ሬውይተርስ በጥር 18 ፤ 2014 ዓ.ም ባወጣው የዜና ሪፖርት፣ “የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ከውሳኔ ላይ ደርሷል” የሚል ርዕስ በድረ ገጹ ላይ አንድ ጽሁፍ አስነብቦ ነበር።” ይሁን እንጂ ሀቅቼክ መረጃውን ሚንስትሩ ከሰጠው መግለጫ ጋር በማመሳከር ዜናውን አሳሳች ብሎታል። 

በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በህወሓት እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን ድረስ ቀጥሏል። የፌደራሉ መንግስት በሰኔ 2013 ከመቀሌ እና ከክልሉ አካባቢዎች ለቆ ከወጣ በኋላ የህወሓት ሃይሎች እራሳቸውን በማጠናከር በአማራ ክልል በምትገኘው የደብረሲና ከተማ ድረስ በመምጣት መቆጣጠር ችለው ነበር። 

ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች መስፋፋቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በመላው ሃገሪቱ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ እና ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስራ ላይ አውሎ ነበር። 

ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በህወሓት ሃይሎች ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃን በመውሰድ ተቀጣጥረዋቸው ከነበሩት የአማራ እና አፋር ክልሎች አስወጥቷቸዋል። ከመጀመርያው ዘመቻ መጠናቀቅ በኋላ የፌደራል እና ሌሎች የክልል ልዩ ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡ እና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ በተጠንቀቅ እንዲቆዩ መንግስት ማዘዙን አስታውቋል።    

በቅርብ መንግስት ጃዋር መሀመድ፣ ስብሃት ነጋን እንዲሁም ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር ፈቷል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ጦርነቱን ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ለድርድር እየተዘጋጀ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። 

የኢፌዲሪ የሚንስትሮች ምክር ቤት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቋረጥ ጥር 18 ቀን  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አስተላልፏል። 

ይህ የሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ ሬውተርስ የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ አስተላልፏል የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ሁኔታውን አጣርቶ አሳሳች ብሎታል። 

የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የውሳኔ ኃሳብ ቢያቀርብም ኃሳቡ ላይ በመወያየት ውሳኔውን ሊያፀድቅ የሚችለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ምክር ቤቱ ሰነዱ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መርቶታል።  

ጥቅምት 23 ፤ 2014 ዓ.ም የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ከሆነ የአስቸኳይ አዋጁ ከመጠናቀቁ በፊት ማንሳት እንደሚችል አስቀምጧል። 

ይህም በመሆኑ ሀቅቼክ የዜና ሪፖርቱ ያቀረበውን መረጃ ሚንስትሩ ከሰጠው መግለጫ ጋር በማመሳከር ዜናውን አሳሳች ብሎታል። 

Similar Posts