አዲስ ስታንዳርድ በፌስቡክ ላይ ከ151,000 በላይ ተከታዮች ያሉት በትዊተር ላይ ደግሞ ከ180,000 በላይ ተከታዮች ያሉት በኢትዮጵያ የሚገኝ የዜና አውታር ነው። አዲስ ስታንዳርድ በድህረ-ገፁ ላይ በእንግሊዘኛ በተፃፈ ርዕስ “ዜና: የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቃዋሚ ፓርቲ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በመጪው ምርጫ ላይ እንደማይሳተፍ ገልጿል” የሚል ርእስ ያለው የትዊተር ፅሁፍ ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡ ይህንኑ ፅሁፍ በፌስቡክ እና በትዊተር ገፆቹም በማጋራት ላይ ይገኛል ፡፡ ድህረ-ገጹ ፓርቲው በኦሮምኛ እና በአማርኛ የላከውን መግለጫ እንደ ማስረጃነት በመጠቀም ከላይ የተጠቀሰውን መረጃ ከላይ በተቀመጠው ርዕስ ስር አቅርቧል፡፡ ሆኖም ሀቅቼክ በዜና አውታሩ የቀረበውን ፅሁፍ እና ማስረጃ በመመርመር አሳሳች ርዕስ እንዳለው አረጋግጧል፡፡

በኢትዮጵያ በመጪው ምርጫ ይሳተፋሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ጠንካራ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አንደኛው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል እንደፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና (PHD) ፣ እንደምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እና እንደጃዋር መሃመድ የመሳሰሉ ግለሰቦችን ያካተተ ፓርቲም ነው። በአሁኑ ጊዜ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት በሽብርተኝነት ፣ በዓመፅ ቅስቀሳ ፣ በቴሌኮም ማጭበርበር እና በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ክስ ተከሰው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸው ይታወቃል፡ ፡አቶ ጃዋር መሀመድ በአራቱም ወንጀሎች ተጠርጥረው የተከሰሱ ሲሆን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በአንፃሩ ከቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ውጪ በሁሉም ክሶች በጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደቀረበባቸው የሚታወቅ ነው። በቅርቡም አቶ በቀለ ገርባ እና ጃዋር መሀመድ የሀገሪቱን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን ምክንያት በማድረግ ያለፈውን የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ለመቅረብ ፈቃደኛ ያመሆናቸውን ገልፀው በጊዜያዊ ማቆያቸው አቅራቢያ በሚገኝ ጊዜያዊ ችሎት መቅረብ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ኦፌኮ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አብዛኛዎቹ አመራሮቻቸው እና አባላቶቻቸው የታሰሩ በመሆናቸውና ከዋና መስሪያ ቤቱ ውጭ ያሉ ቢሮዎቻቸው በመዘጋታቸው በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ “እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል” የሚል መግለጫ አውጥቷል ፡፡ .

ምስል 1-ከኦፌኮ የተሰጠ መግለጫ በአማርኛ

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ሶስት ነገሮችን እንዲሟሉለት መጠየቁ ሀቅ ነው። (እነዚህም በእስር ላይ ያሉ የኦፌኮ አመራሮች እና አባላት እንዲለቀቁ ፣ የተዘጉ የኦፌኮ ቢሮዎች ተመልሰው እንዲከፈቱ እና ለምርጫ ቅስቀሳ እና ሌሎች የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ አመቺ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋዋል)። አዲስ ስታንዳርድም ከላይ የተጠቀሰውን የኦፌኮ መግለጫ በጽሁፉ አካል ውስጥ በሚገባ ገልፆታል፡፡ አዲስ ስታንዳርድ ባወጣው ፅሁፍ መልእክቱን እንደ አርዕስተ ዜና የተጠቀመው ቢሆንም ከላይ በተጠቀሰው ደብዳቤም ሆነ የኦሮምኛ አቻው ፓርቲው አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታዎች ውስጥ በምርጫ ላይሳተፍ እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች ቢያቀርብም ፓርቲው በመጪው ምርጫ በእርግጠኛነት አንካፈልም የሚል መልእክት እንዳልያዘ መገንዘብ ይቻላል። ምንም እንኳን የፅሁፉ ዋና አካል አርዕስቱን በትክክል እንዳብራራ መከራከር ቢቻልም ፣በኮሎምብያ ዩንቨርስቲ በተደረገ ጥናት 60 ፐርሰንት የሚሆኑት የትዊተር ተጠቃሚዎች የትዊተር መልእክቶችን የሚያጋሩት አርዕስቱን  ሳያነቡ እንደሆነ ያሳያል። ይህም እንደነዚህ ያሉ ርዕሶች ህዝብን ለማሳሳት ያላቸውን አቅም የሚያሳይ ነው። 

በዚህም ምክንያት ሀቅቼክ የፅሁፉን አርዕስት በጥልቀት ከመረመረ በኋላ (ዋና የፅሁፉን አካል ሳያጠቃልል) አሳሳች ርዕስ በማለት መረጃውን ፈርጆታል። ለዚህ ውሳኔ ምክንያቱ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተጻፈው አርዕስት ላይ የተጠቀሰውን መልእክት  ፓርቲው በመግለጫው ላይ ባለማስተላለፉ ነው።

አጣሪ: አብዱላሂ አብዱልቃድር

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።

Similar Posts