ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን በሀገር ውስጥ ማተም ልትጀምር ነው?

እንደ ዩቲዩብ ባሉ የኦንላይን መድረኮች ላይ ከዘጠኝ ሺህ በላይ እይታዎች እንዲሁም በቲክቶክ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ እይታዎችን በማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለው ይህ ቪዲዮ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቅ መሠረተ ልማት ለመገንባት ከጃፓን ኩባንያ TOPPAN GRAVITY ጋር ስምምነት መፈራረሟን ይገልፃል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ቪዲዮ በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን ሀገር ውስጥ ማትም እንደሚያስችላት ይናገራል።

ሊንክ

ቪዲዮው መግለጫውን ለመደገፍ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትን እና የTOPPAN GRAVITY አስተዳዳሪዎችን ምስል ከቪዲዮው ጋር በማያያዝ ተጠቅሟል።

ሊንክ

ነገር ግን ሀቅቼክ መረጃውን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ስምምነቱ ለገንዘብ ህትመት ሳይሆን እንደ ፓስፖርት ፤ ብሄራዊ መታወቂያ ፤ ኤቲኤም ካርዶች ፤ የማስተርካርድ ምርቶች እና ሌሎች የመንግስት ሰነዶችን የመሳሰሉ ከፍተኛ የደህንነት ሰነዶችን ለማምረት እንደሆነ አረጋግጧል። 

በሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው በኢትዮጵያ እና በTOPPAN GRAVITY መካከል የተደረገው ስምምነት ደህንነታቸው የተጠበቀ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፓስፖርት፡  ለዜጐች ደህንነቱ የተጠበቀ የጉዞ አገልግሎት መስጠት ለማስቻል ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ካርዶች፡ የማንነት ማረጋገጫ እና የደህንነት እርምጃዎችን ለማሳደግ ፤ ኤቲኤም ካርዶች፡ ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ፤ ማስተር ካርድ ምርቶች፡ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የክፍያ ግብይቶችን ለማስቻል ሲሆን እነዚህ ሰነዶች በውስጣቸው ማይክሮ ቺፖችን በማካተት ደህንነታቸውን እና ትክክለኛነትን የበለጠ እንዲያሳድጉ ተደርገው የሚመረቱ ይሆናል።

ከፋና ዘገባ በተጨማሪ TOPPAN GRAVITY በድህረ-ገጹ ስለ ስምምነቱ እንደገለፀው “በኢትዮጵያ የሚገነባው የህትመት ፋብሪካ እንደ መጀመሪያ እርምጃ የቶፓን ግሩፕ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኢትዮጵያ የተሟላ አቅርቦት አቅም ለመፍጠር አቅዷል። ለወደፊቱ ለኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች መታወቂያ እና ፓስፖርት በማምረት በአፍሪካ ገበያ መፍትሄዎችን ይዞ የመምጣት ትልቅ ሃሳብ እንዳለውም ጠቁሟል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የፓስፖርት እና የመታወቂያ ደንቦችን በማውጣት ከአካባቢው ፍላጎቶች ጋር የተጣጣመ የአሰራር ዲዛይን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል።”

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ገንዘብ ማተምን እንደማይጨምር ለሀቅቼክ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ለውጥ ስታደርግ ከተለያዩ የገንዘብ ማተሚያ ድርጅቶች ጋር ስምምነቶችን ተፈራርማለች። ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት የገንዘብ ኖት ላይ  የተለያዩ ለውጦችን ብታደርግም፣ ስለ ገንዘብ ህትመት ይህን ያህል ሰፊ መረጃ ማግኘት ቀላል አይደለም።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ካደረገችው የገንዘብ ኖት ቅያሪ ባለፈ በታሪክ ባለፉት ዓመታት በርካታ ግዜ የገንዘብ ኖት ለውጦችን አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ጉዞ በ1895 ዓ.ም ሲጀምር ፣ 200,000 ዶላር ዋጋ ያለው አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ሥርዓት በ1886 ዓ.ም  በፓሪስ ሚንት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደተመረተ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የባንክ ኖቶች ወይም የወረቀት ገንዘቦች በ1907 ዓ.ም በአቢሲኒያ ባንክ ነበር የተዋወቁት ፣ ይህም ሳንቲሞችን እንደ መገበያያ ከመጠቀም ባሻገር የተደረገ ለውጥ ነው ። የአቢሲኒያ ባንክ በ5፣ 10 ፣ 100 እና 500 ዋጋ የመጀመሪያዎቹን የባንክ ኖቶችን አስተዋቆ ነበር።

በህዳር ወር 1990 ዓ.ም በሃገሪቱ ስልጣን ላይ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በደርግ ዘመን የነበረው ገንዘብ ላይ ጥቃቅን ለውጦችን እና የቀለም ማሻሻያዎችን አድርጎ ነበር። ከዚህ በተጨረማሪ የከፍተኛ ደረጃ ኖቶች በተለይም የ50 እና 100 ብር ሂሳቦች ላይ የተሻሻሉ የደህንነት ማረጋገጫዎች እና የተለየ ዲዛይንን አካቷዋል።

በመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተሻሻሉ የደህንነት ባህሪያትን እና ሌሎች ልዩ ክፍሎችን የያዘ አዳዲስ የገንዘብ ኖቶች አስተዋውቋል። አዲስ የተዋወቁት የገንዘብ ኖቶች ላይ ከ10 ፣ 50 እና 100 ቢል ኖቶች በተጨማሪ የ200 ብር ኖቶች እንዲቀርቡ ተደርገዋል። 

ምስል

ብሔራዊ ባንክ በግንቦት ወር 2000 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማተሚያ ድርጅቶችን በመጋበዝ ከ1.1 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ለማምረት ጨረታ አቅርቧል።

በ2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁለት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማተሚያ ኩባንያዎች – ጂሴኬ እና ዴቭሪየንት ጂም ኤች (ጀርመን) እና ደላሩ (ዩኬ) – የተለያዩ የኢትዮጵያ ብር ኅትመቶችን ለማተም የብዙ ሚሊዮን ዶላር ውል ሰጥቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። 

ሐምሌ 24, 2005 ዓ.ም በሚዲያዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሱዳን የብር ኖቶችን ለማሳተም እያሰበ እንደሆነ ዘገባዎች ወጥተው የነበረ ሲሆን የባለሙያዎች ቡድንም ወደ ሱዳን በመጓዝ በ1986 የተቋቋመውን የሱዳን ገንዘብ ማተሚያ (ኤስ.ፒ.ፒ.) የተባለውን የግል ድርጅት ጎበኝተዋል። በሪፖርቱ መሠረት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ባለሙያዎች ወደ ሱዳን ሄደው ኤስ.ፒ.ፒ. ማሽኖች እና የኩባንያውን አቅም እንደገመገሙ መረጃዎች ያሳያሉ።

ታህሳስ ወር, 2007ዓ.ም አዲስ ፎርቹን የተባለው ጋዜጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገር ውስጥ ጥሬ ገንዘብ እና በተጨማሪም የተለያዩ የደኅንነት ሰነዶችን ለማተም የሚያስችለውን ማተሚያ ፋብሪካ የማቋቋም ሂደት ላይ እንደሆነ አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን ዶቼ ቬለ መጋቢት 5 ቀን, 2014 ዓ.ም ባወጣው ፅሁፍ መሰረት ኢትዮጵያ ገንዘቧን እንድትታትም ከብሪታኒያ ግዙፉ የብር ኖት ማተሚያ ዴላሩ ጋር ስምምነት እንዳደረግች ገልፆ ነበር።

ምስል

ግንቦት 21 ቀን ,2016 ዓ.ም በወጣው ሌላ ዘገባ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ገንዘባቸውን በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ እንደሚያሳትሙ ተገልጿል። ከዚህ ዘገባ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን ዴላሩ በተባለ የእንግሊዝ አታሚ እንደምታሳትም የሚገልፁ መረጃዎች ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ምንዛሪ ህትመት ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ቢነሱም እስካሁን ከመንግስትም ሆነ ከብሄራዊ ባንክ የተገኘ ይፋዊ መረጃ የለም። ነገር ግን አሁን ላይ ኢትዮጵያ ‘ገንዘብ ማተሚያ ማዕከል’ ልትገነባ ነው እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ሃሰተኛ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በ TOPPAN GRAVITY መካከል የተደረገው ስምምነት የገንዘብ ህትመትን አይጨምርም።

የቪዲዮው አሳሳች መልዕክት የስምምነቱን ወሰን ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ቢችልም መረጃዎችን ከማሰራጨት በፊት ታማኝ ከሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።  ከፍተኛ የደህንነት ሰነዶች ላይ የተደረገውን ስምምነት ብር ለማተም በማለት በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል።

ኢትዮጵያ ከTOPPAN ግራቪቲ ጋር ገንዘብ ለማተም ስምምነት ተፈራረመች የሚለው ቪዲዮ ሀሰት ነው። 

Exit mobile version