የተጣሩ መረጃዎች

ምስሉ የግብፅ ወታደሮች ከሱዳን ጋር መሰማራታቸውን ያሳያል?

በ12 ጥር 2013 ዓ.ም Afmeer tv. የተባለ (ከ237,000 በላይ ተከታዮች ያሉት) የፌስቡክ ገፅ በርከት ያሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ከወታደሮች ጋር የሚያሳይ አንድ ምስል አጋርቷል። በፌስቡክ ልጥፉ ላይ በሶማሊኛ የተፃፈው ጽሑፍ “5000 የሚደርሱ የግብፅ መከላከያ ሠራዊት የሱዳን ጦርን ለማገዝ ሱዳን መድረሳቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አትተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሱዳንና ኤርትራ ድንበር አከባቢዎች ከ3000 በላይ የሚሆኑ የሱዳን ጦር ሠራዊት እየገሰገሱ ሲሆን ጉዳዩ እየተባባሰ ነው።” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ምስሉ በሱዳን የተሰማሩ 5,000 የግብፅ ወታደሮችን ስለማያሳይ እና መረጃውን ለመደገፍ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ልጥፉን ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ የታጠቁ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። በድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች በሱዳን ጦር ላይ ያደረጉት ጥቃት “ተገቢ ያልሆነ ጥቃት” ስትል ግብፅ አውግዛለች። ከዚህም በተጨማሪ ግብፅ ለሱዳን ሙሉ አጋርነቷን እና አገሪቷ ግዛቷን የመጠበቅ መብቷን መደገፏን አረጋግጣለች። ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ድንበር አከባቢዎች መላኳን እና ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጹ መረጃዎችም እየወጡ ይገኛሉ።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያመለክተው በልጥፉ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የሱዳንን ሀይሎች ለመደገፍ በሱዳን ድንበር ላይ ተሰማርተው ያሉ የግብፅ ወታደሮችን አያሳይም። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በ7 የካቲት 2010 ዓ.ም አህራም ኦንላይን (Ahram Online) በተባለ ድረ ገፅ ላይ የተለጠፈው ሲሆን በሲና በረሃ በአሸባሪዎች እና በወንጀል ቡድኖች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መወሰዱን ለማሳየት ጥቅም ላይ ውሏል። አህራም ኦንላይን ምስሉን የወሰደው ከግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር ነበር።

በቅርቡ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ እየጨመረ መምጣቱ እና ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ድንበሩ አካባቢዎች ማሰማራቷ እየተዘገበ ይገኛል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ሱዳንን ለመደገፍ በድንበሩ ዙሪያ የመጡ የግብፅ ወታደሮችን የማያሳይ በመሆኑ እና መረጃውን ለመደገፍ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ልጥፉን ሀሰት በማለት ፈርጆታል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ጥር 13 በደጀን ወረዳ በተከሰተ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት አልፏል?

ብሩክ አይናለም የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ በ13 ጥር 2013 ዓ.ም የጨዋዎች ግሩፕ በተባለ (ከ142,000 በላይ አባላት ባሉት) የፌስቡክ ግሩፕ ላይ በአማራ ክልል የመኪና አደጋ ደርሶ 39 ሰዎች መሞታቸውን የሚገልፅ መረጃ አጋርቷል። በልጥፉ ላይ የተፃፈው ፅሁፍ “… ከአዲስ አበባ ወደ በባህርዳር 65 ሠዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተገልብጦ የ39 ሠዎች ህይወት አልፏል። አደጋው የደረሰው ዛሬ (13 ጥር 2013 ዓ.ም) ከቀኑ 5:35 አውቶብሱ በአማራ ክልል፤ ደጀን ወረዳ፤ ባልበሌ ቀበሌ አካባቢ በሚገኝና 50ሜትር ጥልቀት ባለው ገደል ገብቶ ነው። ማንነታቸው ስላልታወቀ ከቤተሰቦቻቸው እናገናኛቸው አስክሬናቸው በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል ይገኛል…” ሲል ይነበባል። ልጥፉ በሌሎች የተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖች ውስጥ እየተሰራጨ እና በብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተጋራ ይገኛል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ በምስሉ ትክክለኛ ያለመሆን እና በልጥፉ ላይ በተገለፁት ማስረጃዎች ምክንያት ልጥፉ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል.

በዓለም ላይ ከፍተኛ የመኪና አደጋዎች ካሉባቸው አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች የሚታወቅ ነው። ባለፈው የበጀት ዓመት (2012 ዓ.ም) በመላው አገሪቱ በትራፊክ አደጋ የ4,133 ሰዎች ህይወት ማለፉም የሚታወቅ ነው። ስለዚህም አማራ ክልልንም ጨምሮ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የትራፊክ አደጋ ከባድ እና አሳሳቢ ችግር መሆኑ እርግጥ ነው።

ሆኖም አዲስ ዘይቤ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አናግራ በ13 ጥር 2013 ዓ.ም በደጀን ወረዳ 39 ሰዎችን የገደለ የመኪና አደጋ አለመኖሩ አረጋግጣለች። የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው “መረጃው በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉም አረጋግጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የሟቾቹ አስከሬን በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኝ የተገልፀ ቢሆንም በወረዳው ሪፈራል ሆስፒታል እንደሌለ እና በአቅራቢው ያለው ሪፈራል ሆስፒታል የሚገኘው ከደጀን በ61.5 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ደብረ ማርቆስ ከተማ መሆኑን ለማረጋግጥ ተችሏል።

በተጨማሪም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው መረጃውን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የተነሳው በ8 መጋቢት 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 (Boeing 737 MAX 8) አውሮፕላን በተከሰከስ ወቅት ለአደጋው ሰለባዎች በተደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መሆኑን ያሳያል። አደጋው የተከሰተው 1 መጋቢት 2011 ዓ.ም ላይ አውሮፕላኑ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ለማቅናት እንደተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሲሆን ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በመጨረሻም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ በአማራ ክልል በደጀን ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና የሟቾች አስከሬን በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል እንደሚግኝ የሚገልፀው የፌስቡክ ልጥፍ ትክክለኛ ያልሆነ እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

 

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

ምስሉ ከትግራይ ክልል በኤርትራውያን የተሰረቀ አህያን ያሳያል?

በ2 ጥር 2013 ዓ.ም World Page (ወርልድ ፔጅ) የተባለ ከ39,200 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በሚኒባስ ውስጥ ያለው አህያ ከትግራይ በኤርትራውያን ተሰርቋል በማለት ከዚህ በታች ያለውን ምስል ጋር አጋርቷል። ልጥፉ የወጣው በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እና በትግራይ አለመረጋጋት ተከትሎ ሲሆን በምስሉ ላይ የሚታየው አህያው በኤርትራውያን እንደተሰረቀ ለማሳየት በሚኒባስ መኪናው ታርጋ (የኤርትራ) ላይ ይጠቁማል። ልጥፉ በፌስቡክ ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት ሰአት ከ50 የሚበልጡ  ተጠቃሚዎች አጋርተውታል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ በኤርትራዊያን ከትግራይ የተዘረፈን አህያ እንደማያሳይ እና ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም  ጀምሮ በህወሃት በሚመራው የክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭት መነሳቱ የሚታወቅ ነው። የፌደራል መንግስትም በቅርቡ የህወሓትን ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ መኮንኖችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል ስራ ላይ እንደሚገኝ ያሳወቀ ሲሆን በወታደራዊ እንቅስቃሴ እና አለመረጋጋት መካከል የኤርትራ ወታደሮች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን አስተዳደር በመደገፍ በጦርነቱ ተሳትፈዋል የሚሉ ክሶች እና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንዳሉ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ብዙዎች በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ውስጥ ዘረፋ እያደረጉ ነው ሲሉ ይሰማሉ።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ18 ነሃሴ 2011 ዓ.ም  Reddit (ሬዲት) በተባለ የአሜሪካን በይነመረብ ላይ የተመሠረተ የምስል እና ቪዲዮ ማጋሪያ ማህበራዊ አውታር ላይ ነው። ከምስሉም ጋር “ይህች አህያ በሚኒባስ ወደ ቤቷ ልትሄድ ነው” የሚል ጽሑፍ ተያይዞ ተለቋል። 

የተቀናበረው ምስል

ዋናው ምስል

በእርግጥ የፌስቡክ ልጥፉ በተጋራበት ወቅት በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ግጭት የነበረ ሲሆን የኤርትራ ጦር በጦርነቱ እና በዘረፋው ውስጥ ተሳትፏል የሚሉ ክሶች እና ያልተረጋገጡ መረጃዎች ሲሰራጩ እንደነበር የሚታወስ ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ በኤርትራዊያን ከትግራይ የተዘረፈን አህያ እንደማያሳይ እና ምስሉ ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ በህወሃት ሀይሎች ላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ትግራይ እየገቡ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደሮችን የሚያሳይ ነው?

በ30 ታህሳስ 2013 ዓ.ም ደሃይ ውቅሮን ትግራይን የተባለ ከ1,950 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ ከዚህ በታች ያለውን ብዙ ወታደሮችን የጫኑ የጭነት መኪናዎችን እና በመንገድ ዳር ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚያሳየው ምስል የፌደራል ወታደሮች መሆናቸውን እና በህወሃት ሀይሎች ላይ እየተካሄደ ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ እየገቡ መሆናቸውን ገልፆ አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “እባክዎን ይህንን አስቸኳይ መረጃ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እንዲያየው አጋሩ። [አብይ አህመድ] ብዙ በወታደሮች  የጫኑ የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ከተሞች እየላከ ነው” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ከዚህ በታች ያለው ምስል ወደ ትግራይ የተላኩት የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደማያሳይ እና መረጃው ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት እና በህወሃት የሚመራው የትግራይ ልዩ ፖሊስና በፌደራል መንግስት ሀይሎች መካከል ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግጭት የተከሰተ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከተካሄደ ውጊያ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃይሎች መቐለ፣ ሽሬ፣ አዲግራት፣ አክሱም እና ሌሎችንም በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞችን መቆጣጠሩን መንግስት መግለፁ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በኋላ የፌደራል መከላከያ ሰራዊቱ እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በጋራ ባደረጉት ዘመቻ በ30 ታህሳስ 2013 ዓ.ም ስብሃት ነጋን እና በ2 ጥር 2013 ዓ.ም የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩትን አባይ ወልዱን ጨምሮ ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች መገደላቸው እና በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልፁአል

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው የፌስቡክ ልጥፍ ቢሰራጭም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባል የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ በፌስቡክ ልጥፉ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በትግራይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ትግራይ እየሄዱ የሚገኙ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አያሳይም። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በ9 ግንቦት 2009 ዓ.ም  The World (ዘ ወርልድ) በተባለ የአሜሪካን ዲጂታል ሚዲያ ድረ ገጽ ላይ ሲሆን በምስሉ ላይ የሚታዩት ወታደሮች በ4 ሰኔ 1990 ዓ.ም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ዛላምበሳ ግንባር በሚወስደው መንገድ ላይ ያልፉ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን የሚያሳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። 

እውነት ነው በፌደራል መከላከያ ሰራዊት እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይሎች መካከል በትግራይ ውስጥ ግጭት እና አለመረጋጋት ነበር። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ በልጥፉ ላይ የሚታየው ምስል ወታደራዊ ዘመቻ በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ትግራይ ሲገቡ የማያሳይ በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። .

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ በሱዳን ጦር የተያዙ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ያሳያል?

በ28 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Tigray Defence Force በሚል ስያሜ የተከፈተውና ከ16,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ገጽ በሱዳን ወታደሮች ላይ ወታደራዊ ጥቃት ሲያካሂዱ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሱዳን ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል በሚል በርካታ ወታደሮችን እና ታንኮችን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል። በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ የተፃፈው ጽሑፍ “በሁለት ግንባሮች ጥቃት ከፍቶ የሱዳንን ድንበር አቋርጦ የወጣውን ወራሪውን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የሱዳን ጦር በቁጥጥር ስር አውሏል” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ ከዚህ በታች ያለው ምስል በሱዳን ጦር በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተያዙትን የኢትዮጵያ ወታደሮችን የሚያሳይ ባለመሆኑ እና ልጥፉ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

 

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ በሁለቱ ሃገራት መካከል ግጭቶች መኖሩ እውነት ነው። የሱዳን ጦር በአል ገዳሪፍ፣ በሰላም ቢር እና ማሃጅ አካባቢዎችን ከኢትዮጵያ ጦር እና ከታጠቁ ሚሊሻዎች ማስመለስ መቻላቸውን መግለፁ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም በ28 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የተወሰዱትን በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉ ሁሉንም ግዛቶች መቆጣጠሩን አክለው መግለፃቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራቱ ጉዳዩን ለመፍታት እና ድንበሩ ለማካለል ድርድር እያደረጉ እንደቆዩም የሚታወቅ ነው፡፡

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው በፌስቡክ ልጥፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው 9 ታህሳስ 2013 ዓ.ም በሐዋር ዜና አገልግሎት ሲሆን የሱዳን ጦር በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ያሉትን የአቡ ቶዮር ተራራን ጨምሮ ሁሉንም ግዛቶች ተቆጣጥሯል ከሚል ጽሑፍ ጋር ተያይዞ ነበር በወቅቱ የወጣው። ዋናው ጽሑፍ ግን ስለ ምስሉ ምንም ዓይነት መግለጫ የለውም ወይም በምስሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች እነማን እንደሆኑ አይናገርም።

በድንበር አካባቢዎች በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ የፌስቡክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ በድንበር አካባቢ ባለው ግጭት ወቅት በሱዳን ጦር የተያዙ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደማያሳይ እና ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

በምስሉ ላይ የሚታዩት አልጋቸውን ይዘው ወደ ምሽጉ የመጡ የሱዳን ወታደሮችን ናቸው?

በ 27 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Selam Nkulu (ሰላም ንኩሉ) በተባለ ከ3,500 በላይ ጓደኞቻቸው ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በተካሄደው ግጭት ወቅት አነስተኛ ምሽግ ውስጥ ምግብ እና የመኝታ ቁሳቁሶች ይዘው የወጡ ወታደሮችን የሚያሳይ ነው በማለት አንድ ምስል አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “የሱዳን ወታደሮች አልጋቸውን ይዘው ወደ ምሽግ መጡ። ሻዕቢያ (ኤርትራ) እና የፎጣ ለባሾች (የአማራ ክልል ኃይሎች) ካዩ ዛሬ ውጊያው ሊጀምሩ ይችላሉ። ኦህህ እናንተ ሱዳኖች ቁጭ ብላቹ በምግቡ ተደሰቱ” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከዚህ በታች ያለው ምስል ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እና ልጥፉ ስላቅ እንደሆነ አረጋግጧል። 

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። በ11 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ስር የነበረውን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ግዛቶች የሱዳን ጦር ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። በድንበር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ሱዳን ወታደሮችን ወደ ድንበሩ አካባቢዎች እያሰማራች መሆኗን የተለያዩ ዘገባዎች አውጥተዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በ9 ታህሳስ 2013 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከ30 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የተደራጁ ጥቃቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች ተዘርፈዋል፣ ካምፖች ተሰብረዋል፣ አርሶ አደሮች የራሳቸውን እርሻ እንዳያጭዱ ተስተጓጉለዋል እንዲሁም በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል ብለዋል። ሁለቱ ወገኖች ሪፖርታቸውን ለሁለቱ አገራት አመራሮች ለማቅረብ የተስማሙ እና የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን የድንበር ማካለል ስራው በፍጥነት እንዲጀመር ወስነዋል።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለው የምስል ማጣሪያ፣ የፌስቡክ ልጥፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አለመሆኑን ያሳያል። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው 22 ግንቦት 2012 ዓ.ም በፌስቡክ ላይ ሲሆን የተለቀቀውም “በጠረፍ ድንበሮች በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወታደሮች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ” ከሚል ጽሑፍ ጋር ነበር።

 

ድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች መከሰታቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት በምሽግ ውስጥ የመኝታ ቁሳቁሶችን እና ምግብ ይዘው የሚታዩትን ወታደሮች የሚያሳየው ይህ ምስል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር እንደማይገናኝ እና የፌስቡክ ልጥፉ ስላቅ መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ ከአዲግራት ጥሕሎ የዘረፈውን የኤርትራ ወታደር ያሳያል?

ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም Tirhas Tesfay የተሰኘ የፌስቡክ አካውንት በፌስቡክ ገጹ ላይ ከዚህ በታች ያለውን ምስል አንድ የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሰረቀ ከሚል ጽሁፉ ጋር አያይዞ በፌስቡክ ልጥፉ አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው የፌስቡክ ጽሁፍ “ሰበር ዜና: አንድ የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሲሰርቅ በአይኔ አይቻለሁ” ይላል። ጥሕሎ ከገብስ ዱቄት የሚሰራ በሰሜን ምስራቅ የትግራይ ክፍልና በደቡብ ኤርትራ የሚዘወተር ባህላዊ ምግብ ነው። ልጥፉ በፌስቡክ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቶ ምስሉ እስከተጣራበት ጊዜ ድረስ 184 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አጋርተውታል። ሀቅቼክ ልጥፉን ከመረመረ በኋላ ምስሉ ከአዲግራት ጥሕሎ የሰረቀ የኤርትራ ወታደርን እንደማያሳይ አረጋግጧል። በመሆኑም የፌስቡክ ልጥፉን ስላቅ በማለት ፈርጆታል።

በትግራይ ክልል ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በህወሃት በሚመራው የታጠቁ የክልል ኃይሎችና በፌደራል  መንግስት በሚመሩ ኃይሎች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። የክልሉን አለመረጋጋት ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደርን በመደገፍ የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ላይ ተሳታፊነት እንደነበራቸው የሚገልፁ የተለያዩ ክሶች እና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ቀርበዋል። በተጨማሪም ብዙዎች በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ውስጥ ዘረፋ እያካሄዱ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው ከአዲግራት ጥሕሎ የሰረቀ ኤርትራዊ ወታደር እንደሆነ የሚገልፅ አንድ የፌስቡክ ልጥፍ ብቅ ብሏል። ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የምስል መመርመሪያ ዘዴን በመጠቀም የምስሉ አመጣጥ ሲጣራ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ናይሮቢ ኒውስ  Nairobi News በተባለ የኬኒያ የዜና እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋም መሆኑ ታውቋል። በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው (ፎቶ አንሺ ኤቫንስ ሀቢል) የኬኒያ መንግስት  በናይሮቢ ከተማ የተገነቡ  ህገወጥ ቤቶችን በሚያፈርስበት ወቅት ከመኖሪያ ቤቱ ኡጋሊ  (የኬንያ ገንፎ) ያዳነ አንድ የኬንያ ዜጋ ነው። በ Nairobi News  ላይ የታተመው የሰውየውን ታሪክ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይቻላል።

  

ይህ የፌስቡክ ጽሁፉ በወጣበት ወቅት በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት የኤርትራ ጦር በጦርነቱ ላይ ተሳታፊ እንደነበረና በርካታ ዘረፋዎችም እንደነበሩ የሚገልጹ የተለያዩ ክሶችና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ሲቀርቡ ነበር። ነገር ግን ሀቅቼክ ምስሉን ከመረመረ በኋላ የፌስቡክ ጽሁፉ ላይ እንደተገለፀው የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሲሰርቅ የሚያሳይ ምስል እንዳልሆነ አረጋግጧል። ስለዚህ የፌስቡክ ጽሁፉ ምስሉን በተሳሳተ መንገድ በማቅረቡ ስላቅ ተብሎ ተፈርጇል። 

አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ በትግራይ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት አራተኛውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ብርጌድ ያጠፋውን ኃይል ያሳያል?

በ21 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Mahder Kiya ማህደር ቅያ የተባለ (ከ10,000 በላይ ተከታዮች ያሉት) አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ከዚህ በታች ያለውን የአንድ ኦራል የጭነት መኪና እና አንድ ወታደር ምስል በህወሃት የሚመራው ኃይል ከአድዋ ወደ ሀውዜን ሲጓዝ  አንድ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ብርጌድ ደምሷል ከሚል ፅሁፍ ጋር አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው ፅሁፍ “…የ 33 ኛው ክፍለ ጦር ከአድዋ ወደ ሃውዜን በእዳጋ አርቢ በኩል ሲጓዝ በነበረ ሀይል ተመቶ ሙሉ በሙሉ አድብቶ 144 ወታደሮች እና ሁሉም የጦር መኮንኖች ተያዙ…” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ምስሉ ትግራይ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት አራተኛውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ያጠፋውን በህወሃት የሚመራ ሃይል የማያሳይ በመሆኑ እና ምንም ግንኙነት እንደሌለው በማረጋገጡ መረጃውን ሀሰት ሲል ፈርጆታል።

ከ28 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል መንግስት እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ የፖሊስ ኃይል እና ሚሊሻ መካከል በትግራይ ክልል ውስጥ ግጭት መከሰቱ እውነት ነው። የፌዴራል መንግሥት ጦርነቱ መጠናቀቁን እና ቀጣዩ እርምጃ የህውሃት አመራሮችን አድኖ ማግኘት መሆኑን ቢናገርም፤ በፌዴራልና በክልል ኃይሎች መካከል ያለው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ያልተረጋገጡ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያመለክተው ምስሉ የአራተኛውን ብርጌድ ወታደሮች እና የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን አያሳይም። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ የወጣው ህውሓት ሀወልቲ በተባለ የፌስቡክ ገጽ 1 ህዳር 2013 ዓ.ም ሲሆን ትግራይ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀች መሆኑንና በትግራይ ላይ ጦርነት ለማካሄድ በሚደፍሩ ጠላቶች ላይ ድል አድራጊ ይሆናል ከሚል ፁሁፍ ጋር ነበር በወቅቱ የተለቀቀው። 

ብመሆኑም በፌዴራል እና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የተደረገው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ቢኖሩም ሀቅቼክ የፌስቡክ መረጃውን መርምሮ ምስሉ በህወሃት የሚመራው ኃይል አራተኛውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን መያዙን የማያሳይ ስለሆነ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ሀሰት መሆኑን አርጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

ምስሉ ትልልቅ መሳሪያዎችን የታጠቀ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የሚያሳይ ነው?

