ኣርሓ ወያናይ ተጋሩ የተባለ ከ5000 በላይ ጓደኞች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ የሁለት ሰዎችን ምስል በኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ተገደሉ በማለት ታህሳስ 17፣ 2013 ዓ.ም ለቆ ነበር። ምስሉን ለመደገፍ በትግርኛ የተጻፈው ጽሑፍ “….የአውሬዎች ዘር! የኤርትራ ወታደሮች እነዚህን ሁለት ንፁሀን ሰዎች በትግራይ ገደሉ ፡፡ በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ!” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ሁለቱ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች ሲገደሉ የማያሳይ እና ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል ፡፡

ከጥቅምት 28፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል መንግስት እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ መካከል በትግራይ ክልል ውስጥ ቀጣይነት ያለው ግጭት ተከስቷል። ግጭቱን ተከትሎም የፌደራል መንግስት በኤርትራ መንግስት ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ ተደጋጋሚ ያልትጣሩ መረጃዎች እና ክሶች ሲወጡ ይሰማሉ። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ኃይሎች በወታደራዊ ዘመቻው ውስጥ እንዳልተሳተፉ ደጋግሞ አስተባብሏል

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው በፌስቡክ ተጠቃሚው የተለቀቀው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ህዳር 21፣ 2010 ዓ.ም awaale afcad በተባለ የትዊተር ገፅ ሲሆን ከምስሉ ጋር ተያይዞም “በሊቢያ ውስጥ” የሚል ፅሁፍ ይነበባል። ምስሉ ከሌሎች ሦስት ምስሎች ጋር ተያይዞ ነበር የተለቀቀው። 

በህወሃት በሚመራው የትግራይ ክልል ኃይል እና በፌዴራል መከላከያ ሰራዊት መካከል በተነሳው ግጭት ኤርትራ ተሳትፋለች የሚሉ ክሶችና ያልተረጋገጡ መረጃዎች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ሁለት ሰዎችን የሚያሳየው ምስል በትግራይ ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን የሚያረጋግጥ ባለመሆኑን እና ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ምስል በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts