ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን ለመጭው የኢትዮጵያ የገና በዓል የ75ሺህ ብር ስጦታ አዘጋጅተዋል?

የበዓል ወቅቶች በቀረቡ ቁጥር የተለያዩ ሰዎችን የማጭበርበሪያ እና የማጥመጃ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። በዚህ ወቅትም የመንግስት ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የፀጥታ ተቋማት ህብረተሰቡ በበዓላት ወቅት ከእንደዚህ አይነት የማጭበርበሪያ መንገዶች እራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰብ አለባቸው።

በአሁኑ ጊዜ አጭበርባሪዎች የተለያዩ ቴክኒክ እና ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ከሚጠቀሟቸው መንገዶች አንዱ የሰዉን ደካማ ጎን እና ስሜቱን ሊይዝ የሚችሉ ነገሮችን በመጠቀም ሲሆን ሰዎች ሽልማቶችን እና ገንዘቦችን ማግኘት ከፈለጉ በፍጥነት እንዲያደርጉ በመገፋፋት በመጠየቅ ነው። ይህንንም ሲያደርጉ የተለያዩ ታዋቂ ፤ ሀብታም እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ስም እና ማንነት ከዚህም ባለፈ የታዋቂ ድርጅቶች ምልክቶችን እና ድረ-ገፆችን አስመስሎ በመስራት ታማኝ ለመምሰል ይሞክራሉ። ከሰሞኑ በተለያዩ የፌስቡክ ገፆች ላይ ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን ለኢትዮጵያውያን የ75ሺ ብር ስጦታ እየሰጡ እንደሆነ እና ሽልማቱንም ለማግኘት የተቀመጠውን ሊንክ በመጫን በድረ-ገፁ ውስጥ ያለውን ፎርም እንዲሞሉ ያስገድዳል። ፖስቶቹን ለመልከት እዚህ ጋር (ይጫኑ ፣ ይጫኑ)።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ እነዚህን ፖስቶች ከመረመረ በኋላ የተሳሳቱ እና የማጭበርበሪያ መንገዶች እንደሆኑ አረጋግጧል።   

ከተለያዩ የፌስቡክ ፖስቶች የተወሰዱ ምስሎች (ምስል አንድ ፤ ምስል ሁለት)

ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑት የሳውዲው ቢልየነር ሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ከየመናዊ አባታቸው እና ከኢትዮጵያዊ አባታቸው በወሎ ክፍለ ሀገር ውስጥ የተወለዱ ሲሆን ከዚያም በኋላ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሄደው የሳውዲ ዜግነትን ማግኘት እንደቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ። 

በፈረንጆቹ 2024 ብሉምበርግ ይዞ በወጣው የቢልየነሮች ዝርዝር ውስጥ የሳውዲ ኢትዮጵያዊው ቢልየነር ሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን በ8.73 ቤልየን ዶላር በአለም ላይ 324ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሀቅቼክ መረጃውን መረጃውን በፌስቡክ ላይ ያሰራጩትን ሰዎች መረጃውን ከየት እንዳገኙት እና መረጃውን ያጋሩበትን አላማ ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሁለቱም የፌስቡክ ገፆች የመልዕክት መቀበያ ክፍሉን መዝጋታቸውን ማስተዋል ችለናል። 

ነገር ግን ሀቅቼክ መረጃውን ያሰራጩትን አካላቶች ከዚህ በፊት ሲያሰራጯቸው የነበሩትን መረጃዎች በማጥናት ይህን መረጃ በምን አላማ ሊያሰራጩ ይችላሉ የሚለውን ተመልክቷል። “Apostl Esrael Abebe” በሚል ስም የተከፈተው የፌስቡክ ገፅ አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን ነገሮች እንደሚያጋራ የተመለከትን ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን ስም ላጋራው መረጃም እርግጠኛ እንዳልሆነ እና ሰዎች ሊንኩን ሲጠቀሙ እንዲጠነቀቁ ሰዎች ለጠየቁት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ ተመልከተናል። ከዚህ በተጨማሪም በኮመንት መስጫው ስር መረጃውን የሚያውቀው ሰው እንዳጋራው እና እሱም ዝምብሎ እንዳጋራው ሲገልፅ ተመልክተናልገ። ከዚህም ተነስተን ይህ የፌስቡክ ገፅ የተሳሳተውን መረጃ ባላማወቅ እንዳጋራው መረዳት ችለናል።

ከዚህ በተጨማሪም ሁለተኛውን እና Mekonnen Maryamawit Muktar በሚል ስም የተከፈተውን የፌስቡክ ገፅ ከዚህ በፊት የሚያጋራቸውን ነገሮች ለመመልከት የሞከርን ሲሆን ይህ ገፅ ከፖለቲካ ነክ ነገሮች አንስቶ እስከ መዝናኛ ቪድዮዎች ድረስ እንደሚያጋራ መመልከት ችለናል። ይህ ገፅ አብዛኛውን ጊዜም ሌሎች ያጋሩትን ነገር መልሶ እንደሚያጋራ መመልከት ችለናል። 

ሀቅቼክ ከነዚህ መረጃዎች በመነሳት በእነዚህ የፌስቡክ ገፆች የተጋራውን ሊንክ ትክክለኛነት ያጣራ ሲሆን ኦንላይን የሚገኙ የማጣሪያ መሳርያዎችን ተጠቅመን ስንመለከት ሊንኩ የሚወስደን ድረ-ገፅ አደገኛ እና ሰዎችን ለማጥመድ የተዘጋጀ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል። ከዚህ በተጨማሪም የማስፈንጠርያ ሊንኩን ሳንጫን ሊንኩ ሊወስደን የሚችለውን ድረ-ገፅ መመልከት ችለናል።


ሊንኩ አደገኛ እንደሆነ ካሳየን መሳርያ እና ከድረ-ገፁ ላይ የተወሰዱ ምስሎች

ሊንኩ የሚወስደን ድረ-ገፅ የሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን ምስልን የያዘ ሲሆን እሰጣለው የሚለውን ገንዘብ በቁጥር 95000 ብር ብሎ ካስቀመጠ በኋላ በቅንፍ ውስጥ በአማርኛ ፅሁፍ 75000 ብር ብሎ ያስቀምጣል። 



ድረ-ገፁ የሰራቸውን የፅሁፍ ስህተቶች የሚያሳይ ምስል 

ሀቅቼክ በብዙ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የሚሳተፈውን እና በዚህ ጉዳይ መልስ ሊሰጠን ይችላል ብለን ያሰብነውን ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕን ያነጋገርን ሲሆን ከሚድሮክ ኢትዮጵያ የሚድያ ሰዎች ጋር ተነጋግረው መልስ እንደሚሰጡን ቃል ገበተውልናል። ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ግሩፕ መልስ እንዳገኘን መልሰን መረጃውን የምናደርስ ይሆናል።

ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን እና ቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ጊዜያቶች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እና በበዓላት ጌዜያቶች አቅም ለሌላቸው ወገኖች እርዳታን እንደሚሰጡ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ በፌስቡክ ገፆቹ የተጋራውን ፖስት እና የተያያዘውን ሊንክ በማጣራት ሰዎችን የማጥመጃ እና የማጭበርበር ይዘት እንዳለው ማረጋገጥ ችሏል።


 

Exit mobile version