Waan Ofii (ዋን ኦፊ) የተባለ ከ39,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ በታህሳስ 20፣  2013 ዓ.ም በለቀቀው የፌስቡክ መረጃ “ከፍተኛ ቁጥር ያለው እና ትልልቅ መሳሪዎች የታጠቀ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ እየተጓዘ ነው”  በማለት ተከታዩን ምስል አያይዞ ለቋል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ መረጃውን ለመደገፍ የተለቀቀው ምስል በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ስለሆነ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ላይ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በ8 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን ጦር አከራካሪውን የድንበር ግዛት መቆጣጠሩ እና ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ላይ መሆኑን በተለያዩ የመረጃ መረቦች እየተዘገበ ይገኛል። በ20 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮ-ሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ ለማብራራት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደነበረም የሚታወስ ነው። በወቅቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ (የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ)  ከ30 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የተደራጁ ጥቃቶች እንደነበሩ ገልፀው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች እየተዘረፉ ፣ ካምፖቻቸው እይተወረሩ እና አርሶ አደሮች የራሳቸውን እርሻ እንዳያጭዱ እንቅፋት እየሆኑባቸው እንዳለ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ንፁሀን መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን አክለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ሁለቱም አገራት በራሳቸው ወገን ያለውን ሪፖርት ለማቅረብ የተስማሙ ሲሆን የድንበር ማካለል ስራውም በፍጥነት እንዲጀመር ወስነዋል።

ሆኖም ቲን ዐይ (TinEye) የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው የሱዳኖች ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየገሰገሰ ነው የሚለውን መረጃ ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ29 ሰኔ 2010 ዓ.ም Haber7.com (ሀበር 7 ዶት ኮም) በተባለ የቱርክ የዜና ድረ-ገፅ ሲሆን የየመን ጦር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተወሰኑ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ እንደነበር ለመግልፅ ነበር ምስሉ ጥቅም ላይ የዋለው። 

  

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወታደራዊ ኃይል መካከል ግጭት መኖሩ እውነት ነው፤ ሆኖም ሀቅቼክ የፌስቡክ መረጃውን መርምሮ ምስሉ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ እየገሰገሰ መሆኑን የማያሳይ እና በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

በምስሉ ላይ ያሉት ሁለቱ ሰዎች በቅርቡ በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት ወቅት በኤርትራ ወታደሮች የተገደሉት ናቸው?

ኣርሓ ወያናይ ተጋሩ የተባለ ከ5000 በላይ ጓደኞች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ የሁለት ሰዎችን ምስል በኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ተገደሉ በማለት ታህሳስ 17፣ 2013 ዓ.ም ለቆ ነበር። ምስሉን ለመደገፍ በትግርኛ የተጻፈው ጽሑፍ “….የአውሬዎች ዘር! የኤርትራ ወታደሮች እነዚህን ሁለት ንፁሀን ሰዎች በትግራይ ገደሉ ፡፡ በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ!” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ሁለቱ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች ሲገደሉ የማያሳይ እና ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል ፡፡

ከጥቅምት 28፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል መንግስት እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ መካከል በትግራይ ክልል ውስጥ ቀጣይነት ያለው ግጭት ተከስቷል። ግጭቱን ተከትሎም የፌደራል መንግስት በኤርትራ መንግስት ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ ተደጋጋሚ ያልትጣሩ መረጃዎች እና ክሶች ሲወጡ ይሰማሉ። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ኃይሎች በወታደራዊ ዘመቻው ውስጥ እንዳልተሳተፉ ደጋግሞ አስተባብሏል

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው በፌስቡክ ተጠቃሚው የተለቀቀው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ህዳር 21፣ 2010 ዓ.ም awaale afcad በተባለ የትዊተር ገፅ ሲሆን ከምስሉ ጋር ተያይዞም “በሊቢያ ውስጥ” የሚል ፅሁፍ ይነበባል። ምስሉ ከሌሎች ሦስት ምስሎች ጋር ተያይዞ ነበር የተለቀቀው። 

በህወሃት በሚመራው የትግራይ ክልል ኃይል እና በፌዴራል መከላከያ ሰራዊት መካከል በተነሳው ግጭት ኤርትራ ተሳትፋለች የሚሉ ክሶችና ያልተረጋገጡ መረጃዎች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ሁለት ሰዎችን የሚያሳየው ምስል በትግራይ ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን የሚያረጋግጥ ባለመሆኑን እና ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ምስል በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Exit mobile version