አንድ የፌስቡክ ፖስት ግንቦት 7 ፤ 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ የታጠቀቻቸው C-130 ሄርኩሊዝ ጀቶች የሚል ፅሁፍን አያይዞ አምስት ምስሎችን አጋርቶ ነበር።

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ከ44 ጊዜ በላይ ሲጋራ ከ500 በላይ ግብረ መልሶችንም ማግኘት ችሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ መረጃውን በከፊል ሀሰት ብሎታል። 

በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን ድረስ ያልተፈታ ችግር ሆኗል። 

ከጥቂት ወራት በፊት ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በሚል በፌደራሉ መንግስት የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት በህወሓት ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ ሲሆን ይህ ስምምነት ለሰላም ንግግር እና ግጭቱን ለማቆም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተገምቶ ነበር። 

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከታወጀ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና በህወሓት አመራር በሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መካከል የቀጥታ የስልክ ንግግር (ውይይት) ተደርጓል የሚሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር።

በዩትዩብ በተለቀቀ አንድ የድምፅ መረጃ መሰረት የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራር የሆኑ አንድ ሰው ከታደሰ ወረደ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም የሆኑት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን በሞሪሽየስ አግኝተው እንዳወሯቸው ገልፀዋል። 

ነገር ግን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከህወሓት አመራሮች ጋር ተገናኝተው ስለ መወያየታቸው የሚሰራጨውን መረጃ ሀሰት እና መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል።

ህወሓት በመግለጫዎቹ ግጭቱን ለማቆም ሰላማዊው መንገድ የማይሳካ ከሆነ በጦርነቱ እንደሚቀጥል ገልጿል

ህወሓት በተለያዩ ጊዜያቶች የፌደራል መንግስቱ እና የክልል ባለስልጣናት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እየከለከሉ ነው በሚል በተደጋጋሚ የተለያየ ክስ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን አሁንም ወደ ትግራይ ክልል የደረሰው እርዳታ በቂ አለመሆኑን ተናግሯል።

ከሳምንታት በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በሁመራ በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንፃሩ ህወሓት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የህዝብ ለህዝብ ውይይት አካሂዶ የነበረ ሲሆን የህወሓት አመራር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ፤ ፈትለወርቅ ዘውዴ ፤ ጌታቸው ረዳ እና አለም ገብረዋህድ ተገኝተው ውይይቱን መርተውታል።

ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ የህዝብ ውይይት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “ለሰላም ያደረገነው ጥረት ስላልተሳካ አሁን ለመጨረሻው የጦርነት ምዕራፍ እንድትዘጋጁ” በማለት ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ አዳዲስ የወረራ እና የግጭት ሪፖርቶች እየወጡ የሚገኙ ሲሆን ይህም ሁኔታ ሀገሪቷ በድጋሚ ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነት እንዳትገባ ስጋትን ፈጥሯል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ህወሓት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው በማለት ህወሓት ወደሌላ ጦርነት እንዳይገባ  የአውሮፓ ህብረት ጫና እንዲያደርግበት የፈደራሉ መንግስት ጠይቋል።  

ይህ የፌስቡክ ፖስትም ኢትዮጵያ ያሏትን የC-130 ሄርኩሊዝ አውሮፕላን ጀቶችን ያሳያል በማለት አምስት ምስሎችን አጋርቷል። 

የአሜሪካ መንግስት ግንቦት 29 ፤ 2010 ዓ.ም ላይ C-130 ሄርኩለስ የጦር አውሮፕላኖችን ሀገሪቱ ለምታካሄደው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲያግዛት ለኢትዮጵያ አስረክቧል። 

የፌስቡክ ፖስቱ ከተጠቀመባቸው ምስሎች መካከል አንዱ ይህ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የለገሰችው የጦር አውሮፕላን ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ከአምስቱ ምስሎች ቀሪዎቹ አራቱ የተወሰዱት ከሌላ እትሞች ሲሆን ኢትዮጵያ የታጠቀችውን C-130 ሄርኩለስ የጦር አውሮፕላኖችን አያሳዩም።   

ምስል አንድ

ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ የተለቀቀው ይህ ቪድዮ የAirbus A400M የጦር አውሮፕላን ያሳያል። 

ምስል ሁለት 

ምስሉ በየካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካ የመከላከያ ዲፓርትመንት ትዊተር ገፅ ላይ ከተለቀቀ ቪድዮ ላይ ተቆርጦ የተወሰደ ሲሆን ምስሉ የሚያሳየው በቅፅል ስሙ “የሞት መልዓክ” ወይም “Angel of Death” የተሰኘውን AC-130 የተባለ ሄርኩሊዝ የጦር አውሮፕላን ነው። 

ምስል ሶስት 

ምስሉ የተወሰደው በአሜሪካ የመከላከያ ዲፓርትመንት በኩል ከተለቀቀ ቪድዮ ሲሆን ከአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የተሰጠውን የC-130 ሄርኩለስ የጦር አውሮፕላን ላይ ከአሜሪካ የመጡ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያውያን አብራሪዎች እና ቴክኒሽያኖች ትምህርት እየሰጡ እንደሆነ የሚያሳይ ምስል ነው።

ምስል አራት 

ምስሉ በግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ከተለቀቀ ቪድዮ ላይ በመውሰድ የተጋራ ሲሆን ይህ የዩቲዩብ ቻናልም መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ ከተጋራ ሌላ የዩቲዩብ ቪድዮ ላይ የተወሰደ ነው። ቪድዮውም የአሜሪካውን C-130 ሄርኩለስ የጦር አውሮፕላንን ያሳያል። 

ምስል አምስት

እንደ ምስል አራት ሁሉ ምስል አምስትም ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ከተለቀቀ የዩቲዩብ ቪድዮ ላይ የተወሰደ ሲሆን ይህ የ ዩቲዩብ ቻናልም መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም ከተለቀቀ ሌላ የዩቲዩብ ቪድዮ ላይ የወሰደ ሲሆን ቪድዮው የአሜሪካውን C-130 ሄርኩሊዝ የጦር አውሮፕላን ጥንካሬን የሚያሳይ ነው።

ይሁን እንጂ የፌስቡክ ፓስቱን ለመደገፍ ከተጋሩት  ከአምስቱ ምስሎች መካከል አንዱ ምስል ብቻ የኢትዮጵያን C-130 የሚያሳይ ሲሆን የቀሩት አራት ምስሎችይህን አውሮፕላን አያሳዩም።
ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን በከፊል ሀሰት ብሎታል።   

Similar Posts