Is Ethiopia’s economy bigger than its neighbors combined?

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአምስት አመት በፊት ከምስራቅ አፍሪካ በምጣኔ ሀብት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ  አሁን ከጎረቤቶቿ ሀገራት ኢኮኖሚ ድምር የላቀ ኢኮኖሚ አላት በማለት ተናግረዋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እአአ በመጋቢት 2018 ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ብልጽግናን እና ዲሞክራሲን ለማጎልበት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ቃል ገብተዋል። በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስትም ማሻሻያው ሀገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል ሲል ይገልጻል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በትክክለኛው የኢኮኖሚ አቅጣጫ ላይ እንደምትገኝ እና ኢኮኖሚዋም እያደገ መምጣቱን በተደጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን  በቅርቡ፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ባለፉት አምስት ዓመታት በእጥፍ ጨምሯል ያሉትም ከነዚህ መካከል የሚጠቀስ ነው።

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በቅርቡ ለክረምት ተማሪዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እያደገች መሆኗን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ጋር በማነፃፀር ለተማሪዎቹ አብራርተዋል፡፡

ጠ/ሚንስትሩ  እንደተናገሩት፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ልኬት ከአምስት ዓመታት በፊት ከኬንያ ቀጥሎ በምስራቅ አፍሪካ ሁለተኛው  ነበር። እ.ኤ.አ. በ2018 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 84.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር፤ እንዲሁም የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ እንደገለጸው፣ የሀገሪቷ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን  91.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ከአምስት ዓመታት በኋላ እአአ በ2022 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 126.8 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ፤ የኬንያ ደግሞ 119.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በዚህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከአምስት አመት በኋላ የኬንያን በልጦ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሆኗል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ድምር እንኳን ይበልጣል ወይም የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ኢኮኖሚ ተደምሮ ከኢትዮጵያ አንሷል በማለት ያስተላለፉት መረጃ ሀሰት ነው።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ስድስት ሀገራት ማለትም፡ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ እና እውቅና ባላገኘችው ሃገር ሶማሊላንድ ትዋሰናለች።

እንደ አለም ባንክ ዘገባ የሱዳን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እ.ኤ.አ. በ2022 51.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በዚህም መሰረት የኬንያ እና የሱዳንን የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ተደምረው ከኢትዮጵያ (171.2 ቢሊዮን እና 126.8 ቢሊየን ሲነጻጸር) ይበልጣሉ።

የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሌላንድ እና የሶማሊያ የቅርብ ጊዜ ኢኮኖሚ መረጃ በየራሳቸው ማዕከላዊ ባንኮች ወይም የስታስቲክስ ኤጀንሲዎች መረጃ ቋት ላይ አይገኝም። ስለዚህ እንደ አይኤምኤፍ ካሉ ሌሎች አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያወጡትን መረጃ አስደግፈን አቅርበናል።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እ.ኤ.አ. በ2022 የበርካታ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ)  አሃዞችን የዘገበ ሲሆን እነዚህም  አሃዞች እንደሚከተለው ናቸው፡- የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 120.37 ቢሊዮን ዶላር፣ የኬንያ 113.7 ቢሊዮን ዶላር፣ የሱዳን 33.75 ቢሊዮን ዶላር፣ የሶማሊያ 10.42 ቢሊዮን ዶላር፣ የደቡብ ሱዳን 8.54 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም የጅቡቲ 3.66 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።  ይህ የአይኤምኤፍ መረጃ ግን ስለ ኤርትራ እና ሶማሌላንድ ለተጠቀሰው አመት መረጃን እንደማያጠቃልል ልብ ሊባል ይገባል።

ስለዚህ በ2022 የአምስቱ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት (ኤርትራ እና ሶማሌላንድን ሳይጨምር) አጠቃላይ  ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 170 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን  120.37 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው።

ይህም ሲጠቃለል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያላት ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጎረቤቶቿ ድምር የበለጠ ነው ማለታቸው እ.ኤ.አ. በ2022 የኢኮኖሚ መረጃን መሰረት በማድረግ ሀሰት ሆኖ ተገኝቷል።

በአዲስ ዘይቤ ውስጥ መረጃን በማረጋገጥ ላይ እየሠራ የሚገኝ። በቀደመ ጊዜ በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ በሪፖርተርነት ይሠራ የነበር።

Similar Posts