ሰኔ 2  ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ የተላለፈ ቪድዮ ባሰራጨው መልዕክት የማነ ገብረመስቀል የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሆኑ ጠቅሶ ነበር። ቪድዮውም በመቀጠል ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እየጠነከረ እንደመጣ ገልጾ በተቃራኒው ደግሞ ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ ይበልጥ እየሻከረ እንደመጣ ይናገራል።

ቪድዮው በትንታኔው በኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በአስመራ የአሜሪካ ኤምባሲ መካከል በፖለቲካ ፤ በሃይማኖት እና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አለመስማማት እና ጭቅጭቆች እንዳሉ በመናገር ይህም ለሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት መሳሳት ይበልጥ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይናገራል።

አሜሪካ ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጡኑ እየሻከረ የመጣው በሰሜን ኢትዮጵያ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ ሲሆን ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ሙሌት ማሳካቷን ተከትሎ አሜሪካ የምታደርገውን የገንዘብ እርዳታዎች ማቆምን ጨምሮ ማዕቀብ የመጣል ማስፈራሪያዎችን ስታሰማ ቆይታለች። ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ለመሻከሩ እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል። 

የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር በነበረው ግጭት የአሜሪካ መግስት በክልሉ ለተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የኢትዮጵያን እና የኤርትራ መንግስት ተጠያቂ አድርጓል። 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እንዲያስወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የቆዩ ሲሆን በመጨረሻም የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ እና በኤርትራ የጦር አመራሮች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። 

የኤርትራ መንግስት በበኩሉ አሜሪካ ህወሓትን በማገዝ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀጠናው አለመረጋጋት አስተዋጾ እያደረገች እንደሆነ ክስ አቅርቧል።  

የማነ ገብረመስቀል ከፍተኛ የኤርትራ መንግስት ባለስልጣን ሲሆኑ በማህበራዊ ሚድያ በተለይም በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ በተደጋጋሚ የአሜሪካ መንግስት ህወሓትን እየረዳ እንደሆነና ይህ ደግሞ ይበልጥ ለቀጠናው አለመረጋጋት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እንደሚያግዝ በመናገር ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።  

በአስመራ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አማካኝነት የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ እንደሆነ በመግለፅ፣ የማነ ገብረመስቀል ሀሰተኛ መረጃን በመፈብረክ በማህበራዊ ሚድያ እያሰራጩ እንደሆነ ገልጿል።      

የማነ ገብረመስቀል የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሲሆኑ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ናቸው። ኦስማን ሳሌህ ከኤርትራ ውጭ በሚኖራቸው ጉዞ የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ አብረዋቸው ይታያሉ።     

የማነ ገብረመስቀል የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የሆኑት አሊ አብዱ ሀገራቸውን ክደው መጥፋታቸው ከታወቀ በኋላ እኤአ በ2015 ነበር።
በዚህም መሰረት የማነ ገብረመስቀል የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳልሆኑ በማረጋገጥ በዩቲዩብ ቻናሉ የተላለፈውን መረጃ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል። 

Similar Posts