ጋጋ ቆሌ ኢጋ በተባለ ከ2900 በላይ ጓደኞች ባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ በአዳማ ከተማ ህፃናት እየጠፉ መሆኑን እና የኩላሊት ስርቆት አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አጋርቶ ነበር። መረጃው ከ25,000 ጊዜ በላይ ሼር ተደርጓል። ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት የተለቀቀው ምስል ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት ነው በማለት በይኗል።

 

የሰውነት ክፍል ንቅለ ተከላ (ኦርጋን ትራንስፕላንት) ከአንድ ለጋሽ አካል ላይ የተወሰደን የሰውነት ክፍል በበሽታ የደከመ ሌላ ሰው ላይ የመትክል ቀዶ ህክምና ሂደት ነው። ንቅለ ተከላው በአብዛኛው የሚካሄደው ለጋሹ ከሞተ በኋላ ቢሆንም የኩላሊት እና የጉበት ንቅለ ተከላ ግን ለጋሹ በህይወት እያለ ሊደረግ ይቻላል። ኩላሊት ከለጋሹ ሰውነት ላይ ከተለያየ በኋላ ከ36 – 48 ሰዐታት ድረስ መቆየት እንደሚችል የሚታወቅ ነው። የሰውነት ክፍል ልገሳ እጥረት መኖሩ፤ ህገወጥ የሰውነት ክፍል ሽያጭየሰውነት ክፍል ስርቆትየሰውነት ክፍልን በግዴታ የመውሰድ ወንጀሎች እንዲስፋፉ አድርጓል። የሰውነት ክፍል ሽያጭ ከኢራን በስተቀር በሁሉም ሀገራት የተከለከለ ሲሆን ቻይና ደግሞ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እስረኞችን የሰውነት ክፍል ያለ ፍቃዳቸው በመውሰድ  ትታወቃለች። በአለም ላይ ብዙ የሰውነት ክፍል ስርቆት እንዳለ ይነገራል።

 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተካሄደው መስከረም 11፣ 2008 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የጤና ኮሌጅ ከሚችገን ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባባር ነበር። እስከ ሚያዚያ 24፣ 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ለ102 ህሙማን ብቻ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ተችሏል። ይህም የሆነበት ምክንያት በአግባቡ የሰለጠኑ የቀዶ ህክምና ሃኪሞች እጥረት እንዲሁም ንቅለ ተከላውን ለማድረግ የሚያገለግል መሳሪያ እጥረት በመኖሩ ነው።

 

ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እነደሚያመለክተው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በ18 ነሐሴ 2009 ዓ.ም (ፌስቡክ ላይ ከመለቀቁ 17 ወራት በፊት) ነበር። ምስሉ የተነሳው በጣሊያን ሮም ውስጥ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች ከመኖሪያቸው ፒያሳ ኢንዲፔንዴዛ ከተባረሩ በኋላ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነበር።

የተለያዩ የሰውነት ክፍል ስርቆቶች መኖራቸው እውነት ቢሆነም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት ምስሉ በአዳማ ያልተነሳ መሆኑን እና ህፃናት ለሰውነት ክፍል ስርቆት እየታገቱ ነው ከሚለው መረጃ ጋር ምንም ግንኙነት እና ማስረጃ የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። በዚህ መሰረት ሀቅቼክ መረጃው ሀሰት ነው በማለት በይኗል።

 

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

 

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

 

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

 

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

 

Similar Posts