በታህሳስ 2፣ 2013 ዓ.ም ሰላም ንኩሉ የተሰኘ 3418 ጓደኞች እና 1337 ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ከስር በሚታየው ምስል ላይ የስለት መሳርያ ይዘው የሚገኙት ግለሰቦች በማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ናቸው በማለት የተለቀቀ ሲሆን ግለሰቡ ምስሉ በሚገባ ተይዞ ግለሰቦቹ ለህግ እንዲቀርቡ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ሀቅ-ቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ በማይካድራው ጭፍጨፋ ወቅት የነበረውን እውነታ የማያሳይ ሆኖ  ስላገኘው ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡

ምስል 1

 

 

በትግራይ ክልል በፌደራል መግስትና በሕወሓት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በጥቅምት 30  በህዳር 1 2013 ዓ.ም ከ600 በሚበልጡ ንፁሀን ዜጎች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጭፍጨፋው የተፈፀመው በከተማዋ የመንግስት አካላት እና የፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ በተደረገለት ራሱን ሳምሪ በማለት በሚጠራ አክራሪ ቡድን እንደሆነ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች ሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች መግለፃቸው የሚታወስ ነው። በተጨማሪም እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና አመነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፃ ወንጀለኞቹ በከተማዋ በሚኖሩ የአማራ እና ወልቃይት ኢትጵያውያን ላይ አሰቃቂውን የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀሙት ቆንጨራ፣ መጥረቢያ፣ ገመዶችን እና ሌሎች ስለታም ነገሮችን በመጠቀም መሆኑ ታውቋል፡፡ የማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ በገለልተኛ አካላት ምንም አይነት ምርመራ ማካሄድ የማይፈቀድ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖሰት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርመራዎች እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡ 

ምስል 1፡ በተጠቀሰው የፌስቡክ ገፅ የተሰራጨው ፎቶ። 


 

ሪቨርስ ኢሜጅ በተባለ የምስል ማጣርያ መንገድን በመጠቀም ሀቅቼክ ለማወቅ እንደቻለችው ከሆነ በፌስቡክ ገፁ ላይ የተለቀቀው ምስል ከ600 በላይ ሰዎች በተገደሉበት የማይካድራው ጭፍጨፋ ወቅት የተወሰደ አለመሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው ሀምሌ 3 2013 ሲሆን ኢብሳ የሚል ስም ባለው የትዊተር ገፅ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ እንደተለቀቀ መረዳት ይቻላል። በወቅቱ ኢብሳ ከላይ ከሚታየውን ምስል ከሌሎች አራት ምስሎች ጋር ያጋራ የነበረ ሲሆን ምስሎቹን “#ፍትህ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኦሮሞ ህዝቦች #አብይ መሄድ አለበት” ከሚል ፅሁፍ ጋር እንዳጋራ ከላይ የተቀመጠውን መስፈንጠርያ በመንካት ማየት ይቻላል። በመሆኑም ምንም እንኳን በማይካድራ በአሰቃቂ መልኩ በ600 ሰዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ላይ ጥቃቱን የፈፀሙት አካላት ስለታማ መሳርያዎችን እንደተጠቀሙ የተለያዩ ተዓማኒነት ያላቸው የመንግስት አካላትና በሰብአዊ መብት ዙርያ የሚሰሩ ድርጅቶች ቢገልፁም ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ በምስሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች ከሁኔታው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውም ስለሆኑ በማረጋገጡ የተነሳ መረጃውን የሀሰት ነው ሲል ፈርጆታል፡፡

 

አጣሪ፡ ሀጎስ ገ/አምላክ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

 

 

 

 

Similar Posts