በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም በጎፋ ዞን, ኢትዮጵያ የደረሰውን ከባድ የመሬት መንሸራተት ያሳያል በሚል የመግለጫ ፅሁፍ የተጋራ አንድ የቲክቶክ ቪዲዮ ከመቶ ሺህ ጊዜ በላይ ሲጋራ ከሶስት ሚሊዮን በላይ እይታዎችን ማግኘት ችሏል።

በሐምሌ ወር ቲክቶክ ላይ የተጋራው ቪዲዮው የሚያሳየው የመሬት መንሸራተት ሲሆን ፍርስራሾች ፣ ዛፎች እና አቧራ እንደጎርፍ ሲወርድ የሚያሳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ቪድዮ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ውስጥ የተከሰተ እንደሆነ እና በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 300 እንደደረሰ ይገልፃል።

እንደ ቢቢሲ እና ሌሎች የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ፤ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም አመሻሽ እና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ማለዳ ላይ የመሬት መንሸራተት ተከስቷል።

ቪዲዮ

አልጄዚራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቦታው ተሰብስበው እና ሌሎች ከሥሩ በአደጋው ወቅት ፍራሹ የተጫነባቸውን ሰዎች ፍለጋ አፈር ውስጥ ሲቆፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮም አጋርቷል።

እሁድ እለት የጣለው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተትን ሲያስከትል በአቅራቢያው ካሉ መንደሮች የመጡ የፖሊስ መኮንኖች፣ መምህራን እና ነዋሪዎች በሰኞ ዕለት ነፍስ የማዳን እና የሞቱ ሰዎችን አስከሬኖች የማውጣት ስራዎችን እያከናወኑ በነበሩበት ወቅት ሁለተኛ የመሬት መንሸራተት ተከስቷል።

እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) መረጃ ከሆነ በመሬት መንሸራተት አደጋው የሟቾች ቁጥር ወደ 257 ከፍ እንዳለ እና ቁፋሮው ሲጠናቀቅ ቁጥሩ እስከ 500 ሊደርስ ይችላል የሚል ግምትን አስቀምጧል። ከሟቾች በተጨማሪም በአደጋው ከ15,500 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ቢያንስ 1,320 ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት እና 5,293 ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ይገኙበታል።

ሀቅቼክ በቲክቶክ ላይ የተሰራጨውን ይህን ቪድዮ በቅርበት ሲመረመር መግለጫው እንደሚያትተው በኢትዮጵያ ፣ ጎፋ ዞን የተከሰተውን ሳይሆን በፈረንጆቹ 2022 በህንድ, ሜጋላያ ግዛት የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ የሚያሳይ ነው።

ቪዲዮ

CNN-News18 የተሰኘው የህንድ ሚድያ እንደዘገበው ከሆነ በሰሜን ምስራቅ ህንድ ሜግሃልያ ግዛት የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ተከስቶ ነበር። ይህ የዜና ተቋምም ይህን ክስተት የሚያሳይ ቪድዮ ብማህበራዊ ገፁ ላይ አጋርቶ ነበር።

ምንም እንኳን ቪዲዮው በተፈጠረው መሬት መንሽራተት አደጋ ክስተት ላይ መሰረት አድርጎ ቢሰራጭም ሀቅቼክ ይህ ቪድዮ በሀገራችን የተከሰተውን ሁኔታ ስለማያሳይ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts