በአንድ የፌስቡክ ፖስት ሀምሌ 7 ቀን የተላለፈ መረጃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ ከስራው በገዛ ፈቃዱ መልቀቁን አስታውቆ ነበር። ይህ ፖስት ዮናስ ዘውዴ ራሱ እንደተናገረው በመጥቀስ “አሁን ያለው አገዛዝ በሙስና የተዘፈቀ እና ለሀገሪቱ መፃኢ ዕድል የማያስብ ስለሆነ አብሬ ልቀጥል ባላመቻሌ በራሴ ፍቃድ ከሃላፊነቴ ለቅቄያለው” ማለቱን ፅፏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ ከኃላፊነቱ አለመልቀቁንና በመስተዳድሩ ወደ ሌላ የስራ መደብ መዘዋወሩን አረጋግጧል።    

አቶ ዮናስ ዘውዴ ከኃላፊነቱ በገዛ ፈቃዱ ለቋል የሚለው የዚህ የፌስቡክ ፖስት መረጃ የተሰራጨው የተለያዩ የመንግስት ባላስልጣናት ከኃላፊነታቸው በተነሱበትና በቁጥጥር ስር በዋሉበት ሰሞን ነው።  

ባለፈው ሳምንት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በቅርቡ ለዕድለኞች የወጣውን የኮንዶሚኒየም ዕጣ በአስተዳደሩ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እና አንዳንድ ባለስልጣናት በዕጣው የማጭበርበር ሂደት ውስጥ ተሳትፈዋል በማለት የእጣ አወጣጥ ሂደቱ እንደሚደገም አስታውቋል። በማጭበርበር ሂደቱም ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን ግለሰቦች ላይ የምርመራ መዝገብ ተከፍቶባቸዋል።

የቀድሞው የአዲስ አበባ መስተዳድር የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ከስራ የመልቀቅ መረጃዎች መሰማት የጀመሩትም የኮንዶሚኒየም የዕጣ አወጣጥ ውዝግብ ባስነሳበት ወቅት ላይ ነበር።           

አቶ ዮናስ ዘውዴ የብልፅግና ፓርቲ አባል ሲሆን በስድስተኛው ሃገር አቀፍ አጠቃላይ ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል ሆኖ ተመርጧል። ይህንንም ተከትሎ በከተማዋ ከንቲባ አማካኝነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተደርጎ ተሹሟል።  

የአቶ ዮናስ ከኃላፊነት የመልቀቅ መረጃን ተከትሎ አል-አይን አማርኛ ባቀረበው ሪፖርት የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወደ ሌላ የስራ መደብ መዘዋወሩን ገልጿል። በሪፖርቱም በዶ/ር ዮናስ ምትክ በቦታው የተሾሙት አቶ አብዲ ፀጋዬ የአቶ ዮናስን ወደ ሌላ የስራ መደብ መዘዋወሩን አረጋግጠዋል። 

ሃቅ ቼክ በጉዳዩ ዙሪያ መልስ ለማግኘት አቶ ዮናስ ዘውዴን በስልክ ያገኘው ሲሆን በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ ገልጾ ስለ ጉዳዩ ያለውን ትክክለኛ መረጃ ራሱ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል።    

በዚህም መሰረት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናስ ዘውዴ በገዛ ፈቃዱ ከኃላፊነቱ አለመልቀቁን እንዲሁም ወደሌላ የስራ መደብ እንደተዘዋወረ ሃቅ ቼክ አረጋግጧል።  

Similar Posts