ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅሟ ከአፍሪካ ሁለተኛ ናት?

የእርስ በእርስ ግጭቶችንና ጦርነቶች እያስተናገደች የምትገኝው ኢትዮጵያ፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተከትሎ የወታደራዊ ወሬዎች ርዕስ እንድትሆን አድርጓታል። ይህን ተከትሎም በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅም ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር እያወዳደሩ የተለያዩ ተንቀሳቀሽ ምስሎችን መልቀቅ እየተለመደ መጥቷል።

ከሰሞኑ በፌስቡክ ላይ ብዙ እይታዎችን ማግኘት የቻለ እና በብዙዎች ዘንድ እየተጋራ የሚገኝ አንድ መረጃ በስፋት ሲዘዋወር ቆይቷል።  ይህ በፌስቡክ ላይ በስፋት ሲጋራ የቆየው መረጃ በያዝነው የፈረንጆቹ 2024 የአፍሪካ ሀገራቶችን የወታደራዊ ጥንካሬን እና ደረጃን የሚያሳይ ነው።

በተለያዩ የፌስቡክ ገፆች እና አካውንቶች በህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም የተጋራው ይህ መረጃ በወታደራዊ ጥንካሬ ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ተቀድማ ፤  አልጄርያ ፤ ግብፅ እና ናይጄርያን አስከትላ ሁለተኛ ደረጃ መያዟን ይገልፃል። ተመሳሳይ መረጃዎችም የተለያዩ ገፆች ላይ ሲጋሩ ቆይተዋል። (ይመልከቱ ፤ ይመልከቱ ፤ ይመልከቱ ፡፡)

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ መረጃውን እና የመረጃው ምንጭ የተባለውን ገፅ ያጋራውን መረጃ በማመሳከር እና በማጣራት መረጃውን ሀሰት ብሎታል።     

      ከተለያዩ የፌስቡክ ገፆች የተወሰዱ ምስሎች ፡ ህዳር 3 ቀን 2017 ዓም የተጋሩ 

የአንድ ሀገር ወታደራዊ ጥንካሬ የሚለካው በተለያዩ መመዘኛ ነጥቦች ሲሆን ከነዚህም መካከል አንድ ሀገር ያሉት ንቁ/Active እና ተጠባባቂ ወታደሮች ፤ ያሉት የመሳሪያ አቅም ማለትም ያለው ወታደር እና የወታደራዊ በጀት ፤ የሎጅቲክ አቅም ከግምት ውስጥ ይገባሉ።  

የአንድ ሀገር ወታደራዊ አቅም በምን ይለካል? 

ወታደራዊ አቅም የሚባለው ነገር ሰፊ እና የተለያዩ ፅንሰ ሀሳቦች በውስጡ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ነጥቦች አንድ ሀይሉን የማሳየት እና ሉአላዊነት እና ጥቅሙን ማስከበር የሚችልበትን ደረጃ ለመምዘን ይረዳሉ። አንድ ሀገር ያላት የወታደር ብዛት ብቻውን ሀገሪቱ ያላትን ወታደራዊ ጥንካሬ ለማሳየት መሆን አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ የወታደር ብዛት ወታደራዊ ውጤታማነት ላይ የሚያመጣው ጥሩ እና መጥፎ ነገሮች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።       

ይህ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ መሳርያዎቹ ያላቸው ጥራት እና ከዘመኑ ጋር አብሮ መሄዳቸው ፤ ሀገሪቱ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና ለመከላከያ የሚመደበው በጀት ከግምት ውስጥ ይገባሉ።

በ2024 የአፍሪካ ሀገራቶች ወታደራዊ ደረጃ

በአለም ላይ ያሉ ሀገራቶችን ወታደራዊ አቅም የሚለኩ እና ደረጃ የሚሰጡ አንዳንድ ድርጅቶች እና ተቋማቶች አሉ።  ይህ የደረጃ አሰጣጥ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሲሆን ይህም የወታደር ብዛት ፣ የጦር መሳሪያዎች ፣ ወታደራዊ በጀት ሎጂስቲክ እና አጠቃላይ ስልታዊ ችሎታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

ከነዚህ ተቋማት መካከል ግሎባል ፋየርፓወር (Global Firepower ) የተሰኘው ተቋም በአለም ላይ ተቀባይነት ያለው እና በአለም ላይ ያሉ ሀገራቶች ወታደራዊ አቅም እና መከላከያው ያለው ሀብቶች ላይ አጠቃላይ ግምገማዎችን ያደርጋል። ግሎባል ፋየርፓወር የተሰኘው ይህ ተቋም በአለም ላይ ያሉ ሀገራት ያላቸውን የመከላከያ ሀይል ጥንካሬ በቁጥር እና ጥራት ላይ መሰረት በማድረግ ልዩ የሆነ የደረጃ አሰጣጥ ስርዓትን ተጠቅሞ ደረጃ ይሰጣል።   ይህ ተቋም በየአመቱ  የሚወጣው ሪፖርት እና የደረጃ አስጣጥ ከ60 በላይ መለኪያዎችን ከጥቅም ላይ ያውላል። 

በፈረንጆቹ 2024 የወጣው ግሎባል ፋየርፓወር ሪፖርትም ከ145 በላይ ሀገራቶችን ከግምት እና ደረጃ ውስጥ ማስገባት ችሏል። በዚህ ዝርዝር ሪፖርት መሰረት ግብፅ ከአፍሪካ ሀገራት በወታደራዊ ጥንካሬ በአንደኝነት ስትቀመጥ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተል ይይዛሉ፡፡

 
ከግሎባል ፋየርፓወር እ.ኤ.አ የ2024 ሪፖርት የተወሰደ ምስል 

ሌላው ሀቅቼክ የተመለከተችው ወታደራዊ መረጃዎችና ንፅፅሮችን በማቅረብ የሚታወቀው ስታቲስታ (Statista) የተባለ ተቋም ሲሆን ድርጅቱ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በመጠቀም ግላጭ ምስሎችን የሚያቀርብ፣ ከ80,000 በላይ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ የስታቲስቲክስ ሪፖርቶች እና ግንዛቤዎች በመብሰብሰብ መረጃ የሚሰጥ መካነ ድር ነው። ይህም ተቋም የ2024 የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ ደረጃዎች ላይም መረጃዎችን አውጥቷል።  በዚህም ሪፖርቱም የኢትዮጵያን ሁለተኛነት አያሳይም፡፡

    ከስታቲስታ የ2024  እ.ኤ.አ ሪፖርት የተወሰደ ምስል 

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩት የኢትዮጵያን ሁለተኛነት የሚያሳዩት ምስሎች የተጠቀሙት ምስል ላይ ስታቲሴንስ (Statisense)  እንደምንጭነት የተጠቀሰ ሲሆን ሀቅቼክ ይህ ተቋም ማነው የሚለውን ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ድርጅቱ በዋናነት በአፍሪካ በትምህርት፣ ጤና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ በመተንተን እና የአቅም ግንባታ ስራዎች አገልገሎት እንደሚሰጥ ተረድቷል፡፡  ይህ ተቋም የንግዶች ተቋማቶች እንዴት እንደሚገናኙ እና የፋይናንሺያል መረጃቸውን በመተንተን ላይ ያተኮረ ሲሆን ለዚህም ስራ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በዋናነት እንደሚጠቀም ማወቅ ተችሏል።

                 
          Screenshot of በማህበራዊ ሚድያ ከተሰራጩት ምስሎች የተወሰደa የStatisense አርማ

ሀቅቼክ በስታቲሴንስ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ላይ የተጋራውን ትክክለኛ እና ያልተቀናበረውን የመረጃ ፖስት ማገኘት ችሏል። ሀቅቼክ ትክክለኛውን ፖስት በስታቲሴንስ ይፋዊ የX ገፅ በጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ላይ ተጋርቶ አግኝቶታል። በግምገማችን መሰረት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ ሲሰራጩ የነበሩት ምስላዊ መረጃዎች ተቀይረው እንደተጋሩ መረዳት ችሏል። በተለይም የአንዳንድ ሀገራቶችን ባንዲራ ቦታውን በመቀያየር በ2024 የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ ጥንካሬ ደረጃ የተለየ እንዲሆን ለማድረግ ሞክረዋል።


                                  የተቀናበረ እና ትክክለኛ መረጃ የሚገኝበት ፖስቶች የተወሰደ ምስል

ስለዚህ መረጃ እንዲነግሩን እና ተጨማሪ መረጃዎችን እንዱያጋሩን ወደ ስታቲሴንስ የኢሜይል መልዕክትን የላክን ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከተጋራበት ጊዜ ድረስ መልስ ማግኘት አልቻልንም።


ማጠቃለያ/ውሳኔ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በወታደራዊ ጥንካሬ ከአፍሪካ በሁለተኛ ላይ ትገኛለች የሚለው መረጃ በስፋት ሲጋራ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ወታደራዊ ጥንካሬን በመረጃ በመመዘን እና በማንፃፀር የሚታወቁ ምንጮችን ዋቢ በማድረግና እንደምንጭነት የተጠቀሰው ተቋም ያጋራውን ትክክለኛ መረጃ መሰረት በማደረግ መረጃው ሀሰት እንደሆነ ማረጋግጥ ችሏል። 

Exit mobile version