አንድ ከ200 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ነሀሴ 27 ፤ 2014 ዓ.ም ላይ “ሁለቱን እንቦቀቅላ ህፃናትን በጭካኔ አርዳ እና አንቃ የገደለችው ግለሰብ እቺ ናት” የሚል ፅሁፍን በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። 

ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ9 ሺህ በላይ ግብረመልስን ሲያገኝ ከ1400 ጊዜ በላይ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን መርምሮ ምስሉን ሀሰት ብሎታል።    

ነሀሴ 26 ፤ 2014 ዓ.ም በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አውታሮች ላይ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚንየም ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤት መንደር አካባቢ በቤት ሰራተኛ አማካኝነት የ2 እና 3 አመት ህፃናት እንደተገደሉ ተነግሮ ነበር።

ነሀሴ 26 ፤ 2014 ዓ.ም ቢቢሲ አማርኛ ያናገራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ “እጅግ በጣም አሳዛኝ እና ዘግናኝ” በተባለው በዚህ ወንጀል የተጠረጠረችው የቤት ሠራተኛ የ19 ዓመት ወጣት መሆኗን የገለፁ ሲሆን በሁለት ህጻናት ላይ ግድያው ከተፈጸመች በኋላ ተጠርጣሪዋ ወንጀሉን መፈጸሟን በማመን ለፖሊስ እጇን ከሰጠች በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

 ይህ የፌስቡክ ፖስትም ይህንን መረጃ መሰረት አድርጎ ተጋርቷል። 

ነገርግን ሀቅቼክ የጎግል የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋን ተጠቅሞ ምስሉን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከሀገር ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞችን ወደ ሀገር እንዲመለሱ መጋበዛቸውን ተከትሎ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም አክቲቪስት እና ፖሊቲከኛ ጀዋር መሀመድን ለመቀበል በተደረገ ስነ ስርዓት ላይ ቦምብ ለመጣል የተዘጋጀች ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏን ከሚገልጽ ፅሁፍ ጋር ተጋርቶ አግኝቶታል። 

ሊንክ

ከሰሞኑን በቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በሰራተኛቸው አማካኝነት የተገደሉ ህፃናት ቢኖሩም ይህ የፌስቡክ ገፅ የሰራተኛዋን ምስል ያሳያል ብሎ የተጠቀመው ምስል የተሳሳተ ነው።
ስለዚህም ሀቅቼክ ምስሉን መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

Similar Posts