ከ700ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም “የአብይ መንግስት ወደ አስመራ ከደብረዘይት አየር ሀይል ግቢ በአንቶኖቭ ወታደሮችን ሲያመላልስ የሚያሳይ ቪድዮ ተመልከቱ። ስለ ሰላም እያወራን ወታደር ማሰማራት ትክክል አየደለም ለማንኛውም ሰራዊታችን TDF አይዘናጋም።” የሚል ፅሁፍ በማያያዝ አንድ የ25 ሰከንድ ርዝመት ያለው ቪድዮ አጋርቶ ነበር።”

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ11ሺህ በላይ እይታን ማግኘት ችሏል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪድዮውን መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 


መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር ሙሳፋኪ ሀማት ለዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ደብዳቤ ጽፈው ነበር። ህብረቱ መስከረም 28 ፤ 2015 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ ወደነበረው የሰላም ድርድር በደብዳቤው ጋብዟቸዋል።  

መሰከረም 25 ፤ 2015 ዓ.ም ህወሓት ከአፍሪካ ህብረት የቀረበለትን የድርድር ጥያቄ መቀበሉን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። 

የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን የድርድር ጥያቄን እንደሚቀበለውና ከዚህ በፊትም የፌደራል መንግስት ግጭቱን ለማስቆም እና ሰላምን ለማውረድ የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ እንደቆየ ገልጿል።    

ሀቅቼክ በፌስቡክ ገፁ ላይ የተጋራውን ቪድዮ ለማጣራት ባደረገው ጥረት ነሀሴ 23 ፤ 2014 ዓ.ም የ4 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ርዝመት ባለው ቪድዮ ውስጥ አግኝቶታል። ይህ ቪድዮም ከ9ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገፅ ላይ “የኢፌዴሪ የአየር ሀይል ልምምድን ተመልከቱ” በሚል የፅሁፍ መግለጫ ተጋርቶ ተገኝቷል። ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስም ቪድዮው ከ500 በላይ እይታን ማግኘት ችሏል።    

ከዚህ በተጨማሪ ሀቅቼክ በሁለቱ ቪድዮዎች ውስጥ ያሉ ተመሳሳይ ምስሎችን ለመመልከት ጥረት ያደረገ ሲሆን ከዚህ በታች የተመለከቱት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።     

ምስል አንድ

ምስል ሁለት 

በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ ቪድዮው የቆየ እና ይህ የፌስቡክ ገፅ ካጋራው መረጃ ጋር ፍጹም ያማይገናኝ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። ስለዚህ ሀቅቼክ ቪድዮውን መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts