ሀሰት፡ ቢቢሲ አማርኛ ከፋኖ አስረስ ማረ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ ላይ ዘገባ አልሰራም

በግጭቶች ጊዜ የሀሰት መረጃ መስፋፋት ይጨምራል። በቅርቡ በፌስቡክ በሰፊው የተጋራ ፅሁፍ በጎጃም ክፍለጦር ውስጥ የፋኖ የፖለቲካ መምሪያ ሀላፊ የነበረው አስረስ ማረ ለቢቢሲ የሰጠው ቃለምልልስ በሚል ተሰራጭቷል።

በመግለጫው “ከጠላት ጋር እያደረግነው ባለው ውጊያ ብልጫ ተወስዶብናል ነገር ግን ለሽንፈት የሚያበቃ አይደለም” የሚለው ጥቅስ ተያይዞ ተሰራጭቷል። ይህ የፌስቡክ ልጥፍ አቶ አስረስ ማረ በፋኖ እና በመከላከያ መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት መንግስት(መከላከያ ሰራዊት) የበላይነቱን እየወሰደ መሆኑን ለቢቢሲ ዜና አማርኛ እንደገለጹ ይናገራል። 

ነገር ግን በቢቢሲ ዜና የአማርኛው ድረ-ገጽ ላይ እንዲህ ያለ ጽሁፍ ባለመኖሩ ሃቅቼክ ምርመራ አድርጎ ይህንን ጽሁፉን ከታማኝ ምንጮች አለመወሰድ በማየት መሠረተ ቢስ እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

ከፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ ምስል

ጎጃም በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ የኢትዮጵያ አማራ ክልል ዞን ነው። “ፋኖ” የሚለው ስያሜ “የነጻነት ታጋይ” የሚለውን ትርጓሜ የሚገልጽ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የአማራን ህዝብ እንወክላለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ይጠቀሙበታል።  

ይህ የተሳሳተ ጽሁፍ ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ቢቢሲ ዜና አማርኛ እንደዘገበው ተደርጎ መሰራጨቱ ነው። 

ቢቢሲ አማርኛን በመጥቀስ ልጥፉን ያጋሩ ፌስቡክ አካውንቶች ምስል

አስረስ ማረ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል እየተካሄድ ባለው ጦርነት በጎጃም ያለውን የፋኖ ሚሊሻ ቡድን እየመራ ይገኛል። 

ሀቅቼክ የቢቢሲ አማርኛ ባለፉት 3ወራት የሰራቸውን ዘገባዎች ላይ ማጣራት ያደረገ ቢሆን በቢቢሲ አማርኛ እና በፋኖ ወታደር አስረስ ማሬ መካከል የተደረገውን ውይይት የሚያሳይ የዜና ዘገባ አላገኘም። እንዲሁም በፌስቡክ የተሰራጨው ልጥፍ ላይ ቢቢሲ ዘግቦበታል የተባለበትን ቀን አላስቀመጠም።

ይህ ስክሪን ሪከርድ የቢቢሲ አማርኛ ያለፉት 3 ወራት ዘገባዎችን ያሳያል  

ቢቢሲ-አማርኛ የብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ሲሆን ዜና እና መረጃን ለአማርኛ ተናጋሪ እና ታዳሚዎች በዋናነት በኢትዮጵያ ፣ በአፍሪካ ቀንድ አህጉራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ይዳስሳል። 

በተጨማሪም ሀቅቼክ በእይታ ምርመራ ቴክኒኮች በጥልቀት ሲመረመር ፣ የተያያዘው ምስል የተቀናበረ ስለመሆኑ ፍንጭ አግኝቷል።  

የቢቢሲ አማርኛ ፖስት ተብሎ የተያያዘው ልጥፍ ምስልም በሀቅቼክ ምርመራ አስረስ ማሬ ዳምጤ በሚል የተሰየመ የፌስቡክ ገፅ ላይ እ.ኤ.አ ሰኔ 20 ፣ 2022 የመግለጫ ምስል ማዘመን (profile picture update) ላይ አግኝቶታል።

እ.ኤ.አ. ሰኔ 20 ፣ 2022 ከተሰራጨ ልጥፍ የተወሰደ ምስል

አንዳንድ ጊዜ የዜና ድረ-ገፆች መረጃዎችን ካጋሩ በኋላ መልሰው ሲያነሱት ይታያል። ለዚህም ሀቅቼክ በማህበራዊ ሚድያ ላይ ስለተሰራጨው ልጥፍ ሀቅቼክ የቢቢሲ አማርኛ አርታኢ የሆኑትን አቶ አሻግሬ ሀይሉን አነጋግሯል። እሳቸውም ቢቢሲ አማርኛው ይህን ዘገባ እንዳልሰራው እና መረጃውም የሀሰት ፈጠራ መሆኑን አሳውቀውናል።

አያይዘውም አንባቢዊች ዜናዎችን በቢቢሲ ስም ሲሰራጩ መረጃው ትክክለኛ መሆኑን ለማወለማወቅ ወደ ይፋዊ የቢቢሲ አማርኛ ድረ-ገጽ https://www.bbc.com/amharic የሚወስድ አገናኝ(link) እንዲፈልጉ መክረዋል።

ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሀቅቼክ ልጥፉን ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

Exit mobile version