ከ1100 በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት ግንቦት 16 ፤ 2014 ዓ.ም ላይ “ሰበር መረጃ’ በትግራይ ክልል አመፅ ተቀስቅሷል ፤ የትግራይ ህዝብ አብይ አህመድ ይምራን እያለ ነው” የሚል ፅሁፍ አያይዞ ሶስት ምስሎችን አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የትዊተር ፖስቱ ከ80 በላይ ግብረ መልሶችን ሲያገኝ ከ30 ጊዜ በላይ ሪትዊት ተደርጓል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሎቹን መርምሮ የተቀናበረ ብሏቸዋል።

በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተከሰተው ግጭት እስካሁን ድረስ መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

ህወሓት ጦርነቱ እንዲያበቃ የተኛውንም አይነት የዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንደሚከተል እና ያ የማይሆን ከሆነ ግን መልሶ ወደ ጦርነቱ ሊገባ እንደሚችል ተናግሯል። ህወሓት የሰብዓዊ እና የመድሃኒት እርዳታ ወደትግራይ ክልል እንዳይገባ የፌደራል እና የክልል መንግስታት እያገዱ ነው በማለት በተደጋጋሚ  ክስ ሲያቀርብ ቆይቷል።   

ግንቦት 12 ፤ 2014 ዓ.ም ህወሓት እንዳስታወቀው የትግራይ መንግስት የፖለቲካ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኛነት ለማሳየት ለአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ለሆኑት የቀድሞ የናይጄርያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በገባው ቃል መሰረት 4208 የሚሆኑ የጦር እስረኞችን የፈታ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 401 የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ በመግለጫው አስታውቋል።

ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታዦማር ሹም የሆኑት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የትግራይ ህዝብ ለህወሓት ሲል ከዚህ በላይ መሞት የለበትም። በሺዎች የሚቆጠር ህይወት ጠፍቷል። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን እምቢ ማለት አለበት።” ብለው ነበር። 

የትዊተር ፖስቱም ይህን አውድ ታሳቢ በማድረግ የተጋራ ነበር። 

ሀቅቼክ ምስሎቹን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ሁለቱ ምስሎችDW አማርኛ የፌስቡክ ገፅ ላይ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተጋራ ፖስት ላይ “ለደህንነታችን እንሰጋለን ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ዛሬ በመቐለ ሰልፍ አካሄዱ። ሰልፈኞቹ የደህንነት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች መማር እንደሚሰጉ በመግለፅ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።” በሚል ፅሁፍ ስር አግኝቶታል።

በሰልፉ ላይ “የተጋሩ ተማሪዎች ህይወት ያሳስበኛል፣ ዋስትና ወደሌለው ቦታ ልጆቻችን አንልክም፣ ተማሪዎች ትርጉም የሌለው መስዋእት መክፈል የለባቸውም፣ የክልል እና ፌደራል መንግስታት መፍትሄ ይስጡን” የሚሉ መፈክሮች ተስተጋብተዋል።

ምስል አንድ 

ምስል ሁለት

ሶስተኛው ምስል ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም borkena.com በተባለ ድረ-ገፅ ላይ “Fresh ethnic-based violence in Asossa left at least eight people dead.” በሚል ፅሁፍ ስር አግኝቶታል። 

የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ምንጮችን በመጥቀስ የተፃፈው ይህ ዜና “የበርታ ተወላጅ ነን የሚሉ ወጣቶች በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሌሎች የአማራ እና ኦሮሞ ነዋሪዎች የሚያንቀሳቅሷቸው ቢዝነስ ተቋማት ላይ በተቀናጀ መልኩ ጥቃት ሰንዝረዋል። ይህን ተከትሎም የአማራ ተወላጆች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እንዳደረጉ ቢሰማም ከበርታ ማህበረሰብ የተጎዳ ይኑር አይኑር የተጣራ መረጃ አልተገኘም” በማለት ያስነብባል።  

ምስል ሶስት       

የመጀመርያ ሁለቱ ምስሎች በትግራይ የነበረን ህዝባዊ ሰልፍ የሚያሳዩ ቢሆንም መረጃውን ለመደገፍ ምስሉ ተቀናብሯል። ከዚያ በተጨማሪ ሶስተኛው ምስል ደግሞ ከትግራይ ክልል እንዳልሆነ ተረጋግጧል።
ስለዚህ ሀቅቼክ ምስሎቹን መርምሮ እና አጣርቶ የተቀናበሩ እንደሆኑ አረጋግጧል።

Similar Posts