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ ላይ ያላቸው አቋም በፖለቲካ ዘመናቸው ሁሉ አከራካሪ የነበረ ሲሆን አንዳንዶች ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል የኢሚግሬሽን ገደቦችን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ሲደግፉ ፣ ሌሎች ደግሞ የአሜሪካ መንግስት ለረጅም ጊዜ ስትደግፍ የኖረችውን የብዝሃነት እና የመደመር እሴቶችን የሚጎዳ አድርገው ይመለከቱታል።

የዚህ ቪዲዮ አሳሳች ባህሪ በቅርቡ የተደረገ ንግግር መሆኑን በውሸት በመግለጽ መረጃን ስለመጠቀም እና በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ስጋትን ይፈጥራል።

አሳሳች ልጥፎች በስደተኞች ላይ ጎጂ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ይዘት ስለ ኢሚግሬሽን ፖሊሲዎች እና ወደ አሜሪካ ለመሰደድ ለሚፈልጉ ግለሰቦች የተሳታቱ መረጃዎችን ያጋራል። 

ይህ የተሳሳተ መረጃ በማህበራዊ ሚድያ ላይ በቀላሉ ሊስፋፋ በሚችልበት በዚህ ወቅት እውነትን መፈተሽ እና ምንጮችን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። 

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አማካኝነት ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ሀሰት/አሳሳች መሆኑን አረጋግጧል።

Exit mobile version