በ2 ጥር 2013 ዓ.ም World Page (ወርልድ ፔጅ) የተባለ ከ39,200 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በሚኒባስ ውስጥ ያለው አህያ ከትግራይ በኤርትራውያን ተሰርቋል በማለት ከዚህ በታች ያለውን ምስል ጋር አጋርቷል። ልጥፉ የወጣው በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እና በትግራይ አለመረጋጋት ተከትሎ ሲሆን በምስሉ ላይ የሚታየው አህያው በኤርትራውያን እንደተሰረቀ ለማሳየት በሚኒባስ መኪናው ታርጋ (የኤርትራ) ላይ ይጠቁማል። ልጥፉ በፌስቡክ ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት ሰአት ከ50 የሚበልጡ  ተጠቃሚዎች አጋርተውታል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ በኤርትራዊያን ከትግራይ የተዘረፈን አህያ እንደማያሳይ እና ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም  ጀምሮ በህወሃት በሚመራው የክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭት መነሳቱ የሚታወቅ ነው። የፌደራል መንግስትም በቅርቡ የህወሓትን ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ መኮንኖችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል ስራ ላይ እንደሚገኝ ያሳወቀ ሲሆን በወታደራዊ እንቅስቃሴ እና አለመረጋጋት መካከል የኤርትራ ወታደሮች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን አስተዳደር በመደገፍ በጦርነቱ ተሳትፈዋል የሚሉ ክሶች እና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንዳሉ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ብዙዎች በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ውስጥ ዘረፋ እያደረጉ ነው ሲሉ ይሰማሉ።

ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ18 ነሃሴ 2011 ዓ.ም  Reddit (ሬዲት) በተባለ የአሜሪካን በይነመረብ ላይ የተመሠረተ የምስል እና ቪዲዮ ማጋሪያ ማህበራዊ አውታር ላይ ነው። ከምስሉም ጋር “ይህች አህያ በሚኒባስ ወደ ቤቷ ልትሄድ ነው” የሚል ጽሑፍ ተያይዞ ተለቋል። 

የተቀናበረው ምስል

ዋናው ምስል

በእርግጥ የፌስቡክ ልጥፉ በተጋራበት ወቅት በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ግጭት የነበረ ሲሆን የኤርትራ ጦር በጦርነቱ እና በዘረፋው ውስጥ ተሳትፏል የሚሉ ክሶች እና ያልተረጋገጡ መረጃዎች ሲሰራጩ እንደነበር የሚታወስ ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ በኤርትራዊያን ከትግራይ የተዘረፈን አህያ እንደማያሳይ እና ምስሉ ቅንብር መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts