ከ5ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ ኢታማጆር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋኖ ታጣቂዎች ታንኮችን ጨምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያዎች ማርከዋል ብለዋል በሚል አንድን ቪድዮ አጋርቷል።
ይህ ጽሁፍ እስከታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ 1300 ግብረመልስን ስያገኝ ከ90 ሺ በላይ ተጠቃሚዎች አይተውታል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪደዮው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያዎችን ማረኩ ማለታቸውን እንደማያሳይ አረጋግጧል። በዚህም የፌስቡክ ፖስቱ ሀሰት ተብሏል።
እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚታወቁት ታጣቂዎች ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል።
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሀላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት በ”አክራሪ” ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ባዘዘበት ወቅት የጸጥታው ቀውስ ተባብሷል።
በነሀሴ 2023 እ.አ.አ በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ የክልሉን ትላልቅ ከተሞች ለመቆጣጠር ችለው ነበር። ለዚህ ምላሽ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት ሁኔታውን መቀልበስ ችሏል። መንግስት ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ ብዙ ቦታዎችን መልሶ ቢቆጣጠርም፣ በክልሉ የነበሩት ግጭቶች ግን ተባብሰው ቀጥለዋል።
ሀቅቼክ የፋኖ ታጣቂዎች መሳሪያ እየማረኩ ነው የሚሉ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ዜናዎችንም ተመልክቷል። ሆኖም ከእነዚህ ልጥፎች መካከል አንዳንዶቹ በውሸት እና በአሮጌ ምስሎች የታጀቡ ነበሩ።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ አንድ የፌስቡክ ገፅ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ታንክን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የጦር መሳሪያዎቻችንን ወስደውብናል” ሲሉ የሚሰሙበት አጭር ቪዲዮ በማጋራት፤ እነዚ በኢታማጆር ሹሙ የተጠቀሱ መሳሪያዎች በፋኖ የተፋረኩ እንደሆኑ አመላክቷል።ነገር ግን ሀቅቼክ የቪዲዮ ክሊፑ ይህንን እንደማያሳይ አረጋግጧል። ቪድዮው የተወሰደው እ.አ.አ በጥቅምት 2021 በዩቲዩብ ላይ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከታተመው ቪዲዮ ሲሆን፤ ይህም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ስለነበረው ግጭት ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ተቆርጦ የተወሰደ ነው። በቪዲዮው ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የህወሓት ሃይሎች ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ታንኮችና ሌሎች መሳሪያዎችን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
ስለዚህ ሀቅቼክ ይህ የፌስቡክ ፖስት የቆየና ትክክለኛ ያልሆነ ቪዲዮን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።