በነሃሴ 9 2023 እአአ ከ12 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የቲክቶክ ገፅ በእስር ላይ የነበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር መፈታታቸውን ያረጋግጣል በማለት  ይህንን  ቪድዮ አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ ቪድዮው 3439 ጊዜ ያህል ተጋርቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ቪድዮው አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር መፈታታቸውን  እንደማያሳይ አረጋግጧል። በዚህም የቲክቶክ ፖስቱ ሀሰት ብሎታል።

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል

የፌደራል መንግስት የክልሉ ልዩ ሀይል አባላትን ለመበተን በወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል ሰፊ ተቃውሞ አጋጥሞታል።

ይህ ውሳኔ  ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀሰቅስና ክልሉ ውስጥ ትጥቅ ግጭት እንዲስፋፋ አድርጓል። በዚህም የፋኖ ታጣቂዎች ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ብዙ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችለው ነበር። ይህንን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት  በጠየቀው እርዳታ መሰረት በሀገሪቱ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት መንግስት ፖለቲከኞችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን አስሯል። የቀድሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት አቶ ክርስቲያን ታደለ በአዋሽ አርባ እስረኛ ማቆያ ካምፕ እንደሚገኙ አረግጧል

በዚህ መነሻነት አቶ ክርስቲያን ታደለ በቅርቡ ከእስር እንደተለቀቁ የሚገልጽ የቲክቶክ ቪዲዮ ተሰራጭቷል።

ይሁን እንጂ ቪድዮው ከዚህ በፊት በመጋቢት 9 ቀን 2020 እአአ በአስራት ሚዲያ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ታትሞ ከነበረው ቪድዮ ላይ ተቆርጦ የተወሰደ እንደሆነ ሀቅቼክ አረጋግጧል። ቪዲዮው አቶ ክርስቲያን ታደለ በግዜው አዲስ አበባ በተዘጋጀ የሕዝብ ውይይት ላይ ንግግር ሲያደርጉ የሚያሳይ ነው።

ስለዚህም ሀቅቼክ ይህን የቲክቶክ ልጥፍ ትክክል ያልሆነና የቆየ ቪድዮ በመጠቀሙ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts