ኢትዮጵያ በ2024 በመጸዳጃ ቤት እጥረት ከአለም ቀዳሚ ስፍራ ላይ ትገኛለች?

ከሰሞኑን ከተካሄደው የ2024 የአለማቀፍ የመፀዳጃ ቤት ቀን ጋር በተያያዘ ኢዮጵያን የሚመለከቱ ዘገባዎች የቀረቡ ሲሆን በዚህም አንድ በቴሌግራም ላይ ዜናዎችን የሚያጋራ ቻናል ኢትዮጵያ በመጸዳጃ ቤት እጥረት ከአለም ቀዳሚዉ ስፍራ ላይ እንደምትገኝ የWaterAid (ዋተር-ኤይድ) ሪፖርት ያሳያል በሚል መረጃ አጋርቷል። ነገር ግን ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት በ2024 ይህን መሰል መረጃ በዋተር-ኤይድ ድህረ ገጽ ላይ አልተገኘም ፣ ይህም የዘገባውን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።


የቴሌግራም ዘገባው ከፊል ገጽታ

Africa News (አፍሪካ ኒውስ) ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ2018 ኢትዮጵያ በመጸዳጃ ቤት እጥረት ቀዳሚ ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ሪፖርት ጽሁፍ አውጥቶ ነበር። ይህንንም መረጃ ከዋተር-ኤይድ 2018 አመታዊ ሪፖርት እንዳገኘው ገልጿል። እውነተኛነቱንም ሀቅቼክ ከዋተር-ኤይድ ሪፖርት ማረጋገጥ ችሏል። 

አፍሪካ ኒውስ ከአፍሪካ አህጉር የተውጣጡ ዜናዎችን እና መረጃዎችን ለማህበረሰብ በማድረስ ላይ የሚያተኩር ዲጂታል የዜና መድረክ ነው። እ.ኤ.አ. በ2016 ስራ የጀመረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ፣ ፖለቲካ ፣ ንግድ ፣ ባህል ፣ ቴክኖሎጂ እና ስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ዘገባዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ። ድህረ ገፁ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የማወቅ ፍላጎት ያላቸውን የአህጉሪቷን እና የአለም አቀፍ ታዳሚዎችን ለማስተናገድ የተነደፈ ነው።

ከአፍሪካ ኒውስ ድህረ-ገጽ የተወሰደ ምስል Nov 20,2018

ይህ መረጃ እንዳለ ሆኖ በ2024 በWorldpopulationreview (ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው) የወጣው ዘገባ የተለየ መረጃን ይዟል። በዚህ ወቅታዊ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ የንፅህና አጠባበቅ ሁኔታዋን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ እመርታ በማስመዝገብ በቂ መጸዳጃ ቤት ከሌላቸው 10 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ራሷን በተሳካ ሁኔታ ማውጣት ችላለች።


ከዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ገጽ የተወሰደ ምስል

WorldPopulationReview.com ስለ አለምአቀፍ የስነ-ህዝብ እና የህዝብ ስታቲስቲክስ ዝርዝር ግንዛቤዎችን በማቅረብ ላይ ያተኮረ የዲጂታል መድረክ ነው። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና ይፋዊ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲዎች መረጃን በሚያካትት የመረጃ አሰባሰብ ሂደት ድህረ ገፁ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሀገራት እንደ የህዝብ ብዛት ፣ የእድገት ደረጃዎች እና የከተሜነት ሁኔታዎችን የተለያዩ የስነ-ሕዝብ መረጃዎችን ያቀርባል። መረጃን በግራፎች ፣ ቻርቶች ፣ ትንተና እና ምስላዊ እይታዎች የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ወቅታዊውን የአለም ህዝብ መረጃ እና የስነ-ህዝብ መረጃ ለማቅረብ ቁርጠኛ የሆነ ራሱን የቻለ ለትርፍ የሚሰራ ድርጅት ነው።

ከ2024 ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ድህረ ገጽ የተወሰደ ምስል

ይህ አስደናቂ እድገት መንግሥታዊ ተነሳሽነቶች እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የንጽህና መሠረተ ልማቶችን እና ተግባራትን ለማሳደግ ባደረጉት ትብብር ጥረት የተገኘ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የእነዚህ አካላት የተቀናጀ ጥረት ፍሬ አፍርቶ በሀገሪቱ የንፅህና አጠባበቅ ገጽታ ላይ ተጨባጭ መሻሻል አስገኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘመናዊ እና ፅዱ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት በማለም የ”ፅዱ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት ሚያዝያ 26 ቀን 2024 አስጀመሩ። ይህ ፕሮጀክት በግንባታው ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡን ተሳትፎ አፅንዖት የሚሰጥ እና ለሁሉም ሰው ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ያለመ ነው። ይህ ፕሮጀክት “ንጹህ ከተሞች – ጤናማ ህይወት” በሚል መሪ ቃል የገንዘብ እና የአይነት መዋጮዎችን ማሰባሰብያ ፕሮግራምን ያካትታል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ድህረ ገጽ የተወሰደ ምስል

ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ተግባራዊ ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም በከተማው ውስጥ እስካሁን ተገንብተው የቀረቡት መጸዳጃ ቤቶች ምስክር የሚሆኑ ናቸው። ለእነዚህ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ዘላቂ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለመጠቀም እና ጥራት ያለው የግንባታ አጨራረስን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውንም ቁርጠኝነትን ገልጸዋል። ይህ ፕሮጀክት ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ በ10 ሰአት ውስጥ ብቻ ከ154 ሚሊየን ብር በላይ በዲጂታል ቴሌቶን ገቢ ማግኘቱም ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድህረ ገጽ የተወሰደ ምስል 

Exit mobile version