በታሪክ አጋጣሚዎች ውዝግብ ለመፍጠር፣ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየር፣ እንዲሁም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ለመፍጠር በማሰብ ሀሰተኛ መረጃዎች ሆን ተብለው ይሰራጫሉ።

እስቲ በታሪክ አጋጣሚ የተሰራጩ ታዋቂ ሀሰተኛ መረጃዎች እና ዘመቻዎችን እንመልከት፦

  1. የጽዮን (አይሁድ) ሽማግሌዎች ሰነድ

ይህ ፅሁፍ ፀረ አይሁድ እና ሆን ተብሎ የተፈጠረ ሲሆን አይሁዶች አለምን ለመቆጣጠር እያሴሩ እንደሆነ የሚገልፅ ነው። ሰነዱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በፈረንጆቹ 1903 በሩሲያ ውስጥ ነበር። ከዚያ በኋላ ይህ ፅሁፍ አሁን ድረስ ሰዎች አይሁዶች ላይ ጥላቻ እና አመፅ እንዲቀሰቅሱ እያደረገ ይገኛል። በዚህ መፅሀፍ ውስጥ ያለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ቢረጋገጥም አሁንም ድረስ በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች ዘንድ ይታመናል።

    2. ኤድስ በአሜሪካ እንደተፈጠረ

በፈረንጆቹ 1980ዎች የሶቭየት ህብረት ሀሰተኛ መረጃን ኦፕሬሽን ኢንፌክሽን (Operation INFEKTION) በሚል ዘመቻ አሜሪካ የኤች አይቪ ቫይረስን ለጦር መሳሪያነት በማሰብ በቤተሙከራ ፈጥራዋለች በማለት አሰራጭታ ነበር።

ይህ መረጃ በተለያዩ የሚድያ አማራጮች ላይ በስፋት መነገሩን ተከትሎ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ትልቅ ጭንቀትና መገለል ፈጥሮ ነበር።

   3. የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሹ መሳርያ

በፈረንጆቹ 2003 በኢራቅ ላይ በተደረገው ወረራ የአሜሪካ መንግስት እና አጋሮቿ ኢራቅ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አላት ብለው ነበር። ይህ መረጃ ኢራቅን ለመውረር እና የሳዳም ሁሴን መንግስት ለመገርሰስ እንደ ምክንያት ቀርቦ ነበር። በኋላ ምንም አይት የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አለመገኘታቸውን ተከትሎ መረጃው በአለም አቀፍ ደረጃ ውግዘትን እና በመንግስት ላይ ያለን እምነት መሸርሸር እስከትሎአል።

  4. የራሽያ ጣልቃ ገብነት በ2016 የአሜሪካ ምርጫ

የአሜሪካ የደህንነት ተቋማቶች በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሩሲያ መንግስት የተለያዩ ዘመቻዎችን በማዘጋጀት በምርጫው ላይ ጣልቃ ገብቶ እንደነበር ይገልፃሉ። ይህም የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ቦቶችን በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ የዲሞክራት ፓርቲ የኢሜል መልዕክቶችን በመጥለፍ ወዘተ ተሳትፏል ተብሏል። ይህ የራሽያ ጣልቃ ገብነት በምርጫ ሂደቱ ላይ የነበረውን እምነት ከመሸርሸሩም ባለፈ በአሜሪካ ውስጥ ፅንፈኝነት እንዲነግስ አድርጓል።

  5. የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የተሰራጩ የውሸት መረጃዎች

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ስለ ቫይረሱ ምንጭ ፤ ስለክትባቱ እና ስለበሽታው አደገኛነት የሚመለከቱ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል። ይህም በማህበረሰቡ እና በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ መወዛገብና አለመተማመን አስከትሏል። ታድያ እነዚህ ሀሰተኛመረጃዎች የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ጎድቶታል።

  6. የራሽያው የቀድሞ ሰላይ መመረዝ

በፈረንጆቹ 2018 የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ የነበረ ሰርጌ ስክሪፓል እና ሴት ልጁ ዩሊያ በእንግሊዝ ሳሊስበሪ ከተማ በነርቭ ጋዝ ተመርዘው ነበር። የእንግሊዝ መንግስት ለጥቃቱ የሩሲያን መንግስት የወነጀለ ሲሆን በተቃራኒው ሩሲያ ይህንን ጥቃት የፈፀመው የእንግሊዝ መንግስት መሆኑን ገልፆ ነበር።

  7. የካታሎንያ የነጻነት ሪፈረንደም

በፈረንጆቹ 2017 በስፔን የምትገኘው ካታሎኒያ የመገንጠል /ህዝበ ውሳኔ/ ጥያቄ  አቅርባ ነበር። የስፔን መንግስት ይህን የመገንጠል ጥያቄ /ህዝበ ውሳኔው/ ህገወጥ ነው በማለት ተናግሮ ነበር። ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር። የመገንጠል ጥያቄ ደጋፊዎች መንግስት ሀሰተኛ መረጃን እያሰራጨ ነው ቢሉም በምላሹ የስፔን መንግስት እነዚህ የመገንጠል ጥያቄውን የሚደግፉ አካላት ሀስተኛ መረጃን እና አመፅን የሚቀሰቅሱ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚድያ ላይ እያጋሩ ነው በማለት ገልፆ ነበር።

  8. የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ህዝበ ውሳኔ

በፈረንጆቹ 2016 የእንግሊዝ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ህዝበ ውሳኔን አካሂዶ ነበር። ይህንን ተከትሎ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል። ከነዚያም መካከል እንግሊዝ ህብረቱን ለቃ ከወጣች በሳምንት እስከ 350 ሚልዮን ፓውንድ ታተርፋለች የሚሉ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር። በሌላ በኩል እንግሊዝ ህብረቱን ለቃ ከወጣች የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል የሚሉ የተጋነኑ ዘመቻዎችም ነበሩ። የሀሰተኛ መረጃ አስተዋፅኦ ለዚህ ህዝበ ውሳኔ እስካሁን ድረስ ለቀጠሉ ውዝግቦች መንስኤ ሆኗል።

  9. የ2015ቱ የስደተኞች ቀውስ

በፈረንጆቹ 2015 ግሪክ ለስደተኞች ወደ አውሮፓ መግቢያ ዋነኛ ቦታ ሆና ነበር። ይህንን ከፍተኛ የሆነ የስደተኛ ቁጥርን ተከትሎ በስደተኞቹ ላይ ያነጣጠሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር። ከዘመቻዎቹ መካከል የወንጀል ቁጥር ጨምሯል ፣ የሽብር ስጋቶች በርትተዋል የሚሉ ይገኙበታል።

  10. የዩክሬን ጦርነት

ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ግጭት እና የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻዎችን ነበሩ።  የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች የዩክሬንን መንግስት ፋሽሽታዊ አገዛዝ ነው ሲሉ ነበር። እነዚህ ዘመቻዎች ግጭቱን ሲያባብሱ እና በዩክሬንና ራሽያ ህዝቦች መካከል የጥላቻ ስሜት ሲቀሰቅሱ ኖሯል።

Similar Posts