አንድ የፌስቡክ ገፅ  ይህንን (ከታች ያለው) ምስል  የመከላከያ ጦር ሄሊኮፕተር በፋኖ ታጣቂዎች ተመቶ መውደቁን  ያሳያል በማለት አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከታተምበት ጊዜ ድረስ ፖስቱ ከ21 ጊዜ በላይ በመጋራት የብዙዎችን እይታ አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ምስሉ ፋኖ  የመከላከያን ሄሊኮፕተር መቶ እንደጣለ እንደማያሳይ በማረጋገጥ የፌስቡክ ፖስቱን ሀሰት ብሎታል።  

እ.አ.አ በየካቲት 2023 የኢትዮጵያ መንግስት  የክልል ልዩ ሀይሎችን እንዲበተኑ እና ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ወስኗል። ይህም በአማራ ክልል የሚገኘውን ፋኖ በመባል የሚጠራውን የታጠቀ ቡድን  ያበሳጨና ተቃውሞ ያስነሳ ነው ። ይህን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎችና  በመንግስት ወታደሮች መካከል ብዙ ግጭቶች ተካሂደዋል።

እ.ኤ.አ. ነሀሴ 11 ቀን 2023 የወጡ ዘገባዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎች እንዳመላከቱት በዚህ ግጭት ሳቢያ በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል።

ምንም እንኳን መንግስት የአማራ ክልል ትላልቅ ከተሞችን መልሶ ቢቆጣጠርም አሁንም በኢትዮጵያ ሰራዊት እና በፋኖ ሚሊሻ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት ቀጥሏል።

ይህ በፌስቡክ የተጋራው ምስል በአማራ ክልል  የፋኖ ታጣቂዎች የመከላከያን ሄሊኮፕተር መትተው እንደጣሉ ለማሳየት የቀረበ ነው። ይህ መረጃ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሀቅቼክ የጉግል ተገላቢጦሽ ምስል መፈለጊያን በመጠቀም ምስሉን መርምሯል። በዚህም ምስሉ ከዚህ በፊት በአንድ ድህረገጽ ላይ እ.አ.አ በመጋቢት 3 ቀን 2023 የታተመ መሆኑን አረጋግጧል።

በምስሉ ላይ የሚታየው አንድ የሮማንያ የጦር ሄሊኮፕተር ሲሆን በጥቁር ባህር ላይ የጠፋው የሮማንያ ተዋጊ ጄትን ለመፈልግ እየበረረ ባጋጠመው ችግር የተከሰከሰ ነው።

ስለዚህ ሀቅቼክ  ይህ የፌስቡክ ፖስት የቆየና ትክክለኛ ያልሆነ ምስልን በመጠቀሙ ምክንያት ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts