Safaricom Ethiopia በተባለ እና ከ16,000 በላይ ተከታይ ባለው የቴሌግራም ቻናል አንድ መልዕክት በሰፊው ሲዘዋወር ሀቅቼክ የተመለከተ ሲሆን መልዕክቱ ሰዎች የቴሌግራም ቻናሉ አባል እንዲሆኑና ሌሎችንም የቻናሉ አባል እንዲሆኑ እንዲጋብዙ ይናገራል። በዚህም መሰረት፣ “አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ወደቻነሉ ጋብዞ ያመጣው ሰው 80,000 ብር የሚያወጣ አፕል ላፕቶፕ ተሸላሚ ሆነ” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

መልዕክቱ በተጨማሪም ሰዎች የቴሌግራም ቻናሉን እንዲቀላቀሉ በመጋበዝ ሌሎችም ተመሳሳይ ላፕቶፖችን እና iPhone 13 Pro Max የሞባይል ስልክ ቀፎዎችን መሸለም የሚችሉበት እድል እንዳለ ይናገራል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ መልዕክቱ ከ58,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደርሷል።

ሀቅቼክ መልዕክቱን በመመርመር የማጭበርበሪያ (የማታለያ) መንገድ (SCAM) እንደሆነ አጣርቷል።  

ተመሳሳይ ይዘት ያለውና ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ሌላ የፌስቡክ ገጽም ይህን መልዕክት አጋርቶት ነበር። ይሁን እንጂ ገጹ ቀደም ብሎ በጥር 2012 ዓ.ም በሌላ ስም ተከፍቶ የነበር ሲሆን በኋላ ላይ በጥር 5 ፤ 2014 ዓ.ም ስሙን ቀይሯል። ይህ የሚያሳየው የፌስቡክ ገጹ ለሌላ አላማ የተከፈተ እንደነበርና አሁን ስሙን ወደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በመለወጥ እያዘዋወረ ላለው መልዕክት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር አላማ እንዳለው ያስረዳል ነው። 

በግንቦት 13 ፤ 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የገንዘብ ሚኒስቴር የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት እንዲሳተፉ ጨረታ አውጥቷል

በተፈጠረው የቴሌኮም ፕራይቬታይዜሽን እድል አሸናፊ በመሆን ሳፋሪኮም ፣ የቮዳኮም ግሩፕ ፣ የቮዳፎን ግሩፕ እና የሱሚቶሞ ግሩፕ በጥምረት በመሆን በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት አንዲሰጡ ፍቃድ ማግኘት ችለዋል።

በዚህም መሰረት ግንቦት 14 ቀን ፤ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለኬንያው ሳፋሪኮም እና ለጃፓኑ ሱሚቶሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩበትን ፍቃድ ሰቷቸዋል። 

በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ብሩክ ታዬ እንደገለፁት፣ ቮዳኮም ፣ ቮዳፎን ፣ እና የእንግሊዝ ልማት እና ፋይናንስ ኤጀንሲ (CDC)ን የሚያጠቃልለው የጋራ ስምምነት ፍቃዱን ለማግኘት እስከ 850 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ከፍለዋል። 

የአገልግሎት ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎም ሳፋሪኮም ሰፊ የማስታወቂያ፣ የሰው ኃይል ቅጥርና የተለያዩ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል። የቴሌግራም መልዕክቱም ይህን የብዙዎች ትኩረት ያገኘውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰፊው በመዘዋወር ላይ ይገኛል። 

ሀቅቼክ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ስለጉዳዩ ያናገረ ሲሆን ድርጅቱ የቴሌግራም ቻናል ያለው ቢሆንም ምንም አይነት የሽልማት ፕሮግራም እንደሌለውና የሚዘዋወረው የቴሌግራም ቻናል የድርጅቱ እንዳልሆነ መረዳት ችሏል።     

የድርጅቱ ይፋዊ የማህበራዊ ሚድያ ገፆችም  ፌስቡክ ፣ ቴሌግራም ፣ ትዊተር ፣ ኢንስታግራም እና ሊንኪድን  እንደሆኑ ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጽሁፉን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የተቀነባበረ ሲሆን፣ ከጀርባ ያለው ምስል እና የሳፋሪኮም ምልክት ያለበት ሱቅ በኬንያ የሚገኘው የድርጅቱ መሸጫ እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሚል ስም በተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ ላይ እየተዘዋወረ ያለውን መልዕክት ሀቅቼክ የማጭበርበርያ (የማታለያ) መንገድ (SCAM) ብሎታል።                      

Similar Posts