በትግራይ ክልል ድርቅና የረሃብ ችግር መከሰቱን ዘገባዎች ቢያመለክቱም ይህ ቪዲዮ ግን በትግራይ የተራበ ሕፃንን የሚያሳይ አይደለም። 

ህዳር 18 2016 አንድ የፌስቡክ ገጽ በትግራይ የተራበ ጨቅላ ህጻን ነው በማለት ይህንን ቪድዮ አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ ቪዲዮው ወደ 8,000 የሚጠጋ እይታን ያገኘ ሲሆን ከ121 ጊዜ በላይም ተጋርቷል።

ከዚሁ ቪዲዮ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ልጥፍች በሌሎች የፌስቡክ ገጾች ላይም ተጋርተዋል። ተመሳሳይ ቪዲዮ በሌላ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወደ 5,000 የሚጠጋ እይታን ያገኘ ሲሆን ከ80 ጊዜ በላይም ተጋርቷል።

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከፍተኛ ድርቅ እና የረሃብ ቀውስ መከሰቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአበርገለ ወረዳ ብቻ ከ19,000 ሄክታር ሰብል 17,000 ሄክታር ሰብል ለድርቅ መጋለጡን የትግራይ ክልል ግዝያዊ መንግስት አስታውቋል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤድ) እና የተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ፕሮግራም (ዳብልዩ ኤፍ ፒ) በመንግስት ባለስልጣናት የእርዳታ ስርቆትን ክስ በመጥቀስ ዕርዳታውን አቁሟል።

በህዳር 3፣ 2016 ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ከስድስት ወራት እገዳ በኋላ በኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ ስርጭትን በታህሳስ ወር እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በ2016 ጥቅምት 20 የወጣው የኦቻ ዘገባ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአማራ እና በትግራይ ክልል በድርቅ መሰል ሁኔታዎች ተጎጂ ሆነዋል ብሏል።

በተጨማሪም የትግራይ ክልል አስተዳደር በወጀራትና አጽቢ ወረዳ ድርቅና ረሃብ መከሰቱን ገልጿል

ከሰሞኑ በትግራይ ክልላዊ መንግስት አበርገሌ ወረዳ ከፍተኛ ረሃብ እንዳለ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ አየተጋራ ቆይቷል።

በተጨማሪ እነዚህ ልጥፎች በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ሰዎች የገንዘብ ማሰባሰብያ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን ጀምረዋል።

በረሃብ የገንዘብ ማሰባሰብያ ዘመቻ መካከል አንድ የተራበ ጨቅላ ሕፃንን የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው ሲጋራ ነበር።

ነገር ግን ትክክለኛው ቪዲዮ ከሶስት ሳምንት በፊት ማለትም ህዳር 2፣ 2016 በቲክቶክ ላይ ተጋርቶ ተገኝቷል። 

የተጋራው ቪዲዮ በመጀመሪያ ካቶ ኒኮደም በተባለ የቲክ ቶክ አካውንት ላይ ተጋርቶ ተገኝቷል። ይህ የቲክ ቶክ አክውንት 1.8 ሚሊዮን ተከታዮች ሲኖሩት 34.5 ሚሊዮን የሚሆን ግብረመልስን አጊንቷል።

ይህ ኒኮደም የተባለ ግለሰብ በዩጋንዳ ወላጅ አልባ ህጻናትን የሚረዳ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሪ እንደሆነ ይገልጻል። ለዚህ ሃሰተኛ መረጃ ጥቅም ላይ የዋለውን ቪዲዮ ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ግለሰብ የቲክቶክ አካውንት ላይ እንክብካቤ እያገኙ ያሉ ሕፃናትን የሚያሳዩ ተመሳሳይ ቪዲዮዎችን በተደጋጋሚ ይጋራሉ።

ይህንኑ ህጻን ልጅ የሚያሳዩ ሌሎች ቪዲዮዎች እንዲሁ በዚሁ የቲክቶክ አካውንት ላይ ተጋርተዋል

ኒኮደም በ ጎፈንድሚ ላይ ባወጣው የገቢ ማሰባሰቢያ ልጥፍ ላይ “ሴቭ አፍሪካን ቻይልድ 254 ሚኒስትሪ (Save African Child 254 Ministry)” የተባለ በኡጋንዳ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚረዳ ድርጅት እና “ኪንደር ሂልፈዘንትረም (Kinderhilfezentrum)” የተባለ ሌላ ግበረ-ሰናይ ድርጅት መስራች እንደሆነ ገልጿል።

በተጨማሪም “ኒኮላስ ሰቡፉ” ትክክለኛ ስሙ እንደሆነ እና “ካቶ ኒቆዲም” ቅፅል ስሙ መሆኑን ገልጿል

በትግራይ ክልል ድርቅና የረሃብ ችግር መከሰቱን ዘገባዎች ቢያመለክቱም ይህ ቪዲዮ ግን በትግራይ የተራበ ሕፃንን የሚያሳይ አይደለም። 

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የፌስቡክ ፖስት ትክክል ያልሆነ ቪዲዮ በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

በአዲስ ዘይቤ ውስጥ መረጃን በማረጋገጥ ላይ እየሠራ የሚገኝ። በቀደመ ጊዜ በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ በሪፖርተርነት ይሠራ የነበር።

Similar Posts