የተጣሩ መረጃዎች

ሀሰት፡ ምስሉ የኦነግ ሸኔ ጦርን የተቀላቀሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎችን አያሳይም

ከ436ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገጽ በሕዳር 23 ፤ 2014 ዓ.ም “1287 የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሀይል አባላት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ተቀላቀሉ።” በማለት አንድ ምስልን በማያያዝ አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ300 ጊዜ በላይ የተጋራ ሲሆን ከ1000 በላይ ግብረ መልስን ማግኘት ችሏል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።      

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚያዝያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም እራሱን ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ማግለሉን ያሳወቀ ሲሆን በሃገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ‘ሸኔ’ አሸባሪ ድርጅት በመባል ተፈርጇል። በመንግስት ‘ሸኔ’ እየተባለ የሚታወቅ ራሱን ደግሞ ‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት’ ብሎ የሚጠራ ወታደራዊ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ባሉ ቦታዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዳደረሰ የሚያሳዩ የተለያዩ ክሶች ይቀርቡበታል። ወታደራዊ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ጦርነትን በማድረግ ላይ ከሚገኘው ህወሓት ጋር ከህዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ለመስራት መስማማቱን አሳውቋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የጸጥታ ሃይሉን በአዲስ መልክ እያደራጀ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።”  

በፌደራል መንግስቱ ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጨማሪ የጸጥታ ሃይሉ በክልሉ ዞን ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንዲያግዛቸው በሚል ከህዳር 6 ፤ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ ታውጇል። በኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይሎች እና በ’ኦነግ ሸኔ’ መካከል ያለው ግጭት እየቀጠለ ቢሆንም አንዳንድ የክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል አባላቶች ወደ ‘ሸኔ’ ጦር ተቀላቅለዋል የሚሉ ወሬዎች ይሰማሉ።  

የኦነግ ‘ሸኔ’ ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ በጥቅምት 25 ፤ 2014 ዓ.ም “በዛሬው ዕለት 1165 የሚሆኑ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል አባላት መንግስትን ክደው የ‘ሸኔ’ን ጦር የተቀላቀሉ ሲሆን ከነሱ መካከል 400 የሚሆኑት ከለገጣፎ እና አካባቢው የመጡ ናቸው። ጦራችን በሁሉም አቅጣጫ እየገፋ በመጠጋት ላይ ሲሆን ይህን ጨቋኝ እና አምባገነን ስርዓት ማብቂያው ጊዜ ቅርብ ነው” በማለት አጋርቶ የነበረ ሲሆን ፣ ይህ የፌስቡክ ልጥፍም በዚህ ሁኔታ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። ይሁን እንጂ በየካቲት 29 ፤ 2012 ዓ.ም ተመሳሳይ ምስል በአንድ የትዊተር አካውንት ላይ “አብይ አህመድ 20 ሚልዮን የሚደርሱ ነፍጠኛ እና ጎበናዎችን ቢያሰልፍ እንኳን አያድኑትም” በሚል ተጋርቶ ነበር።  

ከዚህም በተጨማሪ ምስሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለ30ኛ ዙር ያስመረቃቸውን የልዩ ፖሊስ ሃይል አባላት የምርቃት ስነ-ስርዓት ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ምስል ነው። አንዳንድ የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት ወደ ‘ኦነግ ሸኔ’ ተቀላቅለዋል የሚል ያልተረጋገጡ ወሬዎች ይኑሩ እንጂ ምስሉ የኦነግ ሸኔን ጦር ለመቀላቀል ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል የተመለመሉ ወታደሮችን አያሳይም። ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ልጥፉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

ሀሰት፡ ምስሉ በቅርቡ የተማረኩ የመንግስት ወታደሮችን አያሳይም

ከ75,000 በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገጽ በሕዳር 19 ፤ 2014 ዓ.ም “ትናንት በካሳጊታ አፋር ግንባር የተማረኩ የብልጽግና ወታደሮች” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቦክ ልጥፉ ከ800 በላይ ግብረ መልስ አግኝቷል።

ምስሉ በሌሎች ገጾች እና የዜና አውታሮች በተለያየ አውድ የቀረበ ሲሆን ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

 

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት ቀጥሏል። በግንቦት 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ድንገተኛ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ ሁሉንም የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ ዋና ዋና ቦታዎች አስወጥቷል። 

ከዚያ በኋላ የህወሓት ሃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር ወደክልሉ ደቡባዊ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ አጎራባች በሆኑት የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በሓምሌ 29 ፤ 2013 ዓ.ም የህወኃት ሃይሎች በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ አካባቢ የምትገኘውን የላሊበላ ከተማን እና አካባቢውን ተቀጣጥረዋል። 

በሕዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦርነቱን በግምባር ሆነው ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የተለያዩ የማጥቃት እና የመልሶ ማጥቃት የጦርነት ዜናዎች እየተሰማ ይገኛል። በሕዳር 17 ፤ 2014 ዓ.ም በፌደራል መንግስት የሚመራው ጥምር ሀይል ካሳጊታን መልሶ መያዙን እና ወደ ቡርቃ እና ባቲ አካባቢ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አሳውቀዋል። 

ከፌስቡክ ልጥፉ ጋር የተያያዘው ምስል የጉግል ተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ከሆነ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው ትግራይ ፕሬስ በሚባል የፌስቡክ ገጽ በነሃሴ 2013 ዓ.ም ነበር።   

ስለሆነም ምስሉ ማስተላለፍ ከፈለገው መልዕክት ጋር የተሳሳተ ግንኙነት ስላለው ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።

ሀሰት ፡ ምስሉ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሰፈሩ የሱዳን ወታደሮችን አያሳይም

አንድ ከ436,600 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ እንዲሁም ከ1,500 በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት ላይ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትጋራው ድንበር አካባቢ በቁጥር በዛ ያሉ ወታደሮቿን አስፍራለች” በማለት በህዳር 21 ፤ 2014 ዓ.ም የተለያዩ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል። 

በጥቅምት 2013 የፌደራል መንግስት ከህወኃት ጋር በገቡት ግጭት ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱን ወደ ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ያንቀሳቀሰ ሲሆን ይህን አጋጣሚ ካርቱም ወታደሮቿን አልፋሽጋ በሚባለው አካባቢ ላይ ለማስፈር ተጠቅማበታለች። ይህን የሱዳን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ትንኮሳ ብሎ የፈረጀው ሲሆን ይህ አካባቢ ሱዳን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የሚጋሩት ቦታ ሲሆን ድንበሩ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያ ስር የነበረ ነው። የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ሃይሎች አወዛጋቢ በሆነው ድንበር አካባቢ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በሱዳን ወታደሮች እና በአካባቢው በሰፈሩ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረውብኛል የሚሉ ክሶችን አቅርቧል።  

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሃይሎች በሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚለውን ክስ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን “ብዛት ያላቸው አማጽያን ባንዳዎች እና አሸባሪዎች በሱዳን በኩል ዘልቀው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞከሩ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአካባቢው ሚሊሻ መክቶ ወደመጡበት መልሷቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የልጥፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የጉግል የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ሂደትን ተጠቅሟል። 

የመጀመሪያው ምስል የተወሰደው በህዳር 2009 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮች በሰሜኑ የሱዳን ክፍል አካባቢ ልምምድ ሲያረጉ የሚያሳይ ነው። 

ሁለተኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በሚያዝያ 2 ፤ 2012 ዓ.ም በቻይንኛ ቋንቋ በሚቀረብ አንድ ድህረ-ገጽ ላይ ነበር።

ሶስተኛው ምስል የተወሰደው ከ14 ዓመት በፊት በS.Telliks አማካኝነት ሲሆን ምስሉ በህዳር 14 ፤ 2012 ዓ.ም በአንድ ድህረ-ገጽ ላይ ተለቆ ነበር። 

የመጨረሻው ምስል የተለቀቀው በሕዳር 12 ፤ 2014 ዓ.ም በአንድ የአረብኛ ድህረ-ገጽ ላይ “የሱዳን ወታደራዊ ጦር ከኢትዮጵይ ጋር አለ የሚባለውን ግጭት እንደማይቀበል አስታወቀ” በሚል ርዕስ ስር የቀረበ ነበር።  

ሀቅቼክ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትጋራው ድንበር አካባቢ ብዙ ወታደሮቿን አስፍራለች” የሚለውን ጽሁፍ ለመደገፍ የቀረበው ምስልን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።  

ሀሰት: ምስሉ የመንግስት ሃይሎች ላሊበላን መቆጣጠራቸውን አያሳይም 

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ገፆች ከማክሰኞ ሕዳር ፤ 14 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላሊበላ እና አካባቢው በመንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር ገብተዋል የሚሉ ልጥፎች ሲዘዋወሩ አስተውለናል። ሲዘዋወሩ ከነበሩት ልጥፎች መካከል አንዳንዶቹ አንድ የአማራ ልዩ ሃይልን የደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ከታዋቂው “የቤተ-ጊዮርጊስ” ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አጠገብ ተቀምጦ የሚያሳይ ምስል አያይዘው ለጥፈዋል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል። 

ከህዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፌደራሉ መንግስት እና የህወኃት ሃይሎች በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል አስወጥቷል።

ከዚያ በኋላ የህወኃት ሃይሎች ወደ ደቡባዊ የክልሉ አቅጣጫ በመጓዝ የአማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እየገፉ በመምጣት ሐምሌ ፤ 29 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘውን የላሊበላ ከተማን ተቆጣጥረዋል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የማጥቃት እና የመልሶ ማጥቃት እርመጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል። በሕዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ።” በማለት ጦርነቱን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ጦር ሜዳ መዝመታቸውን ተከትሎ አዳዲስ የመልሶ ማጥቃት ወሬዎች እየተሰሙ ይገኛሉ። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግምባር በመዝመት እና አቅጣጫ ለመስጠት በጦር ሜዳ ግምባር መገኘታቸውን ተከትሎ  በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ የድል ዜናዎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። ይህም የፌስቡክ ልጥፍ በዚህ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ሀቅቼክም ጉዳዩን በመከታተል የልጥፉን እውነታነት ለማጥራት ባደረገው ጥረት መሰረት የተጋራው ምስል የቆየ እንደሆነ አረጋግጧል። ምስሉ ከዚህ ቀደም በሚያዚያ 21 ፤ 2013 ዓ.ም ዉበቱ ይግዛው በተባለ የፌስቡክ አካውንት “የቅዱስ ላሊበላ መቅደሶች በአማራ ልዩ ሃይል በተጠናከረ ሁኔታ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።” በማለት ምስሉን አጋርቶት ነበር። 

የመጀመሪያው ልጥፍ

ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከፌደራል መንግስቱም ሆነ ከህወኃት ሃይሎች ከተማዋ ስለመያዟ የወጣ ምንም አይነት መግለጫ የለም። ከሚመለከታቸው አካላት የተረጋገጠ መረጃን ለማግኘት ጥረት እያደረግን ሲሆን አዲስ መረጃ እንዳገኘን የምናሳውቅ ይሆናል። 

ምንም እንኳን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመንግስት ሃይሎች የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን የሚገልፁ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ሀቅቼክ ምስሉ የመንግስት ሃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ስለማያሳይ ሀሰት ብሎታል። 

ሀሰት፡ ትግራይ ቴሌቪዥን የተጠቀመው ተንቀሳቃሽ ምስል በወሎ የተደረገን የድሮን ድብደባ አያሳይም

ከ274ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “የትግራይ ቴሌቪዥን” ዩትዩብ ቻናል በጥቅምት 29 ፤ 2014 ዓ.ም “የፋሽሽቱ አብይ አህመድ መንግስት ድሮኖችን እና ከባባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም በወሎ ላይ የአየር ድብደባን ፈጽሟል” በማለት በትግርኛ የተፃፈ ርዕስን በመስጠት የዜና ቪዲዮ በመለጠፍ በጥቃቱም ብዙ ንጹሃኖች እንደተገደሉ ዘግቧል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የዩትዩብ ቪድዮው ከ73 ሺህ ጊዜ በላይ እይታን እና ከ1600 በላይ ግብረ መልሶችን ማግኘት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ትግራይ ቴሌቪዥን በዜና ዘገባው ላይ የተጠቀመውን ቪዲዮ አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።     

ከሕዳር 2013 ዓ.ም አንስቶ በህወኃት እና በኢትዮጵያ ፌደራሉ መንግስት መካከል ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አስወጥቷል።   

ከዚያም በኋላ የህወኃት ሃይሎች ወደ ደቡባዊ የክልሉ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ የአማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት ያደርሱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የህወኃት ሃይሎች በአማራ ክልል የሚገኙትን የወሎ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ተሰምቷል።    

በሁለቱ ሃይሎች መካከል ባለው ጦርነትም ከጥቅምት ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተከታታይ የሆኑ የአየር ላይ ጥቃቶችን እያካሄደ ይገኛል። በዚህ ቪዲዮ ላይም በህወሃት የሚታገዘው ትግራይ ቴሌቪዥን ለማሳየት የሞከረው የኢትዮጵያ መንግስት በወሎ አካባቢ ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ የአየር ላይ ድብደባ አካሂዷል በማለት ነው።  

በትግራይ ቴሌቪዥን የተለቀቀው ቪዲዮ የፌደራሉ መንግስት ድሮኖችን ተጠቅሞ ወሎ ላይ ድብደባን ፈጽሟል የሚለውን ዜና ለመደገፍ ከ OMN (Oromia Media Network) ቲቪ ላይ የተደረገን ቃለ-ምልልስን እንደ ግብአት በመውሰድ ተጠቅመዋል።

ሀቅቼክ በOMN የተሰራዉን ቪዲዮ ማግኘት የቻለ ሲሆን ዜናው “ወሎ በብልጽግና አመራሮች ምክንያት በድሮኖች እና በከባባድ መሳሪያዎች እየተደበደበች እንደምትገኝ እና በዚህም ምክንያት ንጹሃንም ተጎድተዋል የሚል ነው።” በእለቱ ተጋባዥ እንግዳ የነበረችው ወ/ሮ ፋጡማ ኑሪዬ ለ OMN እንደተናገረችው በወሎ የሚገኘውና ለክርስትያን እና ለሙስሊም እንደ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቦታ ሆኖ የሚያገለግለው ጡርሲና ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያ አየር ሃይል እንደተደበደበ ገልጻለች። መረጃውን ለመደገፍ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪደዮ) አጋርቷል።

ሀቅቼክ ከቪዲዮው ላይ ስክሪን ሾት በመውሰድ ባደረገው ጉግል የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በጥቅምት 27 ፤ 2014 ዓ.ም በAFP News Agency የዩትዩብ ቻናል ላይ ሲሆን ቪዲዮው የሚያሳየው በሴራ ሊዮን፣ ፍሪታውን በመኪና አደጋ ምክንያት የተቀሰቀሰው እሳት ተስፋፍቶ እሳቱ ወደተለያዩ ቦታዎች በመሰራጨት ብዙ ጉዳቶችን ማድረሱን እና በአደጋው ቢያንስ 92 ሰዎች መሞታቸውን ነበር።

ምንም እንኳን በፌደራሉ መንግስት እና በህወኃት መካከል በአማራ ክልል እየቀጠለ ያለ ጦርነት ቢኖርም በትግራይ ቴሌቪዥን የታየው ቪዲዮ ግን በኢትዮጵያ አየር ሃይሎች የተደረገውን የድሮን እና የአየር ላይ ጥቃት ስለማያሳይ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።                                          

ሀሰት: ምስሉ በአዲስ አበባ ከተማ የተያዙ ጥይቶችን አያሳይም

አንድ የፌስቡክ ልጥፍ “በአዲስ አበባ በፍተሻ በአንድ ቤት የተገኘ ነው” በማለት ብዛት ያለቸው ጥይቶችን የሚያሳዩ ሁለት ምስሎችን በህዳር 7 ፤ 2014 ዓ.ም አጋርቶ ነበር። ይህ የፌስቡክ ገፅ ከ 411 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን 5000 የሚጠጋ ግብረመልስ አግኝቶ ከ690 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ሀሰት ብሎታል። 

  

በሀገሪቷ በሰሜናዊ እና ሰሜናዊ ምስራቅ አካባቢ የተቀሰቀሰው ግጭት መስፋፋቱን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚል የሰዓት እላፊ ተግባራዊ ተደርጓል። የፌደራሉ መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ እና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ ባፋጣኝ ለፀጥታ ሃይሎች እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል። 

በቅርቡ ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ለሽብር ተግባር ሊውሉ ነበሩ ያላቸውን የተለያዩ መሳሪያዎችን እና ተተኳሽ ጥይቶችን መያዙን ሪፖርት አድርጓል።   

ይህ የፌስቡክ ልጥፍም በዚህ ሁኔታዎች መሰረት በአዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተገኙ ጥይቶች በማለት አንድ ምስልን የተጠቀመ ቢሆንም ሀቅቼክ ምስሉ ከ8 ወር በፊት የተወሰደ እንደሆነ አረጋግጧል። 

በልጥፉ ላይ የተመለከተው የመጀመሪያው ምስል በሚያዚያ 7 ፤ 2013 ዓ.ም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦሮምኛ ገጽ ላይ ከተፃፈ ጽሁፍ የተወሰደ ሲሆን ምስሉ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ኬላ ላይ የተያዙ ጥይቶችን ያሳያል። ትክክለኛውን ምስልን እዚህ ማግኘት ይችላሉ።  

የፌስቡክ ልጥፉን ለመደገፍ የተወሰደው ሁለተኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በሚያዚያ 8 ፤ 2013 ዓ.ም በአንድ የፌስቡክ ልጥፍ ላይ ሲሆን ልጥፉ አያይዞም ሁለት ግለሰቦች በኮምቦልቻ ከ5000 ከሚበልጡ ጥይቶች ጋር እንደተያዙ ይገልጻል። ትክክለኛው የፌስቡክ ልጥፍ እዚህ ይገኛል። 

ስለዚህ ሀቅቼክ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የተመለከቱት ምስሎች በቅርቡ በአዲስ አበባ የተያዙ ጥይቶችን የማያሳዩ በመሆናቸው ሀሰት ብሎታል።      

ሀሰት: ምስሉ በትግራይ ሃይሎች የተመታ ሄሊኮፕተርን አያሳይም

Tigray people’s Liberation Front /TPLF/ የተባለ በፌስቡክ ማረጋገጫን ያገኘ እና ከ600 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ “ጀግናው የትግራይ ሰራዊት ዛሬ ጠዋት በሚሌ ግንባር አንድ የወታደራዊ ሄሊኮፕተርን መቶ ጥሏል” በማለት የሚነድ የሄሊኮፕተርን የሚያሳይ ምስል በማያያዝ አንድ ልጥፍ አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ650 ጊዜ በላይ ሲጋራ ከ6ሺህ በላይ ግብረመልስን አግኝቷል።   

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ አሁን በሃገሪቷ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተመቶ የወደቀን ሄሊኮፕተር እንደማያሳይ በማረጋገጥ ሀሰት ብሎታል። 

ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የህወሓት ሃይሎችና የኢትዮጵያው ፌደራል መንግስት አመት የፈጀ ጦርነት ላይ ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ላይ የሕወሃት ባለስልጣናትን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ ሰራዊትን ወደ ትግራይ የላኩ ቢሆንም በሰኔ ወር ሕወኃት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችን ተቆጣጥሯል። 

በቅርቡም ጦርነቱ እየተስፋፋ የሄደ ሲሆን ሕወኃት ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች በመግባት ጥቃት እንደፈጸመ ሪፖርት ተደርጓል። የተለያዩ የሚዲያ ምንጮች የሕወኃት ሃይሎች አዲስ አበባን ለመቆጣጠር በመቃረብ ላይ እንደሚገኙና የፌደራል እና የክልል ሃይሎችን እያሸነፉ እንደሆነም እየዘገቡ ይገኛሉ።

የተለያዩ ቁልፍ ቦታዎችን በመቆጣጠር የፌደራሉን መንግስት ማዳከም ለሕወኃት ሃይሎች እንደወሳኝ ነገር የሚታይ ነው። በዚህ ጽሁፍ መሰረት በአፋር ክልል የምትገኘው የሚሌ ከተማ ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝኝ ዋና መንገድ እንደመሆኗ እሱን አካባቢ መቆጥጠር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋን የተጠቀመ ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በጥቅምት 13 ፤ 2009 ዓ.ም “i was blown up and trapped by isis guns” በሚል ርዕስ  The Times በሚባል ድህረ ገጽ ላይ ነበር።    

ትክክለኛው ምስል 

ስለዚህ ሀቅቼክ ምስሉ በሚሌ ግንባር በህወሓት ሃይሎች ተመቶ የወደቀን ሄሊኮፕተር እንደማያሳይ ያረጋገጠ ሲሆን ይልቁንም ምስሉ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአራት አመት በፊት የተወሰደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች መሰረት ልጥፉ ምስሉ ይገልጸዋል ከተባለው ነገር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስለሌለው ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።   

ሀሰት፡ ምስሉ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) ጦር ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ጉዞ አያሳይም

ከ180 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መሪ ጃል መሮ ጦሩን ወደ አዲስ አበባ እንዲንቀሳቀሱ ካዘዛቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን ጀምረዋል” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር። ልጥፉ ከ1000 በላይ ግብረመልስ ያገኘ ሲሆን ከ100 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት  መሆኑን አረጋግጧል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረ እና የኦሮሞ ብሄረሰብን የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለማስጠበቅ አላማው አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን የተመሰረተውም በ 1963 ዓ.ም ነበር።  በ 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሽብርተኝነት የተፈረጁና ከሃገር የተሰደዱ ፖለቲከኞች እንዲሁም የተለያዩ የፖሊቲካ ፓርቲዎች በ2011 ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዋር ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተደርጓል። 

ከዚያም በኋላ የኦሮሚያ ነጻነት ጦር ወይም ኦነግ ሸኔ የሚባል ስም መሰማት ጀመረ። የሸኔ ሰራዊት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ፣ ሰዎችን አፍኖ መውሰድ እና የመንግስት ባለስልጣናትን መግደልን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ወንጀሎችን ይፈፅማል ተብሎ ይወቀሳል። 

በሚያዚያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም የኢ.ፌ.ድ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕውሃትን እና ኦነግ ሸኔን በሽብርተኝነት የፈረጃቸው ሲሆን በነሃሴ 5 ፤ 2013 ዓ.ም የኦነግ ሸኔ ጦር መሪ ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮ ጦራቸው ከሕውሃት ጦር ጋር አንድነት መፍጠሩን ለአሶሺየትድ ፕሬስ አሳውቋል። በጥቅምት 22 ፤ 2014 ዓ.ም የቢቢሲ አፍሪካ ዜና አጠናቃሪ የሆነችው ካትሪን ብያሩሃንጋ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚስጥራዊ የጦር ቡድኖች” በማለት አንድ ቪዲዮ ሰርታለች ፤ በቪዲዮውም ቡድኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲያደርግ የሚታይ ሲሆን ከቡድኑ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋ ነበር። በሪፖርቱም ጃል መሮ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ የሸኔ ጦር በደቡብ ፣ በምዕራብ እና መካከለኛው ኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችን ተቆጣጥሯል ብሏል።

የፌስቡክ ልጥፉ በዚህ የተጋራ ሲሆን ሀቅቼክ የጎግል የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋን በመጠቀም ምስሎቹን አጣርቷል። ትክክለኛው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በ ሐምሌ 6 ፣ 2013 ዓ.ም genevasolutions.news በሚባል አንድ የዜና ማሰራጫ ድህረ ገጽ ላይ ሲሆን “የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ባለው ግጭት ላይ ውሳኔ አሳልፏል” በሚል አርዕስት የተፃፈ ፅሁፍ ውስጥ ተያይዟል። ልጥፉም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ እና ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በክልሉ የሚታዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስበው ገልጿል።

ይሁን እንጂ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የተመለከተው ምስል በፎቶሾፕ የተቀነባበረ እና ትክክለኛው ምስል ላይ ወታደሮችን በማድረግ የተሰራ ነው። 

የኦነግ ሸኔ ሰራዊት የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ ነው የሚሉ የተለያዩ ወሬዎች ቢኖሩም ምስሉ ግን ሀሰት እና የተቀነባበረ ስለሆነ ልጥፉ ሀሰት ነው።       

ሀሰት፡ ምስሉ የተያዙ ሰርጎ ገቦችን እና ሰላዮችን አያሳይም   

ከ59 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ በጥቅምት 25 ፤ 2014 ዓ.ም ሁለት ምስሎችን አያይዞ ለጥፏል። ከልጥፉ ጋር ተያይዞ የተጻፈው ፅሁፍ “አካል ጉዳተኛ በመምሰል የስለላና የሰርጎ ገብነት ተግባር ሲፈጽሙ የተያዙ የወራሪው ሀይል አባሎች ናቸው…” የሚል ሲሆን ልጥፉ ከተለቀቀበት ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ420 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ መረጃውን አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።  

በጥቅምት 23 ፤ 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ክልል ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ፀጉረ ልውጦችን እንዲከታተሉ እና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱም ሪፖርት እንዲያረጉ የተለያዩ መልዕክቶች ሲተላለፉ ቆይቷል። ይህ ልጥፍም በዚህ ሀሳብ መሰረት ነው የተለጠፈው።

 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ዋናውን ምስል ማግኘት ችሏል። ምስሎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቁት የፌስቡክ ልጥፉ ከመጋራቱ ከ3 ሰዓታት በፊት በሃዲያ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዲፓርትመንት የፌስቡክ ገፅ ሲሆን ጥቅምት 24 ፤ 2014 ዓ.ም በሃዲያ ዞን ውስጥ አካል ጉዳተኛ በመምሰል ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሰዎች መያዛቸውን ለመዘገብ የተጋራ ነበር።       

 

ሀቅቼክ የሃዲያ ዞን ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባለሞያ የሆኑትን አቶ ይዲድያ ተስፋሁንን በስልክ አግኝቶ ያነጋገረ ሲሆን የፌስቡክ ገፁ ትክክለኛ የዞኑ ገፅ እንደሆነ እና ሁኔታውንም የዘገቡት እሳቸው መሆናቸውን አረጋግጠውልናል። 

ሀሰተኛ ምስሉ የተለጠፈበት የፌስቡክ ገጽ የተከፈተው በነሃሴ 17 ፤ 2013 ዓ.ም በታዋቂው የኢሳት ቲቪ ጋዜጠኛ ስም “መሳይ መኮንን – ኢሳት“ ተብሎ የተከፈተ ሲሆን በጥቅምት 2 ፤ 2014 ዓ.ም የፌስቡክ ስሙን ወደ “ክሊክ ደሴ” ቀይሮታል። የታዋቂ ሰዎችን ስም በመጠቀም የሚከፈቱ ግፆች ብዙ ተከታዮችን ለማፍራት እና የተዛባ መረጃን ለማሰራጨት አንዱ መንገድ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እንደዚህ አይነት የስም ለውጦች የገጹን ተለዋዋጭ የሆነ አቋም የሚያሳዩ እና አብዛኛውን ጊዜ ለማሳሳት የሚደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

ነዋሪዎች በየአካባቢያችው ፀጉረልውጦችን እንዲከታተሉ መንግስት መልዕክት ያስተላለፈ ቢሆንም በምስሉ ላይ የተመለከቱት ሰዎች ሰርጎ ገብ እና ሰላዮች አለመሆናቸው እና ልጥፉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።       

ሀሰት: ተንቀሳቃሽ ምስሉ የከሚሴ ነዋሪዎች በቅርቡ የሸኔ ሰራዊት ወደከተማዋ  መግባቱን ተከትሎ ደስታቸውን ሲገልፁ አያሳይም

ከ38 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አንድ የፌስቡክ ገጽ በጥቅምት 21 ፤ 2014 ዓ.ም 3ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ የሚፈጅ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን የከሚሴ ህዝብ ለኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) አቀባበል ሲያደርግ የሚያሳይ በማለት አጋርቶ ነበር። በልጥፉ ላይ የተያያዘው ፅሁፍ “ከሚሴ በአሁኑ ሰዓት የህዝብ ማዕበል እየታየ ነው… ህዝቡ በሙሉ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ከተማዋን በማጥለቅለቅ ደስታውን እየገለፀ ይገኛል። በነጻነት ባንዲራችንም ከተማዋ ደምቃለች…” ሲል ይነበባል። በምስሉ ላይም የኦሮሞ ነጻነት ግምባር (ኦነግ) እና ኦነግ ሸኔ የሚጠቀሙበት ባንዲራ ይታያል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ6300 ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ከ70 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ወቅታዊ ሁኔታን የሚያሳይ ባለመሆኑ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚያዝያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) እና ህወሓትን አሸባሪ ቡድኖች በማለት ፈርጇቸዋል። ነሀሴ 5 ሁለቱ ቡድኖች በጋራ ለመስራት ጥምረት መፍጠራቸውን ገልፀዋል። በትግራይ  ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ አጎራባች አካባቢዎች ከተስፋፋ በኋላ የሕውሃት ጦር ደሴ እና ኮምቦልቻን ጨምሮ ወደተለያዩ ከተሞች መግባቱ ሲዘገብ ቆይቷል። በጥቅምት 22 ሸኔ ከአዲስ አበባ 335 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን የከሚሴ ከተማን መቀጣጠሩን የገለጸ ሲሆን የፌስቡክ ልጥፉም በዚህ ሃሳብ የተጋራ ነበር።   

ይሁን እንጂ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በተወሰደ ስክሪን ሾት የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ መሰረት ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከዚህ ቀደም በጥቅምት 13 ፤ 2011 ዓ.ም በፌስቡክ ላይ የተጋራ መሆኑን ለማወቅ ትችሏል። ምስሉ የት አካባቢ እንደተወሰደ ግልፅ ባይሆንም የተለጠፈበት ጊዜ ግን እንደሚያሳየው ከሀገር ውጪ የነበሩና የተለያዩ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጥሪ ከቀረበላቸው በኋላ በመስከረም 2010 ዓ.ም  የኦነግ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት አከባቢ የተወሰደ መሆኑን ያመለክታል። 

በሌላ በኩል ይህ ገጽ በህዳር 2013 ዓ.ም “DW International ድምጺ ወያኔ” በሚል ስም የተከፈተ እንደሆነ እና በኋላም በነሃሴ 27 ፤ 2013 ዓ.ም ስሙን አዋሽ ፖስት ወደሚል ሌላ ስም የቀየረ ሲሆን እንደዚህ አይነት የስም ለውጦች የገፁን አገልግሎት ወይም ጥቅም ለውጥ የሚያሳዩ እና አብዛኛውን ጊዜ ለማሳሳት የሚደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

ከላይ በቀረቡት የተለያዩ ምክንያቶች መሰረት የከሚሴ ነዋሪዎች የሸኔ ሰራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱን ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለፅ ወጡ ተብሎ የቀረበው ተንቀሳቃሽ ምስል ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።   

Exit mobile version