ከ196ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ በሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ያሰራጨውን ቪድዮ “የምዕራብ ወለጋው ጭፍጨፋ በጥቂቱ ማሳያ ምስል..” የሚል ፅሁፍ በማያያዝ አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ቪድዮው ከ140ሺህ በላይ እይታ ሲያገኝ ከ3500 በላይ ግብረ መልስ አግኝቷል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪድዮውን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።  

ሰኔ 7 ፤ 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ዋና ከተማ የኦነግ ሸኔ እና የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግምባር ጥምር ሀይሎች ከከተማዋ ከመንግስት ሀይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው እንደነበር ተዘግቧል። እንደ ዘገባዎቹ ሁለቱ አማፅያን ሀይሎች በድንገት ከተማዋን በመቆጣጠር በመንግስት ሀይሎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል። 

ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ መንግስት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ገልጿል።

በተመሳሳይ ቀን እና በተቀራራቢ ጊዜ በደምቢ ዶሎ እና በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበርና በአንዳንድ ሪፖርቶች መሰረትም የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከተሞቹን በቁጥጥራቸው ስር ማዋላቸውን ገልጸው ነበር።  

ሰኔ 11 ፤ 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች በተፈጸመው ጥቃት በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ሺዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ነዋሪዎችን እማኝ ያደረጉ ዜናዎች በሰፊው ተሰራጭተዋል።

ሆኖም የኦነግ ሸኔ አለማቀፍ ቃል አቀባይ የሆነው ኦዳ ተርቢ በትዊተር አካውንቱ ዘገባውን አስተባብሏል።       

ኦነግ ሸኔ መረጃዎችን ይፋ በሚያደርግበት የኮምዩኒኬ ድረ-ገፁ ላይ መንግስት ያደራጃቸው “ጋቸና ሲርና” የሚል ስም የተሰጣቸው የሚሊሽያ ቡድኖች እንዳሉና እነሱም የኦነግ ሸኔ አባሎችን ለመምሰል አርቴፊሻል ዊግ እና ሹሩባዎችን እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

ሀቅቼክ ቪድዮውን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ቪድዮው ከዚህ በፊት ሐምሌ 16 ፤ 2013 ዓ.ም በአንድ የፌስቡክ አካውንት “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ፍርድ እየተሰቃዩ የነበሩትን በማስፈታት ነጻ አውጥቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዞ ወደ 4ኪሎ በሚል መርህ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱ ኮማንዶዎች በመገስገስ ላይ ይገኛሉ” በሚል ጽሁፍ ተጋርቶ ነበር። ይህ ቪድዮም ከ460 በላይ እይታን ማግኘት ችሏል። 

ሀቅቼክ በሁለቱ ቪድዮዎች ውስጥ ተመሳሳይ ሲቪል ሰዎችን እና ታጣቂዎችን መመልከት ችሏል።

በምዕራብ ወለጋ የተፈፀሙ የተለያዩ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች እንደተፈፀሙ ሪፖርቶች ቢወጡም ይህ የፌስቡክ ገፅ መረጃውን ለመደገፍ የተጠቀመው ቪድዮ የቆየ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።
ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

Similar Posts