Waan Ofii (ዋን ኦፊ) የተባለ ከ39,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ በታህሳስ 20፣  2013 ዓ.ም በለቀቀው የፌስቡክ መረጃ “ከፍተኛ ቁጥር ያለው እና ትልልቅ መሳሪዎች የታጠቀ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ እየተጓዘ ነው”  በማለት ተከታዩን ምስል አያይዞ ለቋል። ሆኖም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ መረጃውን ለመደገፍ የተለቀቀው ምስል በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ስለሆነ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ላይ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በ8 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን ጦር አከራካሪውን የድንበር ግዛት መቆጣጠሩ እና ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ላይ መሆኑን በተለያዩ የመረጃ መረቦች እየተዘገበ ይገኛል። በ20 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮ-ሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ ለማብራራት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደነበረም የሚታወስ ነው። በወቅቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ (የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ)  ከ30 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የተደራጁ ጥቃቶች እንደነበሩ ገልፀው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች እየተዘረፉ ፣ ካምፖቻቸው እይተወረሩ እና አርሶ አደሮች የራሳቸውን እርሻ እንዳያጭዱ እንቅፋት እየሆኑባቸው እንዳለ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ንፁሀን መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን አክለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ሁለቱም አገራት በራሳቸው ወገን ያለውን ሪፖርት ለማቅረብ የተስማሙ ሲሆን የድንበር ማካለል ስራውም በፍጥነት እንዲጀመር ወስነዋል።

ሆኖም ቲን ዐይ (TinEye) የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው የሱዳኖች ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየገሰገሰ ነው የሚለውን መረጃ ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ29 ሰኔ 2010 ዓ.ም Haber7.com (ሀበር 7 ዶት ኮም) በተባለ የቱርክ የዜና ድረ-ገፅ ሲሆን የየመን ጦር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተወሰኑ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ እንደነበር ለመግልፅ ነበር ምስሉ ጥቅም ላይ የዋለው። 

  

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወታደራዊ ኃይል መካከል ግጭት መኖሩ እውነት ነው፤ ሆኖም ሀቅቼክ የፌስቡክ መረጃውን መርምሮ ምስሉ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ እየገሰገሰ መሆኑን የማያሳይ እና በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

Similar Posts