በ30 ህዳር 2013 ዳዊት እንጢቾ በተባለ 5000 ጓደኞች እና 541 ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ በመሸታ ቤት ውስጥ መጠጥ እየጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ክልል ባለው ተልዕኮ ወቅት በግዳጅ ላይ ያለ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት አባል ነው በማለት ከታች የተቀመጠውን መረጃ አጋርቷል። ፅሁፉም “የብልፅጋና ፓርቲ ህግን በማስከበር ላይ ነው” ሲል ይነበባል፡፡ ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መጠጥ እየጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ክልል መሆኑን የሚያሳይ ያለመሆኑን ተከትሎ መረጃው ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡ 

በፌደራል መንግስት እና በህውሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ መካከል ከ29 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግጭት መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ ከሶስት ሳምንታት ውግያ በኋላ የፌደራል መንግስት ሀይሎች መቀሌ፣ ሽሬ፣ አዲግራት፣ አክሱም እና የተለያዩ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠራቸው የሚታወቅ ሲሆን የህወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ፒ.ኤች.ዲ) እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም በተለያዩ ወቅቶች የህወሃት አመራሮችና እና የትግራይ ልዩ ሀይል አባላት በመቀሌ ከተማ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ውድመት ለመቀነስ ሲባል ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን እንደገለፁ የሚታወቅ ነው። እነዚህ መረጃዎች የሚያሳዩት የፌደራል የመከላከያ ሰራዊትና እና የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ የትግራይ ክፍል ውስጥ ተሰማርተው በህግ ማስከበር ስራ ላይ እንደሚገኙ ነው።

 

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች የተባለ የምስል ማጣሪያን በመጠቀም የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክተው ከሆነ በፌስቡክ ተጠቃሚው የተለቀቀው ምስል በትግራይ በነበረው ግጭት  ጊዜ የነበረ አይደለም፡፡ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በ11 ህዳር 2013 ዓ.ም ፍራንክ ጋሹምባ በተባለ የኡጋንዳ የማህበረሰብ አንቂ (አክቲቪስት) እና ብሎገር  ነበር፡፡ በጊዜው ፍራንክ ጋሹምባ ምስሉን የለቀቀው “የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን የሚያስከብረው ወታደር” በማለት ከፃፈው የእንግሊዘኛ መልዕክት ጋር ነበር። በመሆኑም ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ በምስሉ ላይ ሲጠጣ የሚታየው ወታደር በትግራይ ውስጥ አለመሆኑን እና ወታደሩ የትግራይ ህዝብን ንብረት ሲበዘብዝ የሚያሳይ እንዳልሆነ ማረጋገጡን ተከትሎ ምስሉን ሀሰት ነው በማለት ፈርጆታል፡፡ 

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

 

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

 

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ 

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

Similar Posts