የተለያዩ የቴሌግራም ገፆች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ አባይ ባንክን እና የአማራ ባንክን ስምና ሎጎ በመጠቀም የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያጋሩ ተስተውለዋል። በገፆቹ ውስጥ ያሉት መልዕክቶችም ባንኮቹ ለመጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የቴሌግራም ገፆች እንዲነቃቁ ለባለ ዕድሎች ሽልማት ማዘጋጀታቸውን ይገልፃሉ፡፡

የቴሌግራም ገፆቹም ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ እንደየቅደም ተከተላቸው 52,350 ፣ 7,733 እና 67,480 ተከታዮች አሏቸው፡፡

ሃቅቼክ ልጥፎቹን በመመርመር አታላይ መልዕክቶች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

         

    

 

 

የመጀመሪያው የቴሌግራም ገፅ “እንኳን ደስ አላቸችሁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀብት 1.1 ትሪሊየን ትርፍ ምክንያት በማድረግ  የባንካችን ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ እስከ መስከረም 5 ብቻ የሚቆይ የቴሌግራም ገፅ ማነቃቂያ የሚሆን ሽልማቶች ተዘጋጅቷል።” ካለ በኃላ ለዕድለኞች የሚሸልመውን ዝርዝር ያስቀምጣል፡፡

ሽልማቶቹም “1ኛ” ብሎ ካስቀመጠው  ለ200 እድለኞች ከ300,000 ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችና እያንዳንዳቸው ከ50,000 ብር በላይ ግምት ያላቸው ሙሉ የቤት እቃዎች እስከ 5ኛው ለ 100 ዕድለኞች 5ሺ ብር እና የሞባይል ቀፎች ድረስ ይዘረዝራል፡፡

በመጨረሻም ዕድለኞቹ የሚሸለሙበትን መስፈርት “መጀመርያ የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። በመቀጠል ይህንን መልዕክት ከ50 በላይ ለሆኑ ሰዎች በፍጥነት ሼር ያድርጉ፡፡” የሚል ማሳሰቢያ አያይዟል፡፡ 

ሁለተኛው ገፅም “ዕድልዎን ይሞክሩ። በአዲስ አመት ልዩ የ500,000 ብር ስጦታ ከአባይ ባንክ” በሚል አጓጊ ርዕስ ከጀመረ በኃላ ባንኩ ለሽልማት አዘጋጅቷል ያላቸውን ሽልማቶች እስከ ስድስተኛ ደረጃ ድረስ ይገልፃል፡፡ ሽልማቶች የተባሉትም 1ኛ ላይ ካስቀመጠው “ለ50 እድለኞች 500,000 ብርና እያንዳንዳቸው ከ40,000 ብር በላይ ግምት ያላቸው ማቀዝቀዣ ፊሪጆች” አንስቶ ስድስተኛ ላይ እስካስቀመጠው ለ50 እድለኞች 5,000 ብር ድረስ ሰዎችን ሊያጓጉ የሚችሉ የተለያዩ ደረጃዎችን በረድፍ ሰድሯቸዋል፡፡

ለመሸለምም የቴሌግራም ቻናሉን መቀላቀል ፣ መልዕክቱን ለ50 ሰው ማጋራትና በባንኩ ስም ወደተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ መቀላቀልን እንደመስፈርት አያይዟል፡፡

ሶስተኛው ገፅም የቴሌግራም ቻናሉን በመቀላቀልና ለ50 ሰው በማጋራት ለ200 ዕድለኞች ከሚሰጠው ከ300,000 ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች እስከ ለ 100 እድለኞች 5ሺ ብር እና የሞባይል ቀፎ ድረስ መሸለም እንደሚችሉ ልጥፍ አጋርቷል፡፡ ገፁ የሽልማቱን ምክንያትም “አማራ ባንክ በ2014 መባቻ ሥራ ለመጀመር ሙሉ ዘግጅቱን አጠናቋል! … ሥራ ሲጀምር በመላ ሐገሪቱ ለሚከፈቱ ከ200 በላይ ቅርንጫፎች ደንበኞችን በቀላሉ ለማሰባሠብ የቴሌግራም ቻናል ከፍቶ እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡” በማለት ገልፆአል፡፡

ሃቅቼክ የመረጃውን ሃቀኝነት ለማጣራት የአማራ ባንክ የቦርድ አባል የሆኑትን ዶ/ር ለጤናህ እጅጉን አነጋግሯል፡፡ የቦርድ አባሉም “በአማራ ባንክ ስም የሚወጡት የቴሌግራም መልዕክቶች የፈጠራ ወሬዎች  ናቸው” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ባንካችን እስካሁን ምንም አይነት የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ስለሌለው ደንበኞቻችን ራሳቸውን ከተመሳሳይ የሃሰተኛ መረጃዎች ይጠብቁ፡፡” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ከስድስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በይፋዊው የፌስቡክ ገጹ ላይ ደንበኞቹ ራሳቸውን በተቋሙ ስም ከተከፈቱ ሃሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እንዲጠብቁ ያሳሰበ ሲሆን ድርጅቱ የሚጠቀምባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ 

በተያያዘም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና የአባይ ባንክን ይፋዊ ድረ ገፆች ላይ የተቀመጡት የቴሌግራም አድራሻዎች ለቴሌግራም ተጠቃሚዎች ለበዓል ስለሚሰጡ ስጦታዎችም ሆነ ሽልማቶች የሚዘግቡ መረጃዎች እንደሌሉ ተመልክተናል፡፡

በመሆኑም ሃቅቼክ በቴሌግራም ላይ የተዘዋወሩት መልዕክቶች በባንኮቹ ዕውቅና የሌላቸው አታላይ መልዕክቶች እንደሆኑ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ተጠቃሚዎች እንዲህ አይነት መረጃዎችን በሚመለከቱበት ጊዜ፡

  • የድረ ገፁን ስም እና አድራሻ በሚገባ ማጤን
  • መረጃዎችን እንደመጡ ከማመን ይልቅ በጥንቃቄ መመልከት፣ የላኪውን ትክክለኛ አድራሻ ማረጋገጥ
  • በፍጥነት እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ፣ ጊዜ ወስዶ መመርመር
  • የተጠቀሰውን አካል (ድርጅት) በቀጥታ መጠየቅ ይመከራል።

Similar Posts