በነሀሴ  2023  ከ40 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገፅ  አንድን ምስል የመከላከያ ጦር ሄሊኮፕተር በደብረ ማርቆስ  በፋኖ ታጣቂዎች  ተመቶ መውደቁን  ያሳያል በማለት  አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከሚታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ​​​​ 7000 እይታ በማግኘት ከ300 በላይ ግብረመልሶችን አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ቪድዮው ፋኖ በደብረ ማርቆስ የመከላከያን ሄሊኮፕተር መትቶ እንደጣለ እንደማያሳይ በማረጋገጥ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት  የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚጠራውን የታጠቀ ቡድን  ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው ። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና  በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል። ግጭቱ የተባባሰው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ ከተገደሉ በኋላ መንግስት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ‘ጽንፈኛ’ ያላቸው ታጣቂዎች እንዲዋጋ ባዘዘ ጊዜ ነው። አሁንም በአንዳንድ አከባቢዎች ግጭቱ እንደቀጠለ ነው።

እ.አ.አ. በነሀሴ 2023  የፋኖ ታጣቂዎች  አንዳንድ  ከተሞችን ተቆጣጥረው ነበር። መንግስትም ከተሞቹን መልሶ ለመቆጣጠር  መከላከያ ሰራዊት አሰማርቷል። በዚህም እነዚህ ትላልቅ ከተሞች መመለስ ችለዋል፣ ነገር ግን ግጭቱ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች እየተካሄደ ነው።

ይህ በፌስቡክ የተጋራው ምስል በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በደብረ ማርቆስ የመከላከያን ሄሊኮፕተር  መትተው እንደጣሉ ያሳያል ከሚል መረጃ ጋር ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ምስሉ ከዚህ በፊት ፌስቡክ ላይ በሚያዝያ 21 ቀን 2023 ታትሞ ከነበረው ቪድዮ የተወሰደ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። ቪድዮው እና ምስሉ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ሲበር በሞተር ብልሽት ምክንያት የተከሰከሰ የሚድሮክ ኢትዮጵያ (ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ) የሆነውን ሄሊኮፕተር ያሳያል።

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የፌስቡክ ፖስት ትክክል ያልሆነና የቆየ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts