ከሰሞኑ ፌስቡክ እና ዩቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አውታሮች የተጋራ አንድ ቪድዮ “የፌደራል መንግስt ወታደራዊ ድሮኖችን በመጠቀም በህወሓት አመራሮች ላይ ጥቃት ሲፈፅም የሚያሳይ ቪድዮ” በሚል መግለጫ ሲዘዋወር ተስተውሏል።

ፌስቡክ ላይ ተጋርቶ የነበረው ቪድዮ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ተመልካች ሲያገኝ በዩቲዩብ ላይ ተጋርቶ የነበረው ቪድዮ ከመቶ ሺህ በላይ እይታ ማግኘት ችሏል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪድዮው የፌደራል መንግስት ወታደራዊ ድሮኖችን ተጠቅሞ የህወሓት አመራሮችን ሲያጠቃ የሚያሳይ እንዳልሆነ አረጋግጧል። 

ጥቅምት 24 ፤ 2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ የፌደራል መንግስት ከሌሎች የክልል ልዩ ሀይል እና ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ህወሓትን ከመቀሌ እና ከሌሎች የትግራይ ዋና ዋና ከተሞች ማስለቀቅ ችሎ ነበር።  

ይሁን እንጂ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ይህ ጦርነት ህወሓት ከመቀሌ እና ከሌሎች ዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ከለቀቀ በኋላ የሽምቅ ውጊያን መጠቀሙን ተከትሎ ጦርነቱ ሊራዘም ችሏል።

ይህን ተከትሎ የፌደራሉ መንግስት በጊዜው ተቋቁሞ ከነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን ግንቦት ወር 2013 ዓም ላይ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም በማድረግ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የክልል ልዩ ሀይል እና ሚሊሻዎችን ከትግራይ እና አካባቢው አስወጥቷል።

ይህን የፌደራሉ መንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ህወሓት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን መልሶ መቆጣጠር ችሎ ነበር። ከዚህ በመቀጠልም ህወሓት ጦሩን ወደ አማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች አንቀሳቅሷል። ይህን ተከትሎ የህወሓት ሀይሎችም የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞችን ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ መቃረብ ችለው ነበር።    

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች ጥምር ሀይሎች በህወሓት ጦር ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ የፌደራሉ መንግስት በህወሓት ሀይሎች ተይዘው የነበሩ የአፋር እና አማራ ክልል ቦታዎችን መልሶ መያዝ ችሏል። 

መጋቢት 15 ፤ 2014 ዓ.ም ላይ የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ግጭት ለማቆም መወሰኑን ገልፆ ነበር። ህወሓትም በፌደራል መንግስት የተላለፈውን ይህን ውሳኔ እንደሚቀበል ገልፆ ነበር።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማደራደር ከሶስተኛ ወግን ሀሳብ መቅረቡን ተከትሎ የሰላም እና የድርድር ጥረቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም የቀድሞው የናይጄርያ ፕሬዝዳንት እና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ሊደረግ የታሰበውን የድርድር እና የሰላም ውይይት እንዲያግዙ በአፍሪካ ህብረት ተሹመዋል።

ፕሬዝደንት ኦባሳንጆም የድርድር ሂደቱን ለማስጀመር በተደጋጋሚ በሁለቱ ወገኖች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።       

ነገር ግን ህወሓት በፕሬዝደንት ኦባሳንጆ የሰላም ድርድሩ ለመምራት መመረጣቸው ላይ እንደማያምንበት እና ከፊደራል መንግስቱ ጋር በሚደረገው የድርድር ሂደት ላይ ድርድሩን ለመምራት ብቁነታቸው ላይ ጥያቄ እንዳለው አስታውቋል። 

ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ታንክ እና ከባድ መሳሪያዎችንም ተጠቅሞ ነሀሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጥቃት እንደሰነዘረበት ሕወሃት ገልፆ በመጋቢት ወር በሁለቱ ሀይሎች መካከል ተደርጎ የነበረውን ስምምነት የፈደራል መንግስት እንዳፈረሰው አስታውቋል።

በተጨማሪም ነሀሴ 18 ፤ 2014 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በደቡባዊ የትግራይ አቅጣጫ ጥቃት እንደከፈተባቸው ህወሃት ገልጿል። 

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት ይህ በህወሓት የቀረበው ውንጀላ ሀሰት መሆኑን በመናገር ህወሓት ወደ አጎራባች ክልልሎች ለመንቀሳቀስ የሚያረገውን ሙከራ ለማስቆም የትኛውንም ወታደርዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል።   

የፊደራል መንግስት እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ተከትሎ በፌደራል መንግስት አማካኝነት እየተደረገ ያለ የድሮን ጥቃት በማለት የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች [ቪድዮውች] ሲዘዋወሩ ቆይተዋል። ይህ በፌስቡክና ዩቲዩብ ጨምሮ የተሰራጨው ቪድዮም ከነዚህ አንዱ ነው። 

ይሁን እንጂ ቪድዮው የፌደራል መንግስት በህወሓት አመራሮች ላይ ያደረሰውን የድሮን ጥቃት እንደማያሳይ ሀቅቼክ ማረጋገጥ ችሏል።    

በቪድዮው መሃል ያለው የቪድዮው ክፍል በፈረንጆቹ 2020 በአዘርባጃን እና በአርሜንያ መካከል የተከሰተውና ናጎርኖ ካራባህ እየተባለ በሚጠራው ጦርነት የቱርክ ድሮኖች የነበራቸውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው። 

ሀቅቼክ ቪድዮውን ለማግኘት ባደረገው ጥረት የቪድዮውን ክፍል መጋቢት 29 ፤ 2013 ዓ.ም በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ተጋርቶ አግኝቶታል። 

በዚህም ምክንያትም ሀቅቼክ በፌስቡክ እና በዩቲዩብ ላይ ሲዘዋወር የነበረው ቪድዮ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

Similar Posts