በ 27 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Selam Nkulu (ሰላም ንኩሉ) በተባለ ከ3,500 በላይ ጓደኞቻቸው ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በተካሄደው ግጭት ወቅት አነስተኛ ምሽግ ውስጥ ምግብ እና የመኝታ ቁሳቁሶች ይዘው የወጡ ወታደሮችን የሚያሳይ ነው በማለት አንድ ምስል አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “የሱዳን ወታደሮች አልጋቸውን ይዘው ወደ ምሽግ መጡ። ሻዕቢያ (ኤርትራ) እና የፎጣ ለባሾች (የአማራ ክልል ኃይሎች) ካዩ ዛሬ ውጊያው ሊጀምሩ ይችላሉ። ኦህህ እናንተ ሱዳኖች ቁጭ ብላቹ በምግቡ ተደሰቱ” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከዚህ በታች ያለው ምስል ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እና ልጥፉ ስላቅ እንደሆነ አረጋግጧል። 

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። በ11 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ስር የነበረውን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ግዛቶች የሱዳን ጦር ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። በድንበር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ሱዳን ወታደሮችን ወደ ድንበሩ አካባቢዎች እያሰማራች መሆኗን የተለያዩ ዘገባዎች አውጥተዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በ9 ታህሳስ 2013 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከ30 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የተደራጁ ጥቃቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች ተዘርፈዋል፣ ካምፖች ተሰብረዋል፣ አርሶ አደሮች የራሳቸውን እርሻ እንዳያጭዱ ተስተጓጉለዋል እንዲሁም በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል ብለዋል። ሁለቱ ወገኖች ሪፖርታቸውን ለሁለቱ አገራት አመራሮች ለማቅረብ የተስማሙ እና የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን የድንበር ማካለል ስራው በፍጥነት እንዲጀመር ወስነዋል።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለው የምስል ማጣሪያ፣ የፌስቡክ ልጥፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አለመሆኑን ያሳያል። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው 22 ግንቦት 2012 ዓ.ም በፌስቡክ ላይ ሲሆን የተለቀቀውም “በጠረፍ ድንበሮች በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወታደሮች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ” ከሚል ጽሑፍ ጋር ነበር።

 

ድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች መከሰታቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት በምሽግ ውስጥ የመኝታ ቁሳቁሶችን እና ምግብ ይዘው የሚታዩትን ወታደሮች የሚያሳየው ይህ ምስል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር እንደማይገናኝ እና የፌስቡክ ልጥፉ ስላቅ መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts