በ12 ጥር 2013 ዓ.ም Afmeer tv. የተባለ (ከ237,000 በላይ ተከታዮች ያሉት) የፌስቡክ ገፅ በርከት ያሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ከወታደሮች ጋር የሚያሳይ አንድ ምስል አጋርቷል። በፌስቡክ ልጥፉ ላይ በሶማሊኛ የተፃፈው ጽሑፍ “5000 የሚደርሱ የግብፅ መከላከያ ሠራዊት የሱዳን ጦርን ለማገዝ ሱዳን መድረሳቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አትተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሱዳንና ኤርትራ ድንበር አከባቢዎች ከ3000 በላይ የሚሆኑ የሱዳን ጦር ሠራዊት እየገሰገሱ ሲሆን ጉዳዩ እየተባባሰ ነው።” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ ምስሉ በሱዳን የተሰማሩ 5,000 የግብፅ ወታደሮችን ስለማያሳይ እና መረጃውን ለመደገፍ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ልጥፉን ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ የታጠቁ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። በድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች በሱዳን ጦር ላይ ያደረጉት ጥቃት “ተገቢ ያልሆነ ጥቃት” ስትል ግብፅ አውግዛለች። ከዚህም በተጨማሪ ግብፅ ለሱዳን ሙሉ አጋርነቷን እና አገሪቷ ግዛቷን የመጠበቅ መብቷን መደገፏን አረጋግጣለች። ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ድንበር አከባቢዎች መላኳን እና ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጹ መረጃዎችም እየወጡ ይገኛሉ።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያመለክተው በልጥፉ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የሱዳንን ሀይሎች ለመደገፍ በሱዳን ድንበር ላይ ተሰማርተው ያሉ የግብፅ ወታደሮችን አያሳይም። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በ7 የካቲት 2010 ዓ.ም አህራም ኦንላይን (Ahram Online) በተባለ ድረ ገፅ ላይ የተለጠፈው ሲሆን በሲና በረሃ በአሸባሪዎች እና በወንጀል ቡድኖች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መወሰዱን ለማሳየት ጥቅም ላይ ውሏል። አህራም ኦንላይን ምስሉን የወሰደው ከግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር ነበር።

በቅርቡ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ እየጨመረ መምጣቱ እና ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ድንበሩ አካባቢዎች ማሰማራቷ እየተዘገበ ይገኛል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ሱዳንን ለመደገፍ በድንበሩ ዙሪያ የመጡ የግብፅ ወታደሮችን የማያሳይ በመሆኑ እና መረጃውን ለመደገፍ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ልጥፉን ሀሰት በማለት ፈርጆታል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts