በኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከ7 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ የአማራ ብሄር ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ላይ እየተገደሉ ነው በማለት አንድ ምስል አጋርቶ ነበር።
ይህ የፌስቡክ ገጽ በአያያዘው ምስል ላይ “በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለ ዘር ማጥፋት” የሚል ፅሁፍ አድርጎበታል።
ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ39 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በተለያዩ የእርስ በርስ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። በእነዚህ ጊዜያቶችም ውስጣዊ የድንበር ግጭቶች ፤ የብሄር ግጭት ፤ ሞት እና መፈናቀሎችም ተከስተዋል።
ከነዚህ ክስተቶች መሃልም በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ተከስቶ የነበረው እና ለሁለት አመት ቆይቶ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ይጠቀሳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በተደጋጋሚ የተለያዩ የጅምላ ግድያዎች ፤ ሞት እና መፈናቀሎች እየተሰሙ ይገኛሉ።
በዚህም ግጭት ምክንያት ንፁሃን የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች የዚህ ግጭት ሰለባ ሆነዋል። የዜና ሪፖርቶች በነዚህ ግጭት በተባባሰባቸው አካባቢዎች የአማራ ብሄር ተወላጆች እንደሚገደሉ እና እንደሚፈናቀሉ ያሳያሉ።
ይህን የሰዎች ሞት እና መፈናቀልን ተከትሎ መንግስት ድርጊቱን የፈፀመው ኦነግ ሸኔ ነው ቢልም ኦነግ ሸኔ በተቃራኒው ነገሩን ሲያስተባብልና መንግስትን ሲከስ ቆይቷል።
ይህ የፌስቡክ ፖስትም በዚህ ሀሳብ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።
ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሠረት ምስሉ የቆየ እና በሐምሌ 2012 ዓ.ም በአንድ የዜና ድረገፅ ላይ ተጋርቶ የነበረ ነው።
ምስሉ ለመጀመርያ ግዜ በአንድ የዜና ድረገፅ ላይ የተጋራ ሲሆን፤ ሁለት የሶማልያ ወታደሮች በደቡብ ምዕራብ ሶማልያ በምትገኘው እና ባይዶአ ተብላ በምትጠራው አካባቢ የ10 አመት ወንድ ልጅ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈፀማቸውን ተከትሎ በአደባባይ ተሰቅለው በጥይት እንደተገደሉ የሚያሳይ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ይህ የዜና ምንጭ ሁለቱ ወታደሮች በሶማልያ የ60ኛ ክፍለ ጦር ወታደሮች በጥይት ተመተው ከመገደላቸው በፊት በከተማዋ ውስጥ ታስረው ሲዞሩ እና በህዝብ ፊት ሲታዩ እንደነበረ ዘግቧል።
ስለዚህ ሀቅቼክ ይህ የፌስቡክ ፖስት የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።