ከ130ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ መስከረም 4፤ 2015 ዓ.ም ላይ “አላማጣ ኳስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በተፈፀመ የአየር ጥቃት ወደ ቆቦ እየተጫኑ የነበሩ ሁለት ታንኮች መመታታቸው ታውቋል” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስልን አጋርቶ ነበር።

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ800 በላይ ግብረመልስ ሲያገኝ ከ30 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል።    

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

ጥቅምት 24 ፤ 2013 ዓ.ም በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ ዓመት በላይ አሳልፏል። 

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል አስወትቷል። 

ይህን ተከትሎ ለዘጠኝ ወራት ቆይቶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት [ለሰብዓዊ እርዳታ] ነሀሴ 18 ፤ 2014 ዓ.ም  ዳግም ወደ ግጭት ገብቷል።    

መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም በድምፂ ወያኔ ስም የተከፈተ እና ከ600ሺህ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገፅ ላይ በቀረበ ሪፖርት የፌደራሉ መንግስት በድምፂ ወያኔ የቴሌቪዥን ጣብያ ላይ የድሮን ጥቃት ማድረሱን ተገልጿል።  

መስከረም 14 ፤ 2015 ዓ.ም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ላይ “የፌደራሉ መንግስት ከደቂቃዎች በፊት በመቀሌ ከተማ ላይ የድሮን ጥቃት አድርሷል።” የሚል ፅሁፍን አጋርተው ነበር።

ሀቅቼክ ምስሉን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሉን የካቲት 27 ፤ 2014 ዓ.ም ጽሁፎችን በዩክሬን ቋንቋ በሚያቀርብ suspline.media በተሰኘ አንድ ድረገፅ ላይ አግኝቶታል። 

ምስሉን “የትራንስካርፓቲያን ብርጌድ ተዋጊዎች የሩሲያን BMP ታንክ ሲያወድሙ አንድ ወታደር መማረክ ችለዋል” በሚል  ፅሁፍ ስር ሀቅቼክ ያገኘው ሲሆን በፅሁፉም ውስጥ የወደሙ የሩስያ BMP ታንኮች እና የተማረከ የሩሲያ ወታደር ምስል ተካተዋል።

በ2014 እ.አ.አ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በተከሰተው ግጭት በየካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ሩሲያ ዩክሬንን ወራለች። በሩሲያ የተጀመረው ወረራ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ውስጥ ትልቁን የስደተኞች ቁጥር እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ምክንያት ወደ 7.3 ሚሊዮን(አንድ ሶስተኛ) የሚሆኑ ዩክሬናውያን ለስደት ተዳርገዋል።

ሊንክ

የፌደራል መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተደረገ ባለው ጦርነት የተለያዩ የአየር ጥቃቶችን እያደረገ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም በፌስቡክ ገፁ መረጃውን ይደግፍልኛል በማለት የተጠቀመው ምስል የተሳሳተ ነው።
ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ገጹ የተጠቀመውን ምስል መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Similar Posts