የፌደራሉ መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ትጥቅ በማስፈታት እንደፍላጎታቸው ወደመከላከያ ፤ ፌደራል እና የክልል ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል ግጭት መከሰቱ ይታወሳል። ይህ በክልሉ የተከሰተው ግጭት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥ እየተባባሰ እና ጉዳት እያስከተለ መምጣቱን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።

ይህን ተከትሎ አማራ ክልል በፌደራል መንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የተለያዩ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን እያስተናገደ ይገኛል። በክልሉ ባለው ግጭትም የሰው ልጅ ህይወት ሲጠፋ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም እንደተካሄዱ የሚያሳዩ የተለያዩ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።         


በሰኔ ወር የፋኖ ታጣቂዎች ጎንደር እና ደብረታቦርን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ ዋና ዋና ከተማዎችን ተቆጣጥረው እንደነበር ይታወሳል። ይህን ሁኔታ ተከትሎ በክልሉ የተከሰተው ችግር  ክልሉ ባለኝ አቅም ልገታው አልችልም በማለት የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ እና መፍትሄ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል። ከጥሪው በፊት በክልሉ የተወሰኑ አከባቢዎች ይንቀሳቀስ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት የክልሉን ጥሪ ተከትሎ በክልሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ወታደሮቹን አሰማርቷል። በክልሉ የተከሰተውን ሁኔታ በዘላቂነት ለመቆጣጠር ያግዝ ዘንድ የኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል ላይ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማፅደቁ ይታወሳል።

የፌደራል መንግስት ሀይሎች መጀመሪያ አካባቢ ስኬታማ የነበሩ ሲሆን በፋኖ ታጥቂዎች ስር የነበሩ የተለያዩ ከተማዎችንም መልሶ መቆጣጠር ችለው ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም በክልሉ ላለው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ያልተቻለ ሲሆን ይህም ተጨማሪ ግጭቶች እና አመፆች በክልሉ እንደሚቀጥሉ ተጨባጭ ስጋት አለ፡፡

ከአማራ ብሄር ተወላጆች እስር ጋር ተያይዞ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል ከታወጀበት ከሐምሌ 28 ፤ 2015 ዓ.ም ጊዜ ጀምሮ የፌደራሉ መንግስት የአማራ ብሄር ተወላጆችን ጨምሮ ፖለቲከኞችን ፤ ጋዜጠኞችን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን አስሯል።

ከእነዚህም መካከል የቀድሞው የአማራ ክልል ምክር ቤት እና የገዥው ፓርቲ ብልፅግና አባል የነበሩት አቶ ዮሃንስ ቧያለው እንዲሁም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ ለእስር ከተዳረጉት ጥቂት የአማራ ብሄር ተወላጆች ውስጥ ይጠቀሳሉ። 

እንደ መንግስት ሚድያዎች የዜና ዘገባ ከሆነ የፌደራሉ መንግስት 764 የሚሆኑ በክልሉ ያለውን የትጥቅ እንቅስቃሴ ይደግፋሉ ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ አድርጓል።   


ይሁን እንጂ የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ሪፖርቶች መንግስት የአማራ ብሄር ተወላጆችን ኢላማ አድርጎ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ የእስራ ማቆያ ቦታዎች እንዳሰራቸው እየተናገሩ ይገኛሉ።

ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘው እየወጡ ያሉ የማህበራዊ ሚድያ ላይ ፖስቶች በመንግስት እስር ላይ የሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆችን የሚያሳዩ ናቸው በመባል እየተሰራጩ ይገኛሉ።

ለምሳሌ ያክል በመስከረም 2 ፤ 2016 ዓ.ም አንድ የፌስቡክ ገፅ (ከስር ያለውን ስክሪን ሾት ይመልከቱ) አራት ምስሎችን በማያያዝ ምስሎቹ በመንግስት አማካኝነት ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ቱሉ ዲምቱ ከተማ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆችን እንደሚያሳይ ከሚገልፅ ፅሁፍ ጋር አጋርቶ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ይህ የፌስቡክ ፖስት በካምፕ ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች እየተጠቁ እንደሆነም ገልጿል።  


[የመግለጫ ፅሁፍ ፡ እነዚህ በቱሉ ዲምቱ ካምፕ በእስር ላይ የሚገኙ እና በተላልፊ በሽታዎች የተጠቁ የአማራ ክልል ተወላጆች ናቸው]

ይህ ፖስት ብዙዎች ጋር መድረስ የቻለ ሲሆን ብዙ ግብረመልሶችንም ማግኘት ችሎ ነበር። ነገር ግን ሀቅቼክ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቂ መረጃዎችን ማግኘት ስላልቻለ የምስሎቹን እርግጠኛነት ማጣራት አልቻለም።

የቆዩ ፖስቶችን ኤዲት ማድረግ

በሌላ በኩል አንዳንድ የመንግስት ደጋፊ የሚመስሉ የማህበራዊ ሚድያ አካውንቶች የዚህን ፌስቡክ ፖስት እና ስክሪን ሾት በማጋራት ምስሎቹ ከአመት በፊት እንደተጋራ ገልፀው ከአማራ ብሄር ተወላጆች እስር ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ በመናገር ሲያጋሩ ቆይተዋል።

እነዚህ ፖስቶች የመጡት ምስሎቹ ሀሰተኛ እና መንግስት አሁን ያሰራቸውን የአማራ ክልል ተወላጆች እንደማያሳዩ ለማሳየት ነው።


(የመግለጫ ጽሁፍ ፡ እነዚህ ፖስቶች የተሳሳተ መረጃን ለማስተላለፍ ሀሰተኛ እና የቆዩ ምስሎችን ተጠቅመዋል)

ከስር ካለው ፌስቡክ ፖስት ላይ የተወሰደው ምስል (ስክሪን ሾት) የቆየ የፌስቡክ ፖስት ላይ የተጨመረ  ሲሆን ይህን አወዛጋቢ ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው እዚህ ላይ ነው ለማስባል ይህ የፌስቡክ ገፅ ተጠቅሞበታል።         

 
(የመግለጫ ፅሁፍ፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ጎዳና ተዳዳሪዎች የህክምና አገልግሎት ሰጥቷል)

ሀቅቼክ ምስሎቹ እና የፌስቡክ ላይ ልጥፎቹ ከአንድ አመት በፊት መጋራታቸውን ለማጣራት ጥረት አድርጓል። ሀቅቼክም ሰኔ 22 ፤ 2014 ዓ.ም የተጋራ አንድ የፌስቡክ ፖስት እነዚህን ምስሎች ከአማርኛ የመግለጫ ፅሁፍ ጋር አጋርቶት እንደነበረ ማስተዋል ችሏል።

ኤዲት ተደርጎ (ተቀይሮ) የነበረው የፌስቡክ ፖስት


ሀቅቼክ የቆየ ምስሎች ናቸው ተብሎ የተጋራበት የፌስቡክ ፖስት በቅርቡ የተቀየረ እንደሆነ እንዲሁም ምስሉም ከፅሁፉ ጋር አብሮ የተቀየረ መሆኑን አረጋግጧል።

ይህ የፌስቡክ ፖስት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 22 ፤ 2014 ዓ.ም በኦሮሚኛ ፅሁፍ ተጋርቶ የነበረ ሲሆን በመግለጫውም አምስት ግድያ የተፈፀመባቸውን እና ታላቅ ስብዕና አላቸው ያላቸውን ሰዎች የጠቀሰበት ፖስት ሲሆን እነሱም ጆን ኤፍ ኬኔዲ ፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፤ አብርሃም ሊንከን ፤ ማልኮም እና ሃጫሉ ሁንዴሳ ነበሩ።   

     
ይህ ፖስትም ሰኔ 22 ፤ 2012 ዓ.ም የተገደለውን ታዋቂውን የኦሮሚኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ከሌሎቹ አራት ሰዎች ጋር ያወዳደረብት የኦሮሚኛ ፅሁፍ ነበር። በመጀመሪያ የተጋራው ፖስት አንድ ምስል ብቻ እንደነበረው ማየት ይቻላል ነገር ግን ምስሉ ኤዲት ተደርጎ ስለወጣ እና በሌሎቹ ምስሎች ስለተተካ ሀቅቼክ የመጀመሪያውን ምስል ማግኘት አልቻለም።  

(ይህ ስክሪን ሾት ፡ ኦሪጅናሉን እና በኦሮሚኛ ፅሁፍ ተጋርቶ የነበረውን የሚያሳየው የፌስቡክ ፖስት ነው) 

ይሁን እንጂ ይህ የፌስቡክ ፖስት መስከረም 2 ፤ 2016 ዓ.ም እንደተቀየረ ያሳያል የኦሮሚኛ ፅሁፉም በሌላ የአማርኛ ፅሁፍ እንዲሁም አንድ የነበረው ምስል በሌሎች አምስት ምስሎች ተቀይሯል።

የተቀየረው እና አዲሱ ፖስት የሚያሳየው ፅሁፍ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከመቶ ለሚበልጡ የጎዳና ላይ ነዋሪዎች ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚል መግለጫ ነው።  

(መስከረም 2 ፤ 2016 ዓ.ም ላይ የመግለጫ ፅሁፉ እንደተቀየረ እና አምስት ምስሎች እንደተጨመረበት ያሳያል)  

በዚህ ምክንያት ሀቅቼክ ይህንን የፌስቡክ ፖስት ሐሰት ብሎታል። ይህ ፖስት ሆን ተብሎ እና ሰዎችን ለማሳስት እንደተቀየረ በግልፅ ማየት ይቻላል። 

ሀቅቼክ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ከእነዚህ አይነት አሳሳች የሆኑ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶች መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባል።

በተለይም ፌስቡክ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ተጠቃሚዎች የሚያጋርቱን መልዕክት ላይ የአርታዖት ስራ እንዲሰሩ፣ ተመልሰው እንዲያስተካክሉ የሚፈቅድ አማራጭ ይፋ ማድረጉ ተከትሎ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ተጠቃሚዎችም መረጃዎች የተጋሩበትን ቀን ከማየት ባለፈ የፖስቱን ኤዲት ሂስትሪ(የተጋራውን መልዕክት የአርትዖት ታሪክ) ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።     

Similar Posts