ሀሰት፡ ምስሉ በቅርቡ በአማራ ክልል አጣዬ ከተማ የተከሰተውን ግጭት አያሳይም

ከሰሞኑ በአጣዬ እና አካባቢው ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የሚቃጠሉ ቤቶችን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚድያው ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።

በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከ5ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ከሰሞኑ በአማራ ክልል አጣዬ ከተማ በተከሰተው ግጭት የሚቃጠሉ ቤቶች የሚያሳይ ምስል በሚል መግለጫ ስር አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።


ይህ ምስል ከሌሎች ሁለት ምስሎች ጋር በመሆን ሲጋራ የቆየ ሲሆን ከሁለት ሰዓታት በኋላ በአጣዬ ከተማ ከተከሰተው ግጭት ጋር በማያያዝ ከ5ሺህ በላይ ተከታይ ባለው አንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ ለመጀመርያ ጊዜ ከሶስት አመት በፊት በአንደ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጋርቶ የነበረ እንደሆነ እና አሁን በአጣዬ እና አካባቢው ከተከሰተው ግጭት ጋር እንደማይገናኝ አረጋግጦ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።

ሊንክ

ሊንክ

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ልዩ ዞኖች እንዲሁም አጎራባች አካባቢዎች ላይ ተከታታይ የሆነ ግጭት እና ግድያዎች ተፈፅመዋል። በጥቅምት 2011 ዓ.ም የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ በጊዜው በአካባቢው በተከሰተው ግጭት ሶስት ሰዎች እንደሞቱ ገልጿል።

ከሁለት አመታት በኋላ በ2013 ዓ.ም በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ቦታዎች በተለይም በአጣዬ ከተማ ላይ ከባድ ግጭቶች ተከስተው ነበር።   

ግጭቱ ለሁለት ወራት ያክል ቆይቶ የነበረ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ሰዎች ሲሞቱ በግጭቱ የቆሰሉም አሉ። በዚህ ግጭት ምክንያት በመጋቢት እና ሚያዝያ 2011 ዓ.ም ላይ ከ3 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ ከ3000 በላይ ቤቶች በቃጠሎ ምክንያት ወድመዋል።    

አንድ አራተኛ የሚሆነው የአጣየ ከተማ ክፍል በዚህ ግጭት ምክንያት ወድሟል። ይህ ግጭት ካስከተለው ጉዳት በኋላ የአማራ ክልል መንግስት ለመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን ወደ 1.5 ቢልዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር።  

በሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ልዩ ዞን አካባቢዎች ላይ ግጭቶች ተከስተው የነበረ ሲሆን ይህ ግጭት ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ልዩ ዞን በሚገኙት የአጣዬ እና የጀውሃ ከተሞች አካባቢ ግጭት መከሰቱን የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ሪፖርቶች ያሳያሉ። 

ይህ መረጃ ላይ መሰረት በማድረግ ምስሉ በአጣዬ ከተማ የተፈፀመ ነው በማለት በተለያዩ የፌስቡክ ገፆች ላይ ሲዘዋወር ቆይቷል።


ይህ ምስል በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ በሁለት የፌስቡክ ገፆች ላይ የተጋራ ሲሆን ሁለቱም የፌስቡክ ገፆች እያንዳንዳቸው ከ5ሺህ በላይ ተከታዮች አሏቸው።  

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ የቆየ እና ከሰሞኑ በአጣዬ እና አካባቢው ከተፈጠረው ግጭት ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ችሏል።

ምስሉ ከሶስት አመት በፊት ሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ላይ በአንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጋርቶ ነበር። ከምስሉ ጋር ያለው ፅሁፍ በወቅቱ በአጣዬ ከተማ በእሳት ቃጠሎ የተጠቃ ቤተክርስትያን እንደሚያሳይ ይገልፃል። ስለዚህ ሀቅቼክ መረጃውን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።

Exit mobile version