ከ4 ሚሊየን በላይ ተከታይ ያለው የፊስቡክ ገጽ በሕዳር 30 ፤ 2014 ዓ.ም “ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ ኤርትራና ኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆኑ” የሚል ርዕስን በመጠቀም በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ450 በላይ ግብረመልስን ሲያገኝ ከ21 ጊዜ በላይ ደግሞ ተጋርቷል። ሀቅቼክ ገጹ የተጠቀመው ርዕስ ከጽሁፉ ይዘት ጋር ስለሚለያይ አሳሳች ርዕስ ብሎታል።    

 

በአለም ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን ከጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው አለም-አቀፍ ኮሚቴ Committee to protect journalist (CPJ)  በያዝነው አመት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በ2021 በመላው አለም የታሰሩ የጋዜጠኞች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደጨመረ በአንድ ሪፖርቱ ላይ አስነብቦ ነበር። 

በ2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ እንዲሁም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከሃገር የተሰደዱ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በተከፈተው አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

ይህንንም ተከትሎ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች ከእስር እንደተለቀቁ ይታወሳል። በፈረንጆቹ 2018 ኢትዮጵያ ከብዙ አመታት በኋላ ምንም አይነት ጋዜጠኛ ለእስር ያልተዳረገባት ሀገር ሆና መመዝገብ የቻለች ሲሆን ከዚያ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ ምንም አይነት በእስር ላይ ያለ ጋዜጠኛ ያልነበረው በፈረንጆቹ 2004 ነበር። 

reference: https://theatlas.com/charts/r1yRA3yxV  

Committee to protect journalist (CPJ) ባወጣው ሪፖርት መሰረት እስከ ሕዳር 22 ፤ 2014 ዓ.ም ድረስ በመላው ዓለም በአጠቃላይ 293 የሚሆኑ ጋዘጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። በወጣው ጥናት መሰረት ቻይና 50 ጋዜጠኞችን በማሰር የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ 25 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም 3ተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ከአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያው ሆናለች። ጎረቤታችን ኤርትራ 16 ጋዜጠኞችን በማሰር የ7ተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ 9 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም 11ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ነገር ግን የፌስቡክ ፖስቱ፣ “ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆኑ”የሚል ርዕስ ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ የተያያዘውን ማስፈንጠርያ በመከተል የሪፖርቱን ይዘት ስንመለከት፣  Committee to protect journalist (CPJ) ባወጣው ጥናት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ የቀዳሚነቱን ደረጃ እንደያዘች ያስነብባል። አያይዞም ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ የሚዲያ ነጻነት መፍትሄ የሚሻ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ገልጿል። በፈረንጆቹ 2018 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በሚዲያ ነጻነት ላይ ጉልህ ለውጦችን የታዩ ቢሆንም በ2021 ደግሞ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት መካከል ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ደረጃን የያዘ መሪ እንደሆነ ያስነብባል።    

በአፍሪካ ውስጥ ካሉት 54 ሃገራቶች መካከል ከሰሃራ በታች ያልሆኑ ሃገራት በሰሜኑ የአህጉሪቱ አካባቢ የሚገኙት እንደ አልጄሪያ ፣ ግብጽ ፣ ሊቢያ ፣ ሞሮኮ  እና ቱኒዚያ ሲሆኑ የቀሩት 49 የሚሆኑት የአፍሪካ ሃገራት ከሰሃራ በታች የሚገኙ ናቸው።

ስለዚህ በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተመለከተው ርዕስ በጽሁፉ ውስጥ ካለው ይዘት ጋር ሲለሚለያይ ሀቅቼክ አሳሳች ርዕስ ብሎታል።      

Similar Posts