ታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም አነ ንባእላ ትግራይ (15,849 ተከታዮች ያሉት አካውንት) በተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ አንድ የፌስቡክ መልእክት በተለቀቀ መልዕክት ከዚህ በታች በገለባ ላይ ተኝቶ የሚያታየውን ሰው ምስል (ፅሁፉ ግለሰቡ ሴት ናት ይላል) በትግራይ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በረሃብ ምክንያት ሞቶ የተገኘ ሰው ምስል ነው ሲል ገልጿል። በትግርኛ የተፃፈው ጽሑፍ “በትግራይ ከጥይት ያመለጡ ሰዎች  በረሃብ ምክንያት እየሞቱ እንደሆነና “በአለም ውስጥ ያሉ የትግራይ ተወላጆች እና የትግሬ-ወዳጆች እንዲያዩት እባክዎን ያጋሩ” የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እንዲሁም “ንብረት ተዘርፏል ፣ ኤሌክትሪክ ሀይልም የለም ፣ ባንኮች በመዘጋታቸው ምክንያት ገንዘብ የለም” በማለት የፌስቡክ ተጠቃሚው ምስሉን በዓለም ዙሪያ እንዲያካፍሉ ይለምናል። ሆኖም ሀቅቼክ ከዚህ በታች ያለው ምስል ትግራይ ውስጥ ያሉትን እውነታዎች እንደማያሳይ አረጋግጧል። ስለዚህ የፌስቡክ ተጠቃሚው ምስሉን በሐሰት ያቀረበውን መረጃ ለመደገፍ በመጠቀሙ ብይኑ ሐሰት ሆኗል ፡፡

 

ከ25 ጥቅምት 2013 ጀምሮ በፌዴራል መንግስት በሚመሩ ሃይሎች እና በህወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ አለመረጋጋት መከሰቱ እርግጥ ነው። በክልሉ የተከሰተው ግጭት እና ሌሎች (እንደ የበረሃ አንበጣ ወረራ እና COVID19 ያሉ) ችግሮች በትግራይ ክልል እየተባባሰ ለሚገኘው የሰብዓዊ መብት ቀውስ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ግጭቱ የህውሀት ሀይሎች በሰሜን እዝ ላይ ያደረሱትን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የትራንስፖርት፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎት በክልሉ ተዘግተው የቆዩ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ የትግራይን ዋና ዋና ከተማዎችን  ከተቆጣጠሩ በኋላ በክልሉ የግንኙነት መስመርና የሰብዓዊ እርዳታ መስመርን ለመመለስ እየሰራ ይገኛል። እንደ UNHCR UNOCHA እና ICRC  ያሉ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በክልሉ የምግብ ፣ የመድኃኒትና የሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት እንዳለ እንደገለፁ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡ የፌዴራል መንግሥት ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል በሺዎች የሚቆጠር ኩንታል የምግብ ምርቶችን  ወደ መቀሌ እና ሽሬ ከተማዎች ልኳል ፡፡ 

ምስል 1: የተቀየረ ምስል (“ኣህህህ እናት!” ከሀዘን ስሜት ገላጭ ምስል ጋር)

 

ምስል 2: ዋናው ምስል 

 

ሆኖም በፌስቡክ አካውንቱ የወጣው ምስል ሪቨርስ ኢሜጅ በተሰኘው የምስል ፍለጋ ዘዴ በሚመረመርበት ወቅት በጭድ ላይ ተኝቶ የሚታየው ግለሰብ ከትግራይ አለመሆኑን ያመላክታል። በአንፃሩ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካው የማህበራዊ ሚድያ ድህረገፅ ሬዲት (Reddit) ላይ በ16 ህዳር 2013 ዓ.ም በኔፓል ቋንቋ በተጻፈ ጽሑፍ ጋር የቀረበ ምስል እንደነበረ ማየት ይቻላል። የሬዲት ተጠቃሚው ምስሉን ከተተረጎመው ጽሑፍ “በኬፒ ኦሊ ( የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር) ቋንቋ በአገሪቱ ውስጥ ብልጽግናን ማየት የሚፈራ ብሄራዊ ያልሆነ አካል ነው” ከሚለው መልዕክት ጋር አጣምሮ  ያቀረበ ሲሆን ጽሁፉን የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማግኘት ይቻላል፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲኔካላ (cinekala.com) የተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ድህረገፁ ላይ ግለሰቡ የ77 ዓመት ዕድሜ ያለው የራይ (የኔፓል የብሔረሰብ ቋንቋ ቡድን) ብሄር አባል እንደሆነ እና ለ10 ዓመታት እንደታመመ በመግለጽ እራፊ የጨርቅም ሆነ አልጋ ስላልነበረው በገለባ ላይ ተኝቶ እንደተገኘ አስነብቧል። ታሪኩን የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡

ሀቅቼክ ጽሁፉን ከመረመረ በኋላ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ጊዜ የተነሳ ምስል አለመሆኑን አረጋግጧል። በምስሉ ላይ የሚታየው ሰውም በትግራይ ክልል ሞቶ አልተገኘም። በመሆኑም መረጃውን ያጋራው አካል ሀሳቡን ለመደገፍ የተሳሳተ ምስል በመጠቀሙ ምክንያት ሀቅቼክ ከላይ የተጠቀሰውን መረጃ ሐሰተኛ ነው ብሎ ደምድሟል፡፡

አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ

 

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

 

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።

Similar Posts