ከ 7 ሺ በላይ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም በስፋት ሲዘዋወር የነበረ አንድ ቪዲዮ አጋርቷል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት ኢትዮጵያውያን የጦር እስረኞች ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች እጃቸውን ሲሰጡ እንደሚያሳይ በፅሁፍ መግለጫው ይናገራል።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ቪዲዮ ከስድስት መቶ ጊዜ በላይ የተጋራ ሲሆን በትዊተር ላይ ብቻ ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።

ይሁን እንጂ ቪዲዮው የቆየ እና በቅርቡ በቀጠለው ጦርነት በህወሓት ሃይሎች የተያዙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እንደማያሳይ ማረጋገጥ ተችሏል።

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት ሃይሎች መካከል ለሰብአዊ እርዳታ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ነሀሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሁለቱ ሀይሎች መካከል ዳግም ግጭት አገርሽቷል።

ነሀሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ሕወሓት በመጋቢት ወር መጨረሻ በጋራ የታወጀውን ጦርነት ማቆም ቀድሞ የፌደራል መንግስት እንደጣሰ በመግለጽ የፌደራል መንግስት ሃይሎች በመድፍና በታንክ በመታገዝ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተናግሯል።

ሕወሃት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት በህወሓት ሃይሎች ተይዘው ወደሚገኙ ግዛቶች ለመዝመት የሞከሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ ጦር ክፍሎችን እንደደመሰሰ መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም ገልጿል።

ይህን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተማረኩ የጦር ምርኮኞችን እንደሚያሳይ በመግለጽ ቪዲዮው እንደገና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሊጋራ ችሏል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከዚህ ቀደም ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ድምጽ አማርኛ የፌስቡክ ገጽ ላይ “የትግራይ ክልል መንግሥት የጦር ምርኮኞች እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታወቀ” በሚል ዜና ስር የተጋራ መሆኑን ሀቅቼክ አረጋግጧል። 

ስለሆነም ሀቅቼክ የትዊተር ፖስቱ መረጃውን እንዲደግፍለት የተጠቀመውን ቪዲዮ የቆየና ከተገለፀው ሁነት ጋር ተያያዥነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts