በ19 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Afmeer tv. የተባለ 224,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ አንድ ባለ አንድ ጋቢና ወታደራዊ ተሽከርካሪ እና ወታደሮችን የሚያሳይ ምስል፤ የሶማሌ ልዩ ኃይል እና የአፋር ክልል ኃይሎች በሲቲ ዙሪያ (ቀድሞ ሺኒሌ ዞን በመባል የሚታወቀው) ድንበር ላይ ከፍተኛ ፍልሚያ እያካሄዱ እንደሆኑ እና በግጭቱም በአፋር ክልል ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰና ሶስት ንፁሀን ሶማሌዎች ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል ከሚል ፅሁፍ ጋር አጋርቷል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከዚህ በታች ያሉው የፀትታ ሀይሎችን የሚያሳየው ምስል ከግጭቱ ጋር እንደማይገናኝና በቅርቡ በሶማሌ እና በአፋር ክልል ኃይሎች መካከል የተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጧል። በመሆኑም መረጃውን ሃሰት ብሎታል። .

በኢትዮጵያ የሚገኙት የአፋር ብሄረሰብ አባላትና የኢሳ ሶማሌ ብሄረሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ግጭት ውስጥ ከገቡ ከ10 አመታት በላይ ተቆጥሯል። በድንበር አከባቢዎች በተለይም ከሶማሌ ክልል ዘጠኝ ዞኖች አንዱ በሆነው በሽንሌ ዞን እና በአፋር ክልል ገቢ ራሱ እና አውሲራሱ ዞኖች መካከል የእርስ በርስ ግጭቶች እንደነበረም የሚታወቅ ነው። አክራካሪዎቹ ግዛቶች ኡንዱፎ ፣ ገዳማይቱ እና አዳይቱ ከተሞች በሁለቱ የአፋር ዞኖች ውስጥ ይገኛሉ። በርካታ የኢሳ ሶማሌዎች በአፋር ክልል በገቢ ራሱ እና በአውሲረሱ ዞኖች በሚገኙ ከተሞች ውስጥ በመስፈራቸው ምክንያት የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች እና ግጭቶች በየጊዜው ይነሳሉ። በ2006 ዓ.ም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አነሳሽነት የሶማሌ እና የአፋር ክልላዊ መንግስታት በመካከላቸው ላለው የድንበር ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ይሆን ዘንድ የሰላም ስምምነት ተስማምተው የተፈራረሙ የነበረ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት ሶስቱ አወዛጋቢ ግዛቶች ወደ አፋር ክልል ማለትም ገዳማይቱ ወደ አሚባራ ወረዳ ፣ ኡንዱፎ ወደ ገዋኔ ወረዳ እና አዳይቱ ወደ ሚሌ ወረዳ እንዲዋሀዱ ተደርጎ ነበር። ሆኖም በ2011 ዓ.ም የሶማሌ ክልል ሶስት ቀበሌዎችን ለአፋር ክልል ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና  በአከባቢው ህዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ እና ህገ-መንግስታዊ ያልሆነ ውሳኔ ነው በማለት ከስምምነቱ ውጪ እንደሆነ ማስታወቁም የሚታወስ ሲሆን ከሁለት ወራት በፊት በሁለቱ የክልል ሃይሎች መካከል አዲስ የትጥቅ ግጭት ተከስቶ የ27 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ በፌስቡክ ጽሁፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረ ግጭት አይደለም፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው 26 ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ፌስቡክ ላይ ተለቆ ሲሆን ግጭቶች በክልሉ ኃይሎች መካከል ሲካሄዱ እንደነበር ይገልፃል።

Original Image:

በአፋር እና በሶማሌ ክልል ድንበር ዙሪያ ለአስርተ ዓመታት የዘለቁ ግጭቶች መኖሩ እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ምስሉ በሶማሌ እና በአፋር ክልል ኃይሎች መካከል ከተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ጋር የማይገናኝ እና በአሁን ሰአት በክልሎቹ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የማያሳይ ስለሆነ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts